ሄኖክ መሀሪ እና ወንድሞቹ ተወልደው ላደጉበት ቤት ያላቸው ፍቅር የትየለሌ ነው፡፡ ፒያሳ የሚገኘው ቤታቸው ድክ ድክ ያሉበት ብቻ አልነበረም፡፡ ይልቅስ በሙዚቃ ህይወት ውስጥ በነበሩት ወላጆቻቸው አማካኝነት የሙዚቃን ሀ…ሁ የቆጠሩበት እንጂ፡፡ በተለያዩ ስልቶች የተቀናበሩ በርካታ ሙዚቃዎችን ከማድመጥ እስከ የሙዚቃ መሳሪያ ትምህርት ድረስ የዘለቀ የቤት ውስጥ ቆይታ ነበራቸው፡፡ እንዲህ የማይረሳ የልጅነት ጊዜ ያሳለፉበትን ቤት ለመዘከር ሄኖክ ለፋሲካ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀውን አልበሙን በቤታቸው ቁጥር “790” ሲል ሰይሞታል፡፡
“ማንነትህን የመግለጽ ያህል ነው” ይላል ሄኖክ ስለ አልበሙ አሰያየም ለዋዜማ ሲያስረዳ፡፡ “የፒያሳ ልጅ ነኝ ትልና በመጨረሻ ወደ ቤትህ ትመጣለህ፡፡”
አልበምን በቁጥር መሰየም ያልተለመደ አይደለም፡፡ ከሰባት አመት በፊት ጥቁር አሜሪካዊው ዘፋኝ ኬ አለን በኢትዮጵያ የስልክ መለያ “251” የአልበሙን መጠሪያ ሰይሞ ነበር፡፡
የሄኖክ አዲስ አልበም 15 ዘፈኖች የያዘ ሲሆን ሙሉ በሙሉ የተቀናበረውም ሆነ ዜማው የተደረሰው በእርሱ በራሱ ነው፡፡ አስር ያህል ዘፈኖቹ ሄኖክ እና ወንድሞቹ ባቋቋሙት “መሀሪ ብራዘርስ” ባንድ ታጅቦ በቀጥታ ከመድረክ የተቀዳ ነው፡፡ ሬጌ፣ ሮክ፣ ፈንክን በመሰሉ የሙዚቃ ስልቶች የተቃኙ ዘፈኖች የተካተቱበት አልበም በ”contemporary /urban pop music” ዘውግ ሊመደብ እንደሚችል ሄኖክ ያስረዳል፡፡
ዘፈኖቹ በአጠቃላይ “ጠንካራ መልዕክት” ያላቸው እና “አዎንታዊ አመለካከትን” የሚያንጸባርቁ እንደሆኑ ሄኖክ ይገልጻል፡፡ ስለ ሴት ልጅ ፍቅር፣ ስለ ማንነት፣ ስለ ሀገር እና ስለ ቤተሰብ ጭብጥ ያላቸው ዘፈኖች በአልበሙ መካተታቸውን ያብራራል፡፡
“ዘፈኖቹ የኑሮ ፍልስፍናዬን እና ዓለማችንን የማይበት አተያይ ይንጸባረቁባቸዋል” ሲል ሄኖክ ለዋዜማ ተናግሯል፡፡
ለዚህ ደግሞ ከአስራ አምስቱ የአልበሙ ዘፈኖች የአስራ ሁለቱን ግጥም ራሱ መድረሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ሶስት ዘፈኖችን የጻፈችለት ደግሞ ድምጻዊ ዘሪቱ ከበደ ናት፡፡ “አደራ” የተሰኘው ከሶስቱ አንዱ ዘፈን የዘሪቱ ፊልም በሆነው እና ሄኖክም በረዳት ተዋናይነት ለተሳተፈበት “ቀሚስ የለበስኩ ‘ለት” የዋለ ነው፡፡
“ዘሪቱ የሰጠችኝ የፍቅር ዘፈኖችን ነው” ይላል ሄኖክ ስለ ጭብጦቹ ተጠይቆ ሲመልስ፡፡ “እየተማከርን ነው የሰራናቸው፡፡”
ዘሪቱም ብትሆን “ጥሩ መልዕክት ያለው እና ጤነኛ ሙዚቃ” መምረጣቸው ከሄኖክ ጋር እንደሚያስማማቸው ትናገራለች፡፡ ሁለቱ ዘፋኞች ያላቸው ቅርበት በዘፈን ከመማከር በላይ እንደሆነም ዘሪቱ ትመሰክራለች፡፡ “እንደ ወንድም ነው” የምትልለትን ሄኖክን የተዋወቀችው ገና የ13 ዓመት ታዳጊ እያለች ነው፡፡
በለጋ እድሜያቸው ሙዚቃን አብረው መጫወት የጀመሩት ዘሪቱ እና ሄኖክ አንዱ በአንዱ ስራ ተሳትፎ እያደረጉ እስካሁን አሉ፡፡ “ለረጅም ዓመታት ከማውቃቸው ጥቂት ሰዎች አንዱ ነው” ትላለች ለአልበሙ በተሰራው አጭር ዶክመንተሪ መግቢያ ላይ፡፡
ዘሪቱ የመጀመሪያ አልበሟን ካወጣች በኋላ ለኮንሰርት ከከተማ ከተማ ስትዞር ያጀባት “መሀሪ ብራዘርስ” ባንድ ነበር፡፡ በኮንሰርቶቿ ከሄኖክ ጋር በቅብብሎሽ የምታቀርበው ተወዳጅ የእንግሊዘኛ ዜማም ተወዳጅነት አትርፏል፡፡ ሁለቱ ዘፋኞች ከዓመታት በኋላ ዳግም በዚህ አልበም በድምጽ ተጣምረዋል፡፡ ቤቲ ጂም በሌላ ዘፈን ከሄኖክ ጋር አብራ አቀንቅናለች፡፡
“790” ለሄኖክ ሁለተኛው አልበም ነው፡፡ የዛሬ አስር ዓመት “እውነተኛ ፍቅር” የተሰኘ አልበም ለሙዚቃ አፍቃሪያን አበርክቶ ነበር፡፡ ያኔ በዘፈን ማስተላለፍ በሚፈልገው መልዕክት ይሁን በመረጣቸው የዜማ አይነቶች ምክንያት “አልበሙ መዝሙር ይመስላል” በሚል ተተችቷል፡፡ ይህንን ትችት ሄኖክ አልረሳውም፡፡
“ከስህተቶቼ ተምሬያለሁ፡፡ መያዝ ያለባቸው የማንነት ቀለማት ግን እንዳሉ ናቸው” ይላል ያሻሻላቸውን እና ‘ይዤያቸው መቆየት አለብኝ’ ብሎ ስለሚያምናቸው ነገሮች ሲናገር፡፡
ይህ “የራስን ቀለም አስጠብቆ መቆየት” መርህ ግን በመጀመሪያው አልበም ያጋጠመው አይነት ምላሽ እንዳያስከትልበት የሚፈሩ ሙዚቀኞቸ አሉ፡፡
“አልበሙ አዲስ ነገር ያለው ነው፡፡ ሰው ከለመደው ቅርጽ ትንሽ ለየት ያለ ነው” ይላል የጃኖ ባንድ ሙዚቀኛ እና የድምጽ ኢንጂነሩ ኪሩቤል ተስፋዬ በአልበሙ ማስተዋወቂያ አጭር ዶክመንተሪ ላይ፡፡ “ከዚህ በኋላ ብዙ ነገሮችን ይቀይራል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም አልበሙ ያተኮረው በሁሉም ጎን ሙሉ የሆነ ነገር ለመስጠት ነው፡፡”
አልበሙ “ቀያሪ” ይሁን አይሁን ለመገምገም በፋሲካ ዋዜማ እስኪለቀቅ ሳምንት መጠበቅ ግድ ይላል፡፡ እስከዚያው ከአልበሙ ውስጥ ተመርጠው፣ የሙዚቃ ቪዲዮ ተሰርቶላቸው፣ በነጠላ ዜማ መልክ የተለቀቁትን “የኪራይ ቤት” እና “እወድሻለሁ”ን እያጣጣሙ መቆየት ነው፡፡