“ታላቁ መሪ መለስ ቢኖር ኖሮ እዚህ ችግር ውስጥ አንገባም”
ዋዜማ ራዲዮ- ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በአዲስ አበባ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩ የህወሓት አባላት በየክፍለ ከተሞቻቸው በተጠሩ የጥልቅ ተሀድሶ መድረኮች እርስ በእርስ እየተገማገሙ ይገኛሉ፡፡ ተሀድሶው በአስሩም ክፍለ ከተሞች በተለይም ዕሁድ ሙሉ ቀን የተካሄደ ሲሆን በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ደግሞ ከሰኞ ጀምሮ ቀኑን ሙሉ ተሀድሷቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሌሎች ጥልቅ ተሀድሶውን በግርድፉ አጠናቀዋል፡፡
ብዙዎቹን ተሀድሶዎች የሚመሩት ከአዲስ አበባ መስተዳደር የድርጅት ጽሕፈት ቤት የተወከሉ ከፍተኛ የህወሓት ካድሬዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
እንደቀድሞው ጊዜ የመገማገሚያ መድረኮች በሚኒስትርነት ማዕረግ ያሉ አንጋፋ የሕወሓት ባለሥልጣናት ወደ ታች ወርደው መካከለኛ አመራሩን ያወያያሉ ተብሎ ፕሮግራም ተይዞ የነበረ ሲሆን በመጨረሻው ሰዓት ይህ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ በምትኩም የጽሕፈት ቤትና የቢሮ ከፍተኛ ኃላፊዎች መድረኮቹን መርተዋል፡፡
የተሀድሶው አንኳር ነጥቦች ላይ መጠነኛ ዉዝግብ በተሰብሳቢዎች ዘንድ ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን በህወሓት መካከለኛ አመራር ታሪክ እንዲህ የደመቀ ግምገማ ከ1993 ክፍፍል ወዲህ የመጀመርያው ነው እስከማለት የደረሱ ካድሬዎች አልጠፉም፡፡ የህወሓት የጽሕፈት ቤትና የቢሮ አመራሮች በበኩላቸው በብዙዎቹ መድረኮች ላይ አባሎቻቸውን ለማሳመንና እንደ ወትሮው ወጥ የኾነ አቋም አስታጥቆ ለመመለስ ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡
የዉዝግብ መነሻ የኾኑት በዋናነት የመወያያ ሰነዱ ላይ የሰፈሩ አንዳንድ የመወያያና የመገማገሚያ ነጥቦች ሲኾኑ ነጥቦቹ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ አዲስ የሀሳብ ሙግትን የሚጭሩ የማይደፈሩ የሚመስሉ ነጥቦች ተካተውበታል ተብሏል፡፡
ከእነዚህ አወዛጋቢ ርእሰ ጉዳዮች መካከል በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ጤናማ ባልሆነ መልኩ ያለልክ መመካት፣ በትግራዊ ክልላዊ፣ አውራጃዊ ጎጠኝነት ስሜት ማበብ ዙርያ፣ በሕወሓት የፌዴራል ሥልጣን ድርሻ ማነስ ዙርያና ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር አብሮ በመኖር ጉዳይ ላይ የተነሱ ነጥቦች አንኳሮቹ ነበሩ፡፡
ሰነዱ ባለፉት 15 ዓመታት ተስፋ የሚሰጡና አገሪቱን ወደ መካከለኛ ገቢ የሚያደርሱ ዓለምን ያስደመሙ ምጣኔ ሀብታዊ ጉዞ እንደተካሄደ በማተት የሚጀምር ሲኾን ከዚህ የልማት ጉዞ በኋላ ልማቱና እድገቱ የፈጠረው የሕዝብ የልማት ፍላጎት መገንፈሉን ያስረዳል፡፡ ምንም እንኳ ልማቱ ሰፊ ቢኾንም የሕዝብ ፍላጎቱን ሊቀድም አለመቻሉን ሰነዱ ካመነ በኋላ ከከፍተኛ ተቋማት በብዛት የሚመረቁ ወጣቶች በሚፈልጉት ደረጃ ሥራ ማግኘት አለመቻላቸው፣ የሕዝብ ቁጥር በከተሞች አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር አገሪቱን የእድገቷ ዳፋ መልሶ እየተበተባት እንደሆነ ሰነዱ ለመተንተን ይሞክራል፡፡
በተለይም የአመራር መፋዘዝ እና የመልካም አስተዳደር እጦት እንዲሁም ሥልጣንን ለግል ማበልጸጊያነት ማዋል ኋላ ላይ ለተፈጠሩ የቅርብ ጊዜ የሕዝብ ብሶቶች ምንጭ እንደሆኑ ያስረዳል፡፡
የህወሓት ሚናን በሚተነትንበት አንቀጹ ብዙ አባሎቻችን ችግሩን የተረዱበት መንገድ የተንሸዋረረ ነው፣ ይህም መስተካከል አለበት ሲል ይመክራል፡፡ ከነዚህ አስተሳሰቦች አንዱ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “ታላቁ መሪ” እና “የብሔር ብሔረሰቦች መብትና እኩልነት የተረጋገጠባት የዘመናዊት ልማታዊት ኢትዮጵያ ቀያሽ መሐንዲስ” መኾናቸው የማይካድ ኾኖ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠሩ ሕዝባዊ አመጾች የተፈጠሩት ግን እርሳቸው ባለመኖራቸው ነው የሚለው አስተሳሰብ የህወሓት አባላት ላይ በስፋት መንሰራፋቱን ከዳሰሰ በኋላ ይህን አስተሳሰብ ጊዜ ሳይሰጡ መንግሎ ማውጣት ያሻል ሲል ሰነዱ ምክሩን ያስቀምጣል፡፡
በበርካታ የህወሓት አባላት ዘንድ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተነሳው ረብሻና ችግሩን ለመፍታት የተኬደበት መንገድ አርኪ ሆኖ አይታሰብም ይላል ሰነዱ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም ሁከቶች የተፈጠሩት ታላቁ መሪ በሕይወት ባለመኖራቸውን ነው የሚል ቁጭት በስፋት በድርጅት አባላት ዘንድ እንደሚንጸባረቅም ያትታል፡፡ በተለይ ችግሩ በአገር ደረጃ ሊሰፋ የቻለው አቶ መለስና በሳል አመራራቸው ባለመኖራቸው ነው፣ ታላቁ መሪ ቢኖሩ ከዚህ ሁሉ ችግር በጊዜ ያወጡን ነበር የሚል ጠንካራ አስተሳሰብ በህወሓት ካድሬዎች ዘንድ ስር እየሰደደ መምጣቱን ካስረዳ በኋላ “ይህ ግን ትክክል አይደለም” ሲል ይሞግታል፣ ሰነዱ፡፡
በአንዳንድ መድረኮች ላይ ይህን ሰነድ ያለመቀበል አዝማሚያዎች መታየታቸው ተዘግቧል፡፡ ለምሳሌ በጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት አዳራሽ በተካሄደ የጥልቅ ተሀድሶ መድረክ ይህ ነጥብ ብዙም እንዳልተዋጠላቸው የገለፁ የሕወሓት ካድሬዎች በተቻለ መጠን ፈጣን እርምጃን የሚወስድ፣ መፍትሄ የሚያመነጭ፣ ንቁ፣ ቆራጥና በሳል አመራር አለመኖሩ ለዚህ ችግር ዳርጎናል ሲሉ በግልጽ ለማንጸባረቅ ሞክረዋል፡፡
“እኔ ለምሳሌ ታላቁ መሪ ቢኖሩ እዚህ ማጥ ዉስጥ እንገባ ነበር ብዬ አላስብም፣ ይህ እምነቴ ነው፣ እንደዚህ ለምን ታስባለህ ልባል አይገባም” ሲል የተናገረ ካድሬ በመድረክ መሪው ፈጠን ያለ ምላሽ ተሰጥቶታል፡፡ “የትኛውም አገር፣ በማንኛውም ሁኔታ ፖለቲካዊ ችግር ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ ይህ በተለይ በፈጣን እድገት ላይ ባሉና በርካታ ሕዝብ ባላቸው አገራት የሚፈጠር ችግር ነው፡፡ ታላቁ መሪም ምርጫ 97ን ተከትሎ መጠነኛ ችግር ገጥሟቸው እንደነበር መዘንጋት አይኖርብንም፡፡ ” የሚል መልስ ሲሰጠው መነጋገሪያውን መልሶ በማንሳት እርሳቸው ችግሩን ወዲያው ነበር የፈቱት በማለት ለመከራከር ሞክሯል፡፡
ከብዙ ዉይይትና ማግባባት በኋላም ቢኾን በብዙ ካድሬዎች የረብሻው መፈጠር ምንጭ የአመራር ክፍተት እንደሆነ ሲከራከሩ መሰማቱ አስገራሚ ሆኗል፡፡ “ቀላል የነበሩ ችግሮች መወሳሰባቸውን ካልካድን ችግሮቹ መፈታት ያልቻሉት በአመራር ክፍተት መሆኑን ለምን እንሸፋፍናለን?” ሲሉም ጠንካራ ሙግት ለማንሳት የሞከሩም አልታጡ፡፡
በትግራይ ተወላጆች ዘንድ የጎጥና የአውራጃነት አመለካከት ስር እየሰደደ መሆኑን በሚያትተው የሰነዱ ሌላ ክፍል የአድዋ ተወላጆች በስልጣን ረገድ የተሻለውን ቦታ እየያዙ የሌሎች ትግራይ ክልል ተወላጆች ከፖለቲካው ተገለዋል የሚል አመለካከት በተወላጆች ዘንድ መስፈኑን ሰነዱ አብራርቷል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ለአዲግራት መንገድ አልተሠራም፣ ተምቤን ልማት ርቋታል፣ አክሱም ይሄ የለም፣ የእንትጮ ኔትወርክ በዚህና በዚያ መሥሪያ ቤት ተዘርግቷል እየተባለ እርስ በርስ መወነጃጀል እንደተጀመረ ተብራርቷል፡፡ የትኛውም ቦታ ቢለማ የኢትዮጰያ ልማት ነው፣ ከክልል አልፈን በአገር ደረጃ ማሰብ ሲገባ እኛ ግን የጎጥ፣ የአውራጃ አስተሳሰብን እያስፋፋን ነው ሲሉ ሰነዱን ተንተርሰው ሰብሳቢዎቹ ካድሬዎቹን ተችተዋል፡፡
የሰነዱ ሌላኛው ክፍል የህወሓን የሥልጣን ድርሻ በፌዴራል ደረጃ እየተሸረሸረ መጥቷል በሚለው ጉዳይ ላይ አጭር ማብራሪያ ለመስጠት የሞከረ ሲኾን ህወሓት ለሕዝቦች እኩልነት የብዙ ሺህ ዉድ ልጆቹን ደም የገበረ ድርጅት እንደሆነ ያብራራል፡፡ ኾኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህንንና ያንን የሚኒስትርነት ደረጃ አጥተናል፣ በሠራዊቱ ዉስጥ ያለን ቦታ ተገድቧል፣ እየተባለ ለመረጃ ቅርብ በኾነው መካከለኛ ካድሬ ጭምር የተሳሳተ አመለካከት እያበበ መምጣቱ ትክክል አይደለም፣ የተንሸዋረረ ሀሳብ ነው ሲል ይኮንናል፡፡
ሕወሓት በፌዴራል ደረጃ ያለው ድርሻ እየሳሰ መጥቷል የሚል ስጋት በብዙ አባሎቻችን ላይ እየተንጸባረቀ መሆኑንና ይህም ለአገር ግንባታ ብቻም ሳይሆን አብሮ ለመኖር እንቅፋት እየሆነ እንደመጣ ለተሰብሳቢዎቹ ያስረዱ የጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤቱን ስብሰባ የመሩ መድረክ መሪ ከመካከለኛ አመራሩ መጠነኛ ተቃውሞና ጉምጉምታ እንደደረሰባቸው ተጠቅሷል፡፡
ከነዚህ ነጥቦች ሌላ ሥልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል ጉዳይ የተነሳ ሲሆን ድርጅቱ ከእንግዲህ እነዚህን አመራሮች የሚሸከምበት ትከሻ የለውም ተብሏል፡፡ ኾኖም ከፍተኛ ግምገማ ተካሄዶባቸው ሳለ በሙስና መጨማለቃቸው የደርሰባቸው አባሎች በዝውውር ሌላ ሹመት እየሰጣችሁ ችግሩ ዉስጥ የምትከቱን ራሳችሁ ናችሁ ሲሉ አንዳንድ ካድሬዎች ተሟግተዋል፡፡
በመጨረሻ እርስበእርስ የመገማገሚያ ነጥቦችና የአባላት ሙሉ ስም የተዘረዘረበት ፎርም በቡድን በቡድን እየታደለ ‹‹በጥልቅ ታድሻለሁ››፣ ‹‹የተዛነፈ አስተሳሰቤን አርሜያለሁ›› የሚል ሂስና ግለ ሂስ መድረክ ተካሄዷል፡፡ ካድሬው በአንኳር የዉይይት ነጥቦች መግባቢያ ላይ መድረሱን ቃል የሚገባበት ሂደት ሲሆን ይህም ከአንገት በላይ ለደንብ የሚፈጸም አሰራር እንደሆነ ይታመናል፡፡
በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች ግምገማው ማክሰኞ ዕለት የቀጠለ ሲሆን አንዳንዶች ግን ወጥ ባልሆነ መንገድ ተሀድሷቸውን በአጭሩ ፈጽመው እንዳጠናቀቁ ምንጮቻችን ገልጠውልናል፡፡