ዋዜማ- ለሁለት ሳምንታት የሚደረገው ዓለማቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (COP27) መክፈቻ ላይ ለመታደም ወደ ግብፅ ያመሩት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕዳሴው ግድብ፣ ከሕወሓት ጋር ስለተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ብሎም የብድርና ዕርዳታ ጉዳዮች ላይ የዲፕሎማሲ ስራ ለመስራት ዕቅድ እንዳላቸው ዋዜማ ከዲፕሎማቲክ ምንጮች ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።


በግብፅ የባሕር ዳርቻ ከተማ ሻርም አል ሼክ በሚደረገውና አርባ ሺህ ያህል ተሳታፊዎች በሚገኙበት በዚህ ዓመታዊ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ በርካታ የሀገር መሪዎችና ዓለማቀፍ ድርጅት መሪዎች ይገኛሉ።
በነገው ዕለት ማክሰኞ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ለጉባዔው ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።


የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ፣ የአሜሪካ የሩስያና ሌሎች በርካታ መሪዎች በሚታደሙበት በዚህ ጉባዔ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክትን ከማስተዋወቅ በዘለለ ለታዳጊ ሀገሮች የልማት ፕሮጀክት በቂ ድጋፍ እንዲሰጥ ጥሪ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። የሕዳሴ ግድብ ታዳሽ የኀይል ምንጭ መሆኑን በመጥቀስ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን ግንባታ ፍትሐዊነት ያስረዳሉ ተብሏል።


ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ተከትሎ ከምዕራቡ ዓለም በገጠማቸው ብርቱ የዲፕሎማሲ ጫና ከዓለማቀፍ መድረኮች ርቀው ቆይተዋል።

አሁን በግብፅ ቆይታቸው ከጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር ተገናኝተው እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
በተለይም ከዓለም ባንክና ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ሃላፊዎች ጋር በእንጥልጥል ባሉ የብድርና ድጋፍ እንዲሁም የብድር ሽግሽግ ጉዳዮች ላይ የመነጋገር ዕቅድ አላቸው።


የዓለም የገንዘብ ድርጅት ኢትዮጵያ ያለባትን 30 ቢሊየን ዶላር ያህል የዉጪ ብድር የመክፈያ ጊዜ ለማሸጋሸግ ያቀረበችው ጥያቄ በጦርነቱ ምክንያት በይደር ውሳኔ ሳይሰጠው ቆይቷል። ባለፈው ሳምንት ከሕወሓት ጋር የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ድርጅቱ የኢትዮጵያን የብድር ሽግሽግ ለመመልከት የባለሙያ ቡድን ወደ አዲስ አበባ እንደሚልክ ፍንጭ ሰጥቷል።

የሕዳሴው ግድብ
ዓለማቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ ግብፅ ካለፉት ወራት ጀምሮ ባለባት የውሃ ዕጥረት የገጠማትን የሕልውና ፈተና የሚያሳዩ መረጃዎችን አዘጋጅታ በጉባዔው ላይ ለታደሙ ከሶስት ሺህ በላይ ጋዜጠኞች አሰራጭታለች።


የተመረጡ ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙሀን በግብፅ የዓባይ ወንዝ ለሕልውናዋ ያለውን ሚና የሚያሳይ ዘገባ እንዲያዘጋጁ ተደርጓል። የግብፅ ጥረት የሕዳሴው ግድብ በህልውናዋ ላይ አደጋ መደቀኑን ለቀረው ዓለም ማስረዳት ላይ ያተኮረ ነው።


ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከግብፁ ፕሬዝዳንት ጋር ሲገናኙ በአፍሪቃ ሕብረት አደራዳሪነት ሲደረግ የነበረውንና ያለስምምነት የተቋረጠውን የሶስትዮሽ ድርድር መቀጠል ስለሚቻልበት ሁኔታ ይመካከራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ዐቢይ የኢትዮጵያን አቋምና ፍላጎት የማስረዳት ትልቅ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።

በቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀጥተኛ ተሳትፎ በሕዳሴው ግድብ ድርድር ላይ ኢትዮጵያ ለተደረገባት ጫና እምቢ በማለቷ ከዓለም ባንክ ልታገኝ ይገባ የነበረውን ብድር ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ማገዱ ይታወሳል።

ዐቢይ ባለፈው ሳምንት ከሕወሓት ጋር ስለተደረሰው ስምምነትና የሰብዓዊ ዕርዳታን በተመለከተ ከተለያዩ ሀገራት መሪዎችና ድርጅቶች ጋር እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።

ጉባዔው
ዓመታዊው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ዋና ትኩረቱ ከዚህ ቀደም ለታዳጊ ሀገራት ቃል የተገባው የገንዘብ ድጋፍ ተግባራዊ መሆን ያልቻለበትን ምክን ያት ተወያይቶ ተፈፃሚ የሚሆንበትን መንገድ መፈለግ ነው። ጉባዔው ከ13 ዓመታት በፊት ለታዳጊ ሀገሮች ድጋፍ የሚውል 100 ቢሊየን ዶላር በየዓመቱ ከፈረንጆቹ አቆጣጠር 2020 ጀምሮ ከሀብታም ሀገራት እንዲሰባሰብ ውሳኔ ቢያሳልፍም ተግባራዊ መሆን ሳይችል ቀርቷል። የዓለማችንን የሙቀት መጠን ጭማሪ በ2 ዲግሪ ሴልሺየስ ለመገደብ የተቀመጠው ግብም እስካሁን አልተሳካም።

To contact Wazema Editors please write to wazemaradio@gmail.com