ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በእዳ ጫና ውስጥ ለመዘፈቁ ማሳያ የውጭ ብድር ብቻ ሳይሆን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመቶ ቢሊየኖች ተበድረው በሚፈለገው ጊዜ መክፈል አለመቻላቸውም ነው። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል;የስኳር ኮርፖሬሽንና የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላለፉት አመታት ተበድረው ሳይመልሱ ያከማቹት ገንዘብ በመቶ ቢሊየኖች የሚቆጠር መሆኑን አሁን የየኮርፖሬሽኖቹ ሀላፊዎች በይፋ የሚናገሩት ሀቅ ሆኗል።
የገንዘብ ሚኒስቴር የአውሮፓውያኑ 2017/2018 አመታዊ የመንግስታዊ ዘርፍ የእዳ ክምችትና አስተዳደር ሰነዱ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለልማት ድርጅቶች ካበደረው ገንዘብ ውስጥ መመለሻ ጊዜው የደረሰው የዚህን ዓመት ሳይጨምር ከ336 ቢሊየን ብር በላይ ሆኗል ሲል አስፍሯል።
ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች እንዳረጋገጠችው ይ ህ ግዙፍ ብድር እየተመለስ አይደለም።የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ያለበት የሀገር ውስጥ ብድር 300 ቢሊየን ብርን አልፏል።የስኳር ኮርፖሬሽንም ከሀገር ውስጥ የወሰደው ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ሆኗል።የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ( ሜቴክ )የ70 ቢሊየን ብር ባለ እዳ ነው።
እነዚህ ከሀገሪቱ አመታዊ አጠቃላይ ምርት በመቶኛ የሚቆጠር ገንዘብን በብድር የያዙት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ግን ብድራቸውን እየመለሱ ላለመሆኑ የሜቴክ ሀላፊው ብድጋዲየር ጄነራል አህመድ ሀምዛ ለመንግስታዊው እለታዊ ጋዜጣ አዲስ ዘመን ሰሞኑን በሰጡት ቃለ መጠይቅ ካለብን 70 ቢሊየን እዳ 57 ቢሊየኑን ይሰርዝልን ፣ 13 ቢሊየኑን ደግሞ በጊዜ ሂደት እንከፍላለን ብለዋል።
ሜቴክ የገባበት የንብረት ሽያጭም ብዙም የእዳ ከፋይነት አቅም እየፈጠረለት አለመሆኑን ዋዜማ ራዲዮ ከዚህ ቀደም ዘግባለች።የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይልና የስኳር ኮርፖሬሽንም ተመሳሳይ አካሄድ ውስጥ ነው ናቸው ማለት ።
ይህ ሁሉ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተወሰደ ገንዘብ መመለሻው እንዴት ነው ብለን ለጉዳዩ ቅርበት ላላቸው ሁለት ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ላቀረብነው ጥያቄ ያገኘነው መልስ የልማት ድርጅቶቹ ብድሩን ከንግድ ባንክ የወሰዱት አብዛኛው በሚባል ደረጃ በመንግስት ዋስትና በመሆኑ የብድር አከፋፈሉ ችግር የመጣው ከልማት ድርጅቶቹ ከሆነ ብድሩን መንግስት በጀት ይዞ የሚከፍለው ይሆናል ብለውናል። ካልሆነም ብድሩ የሚሰረዝ ይሆናል የሚል ምላሽም ሰጥተውናል። እዳ ክምር ውስጥ ያሉት ተቋማት እዳ የመክፈል አቅም ሲታይም መንግስት ከዚህ የተለየ አማራጭ እንደሌለው መገመት አይከብድም።
በተለይ እነዚህን የልማት ድርጅቶች በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ለግሉ ዘርፍ የማስተላለፍ እቅድ በመኖሩ እስከዚ የተቆለለ ብድራቸው የሚገዛቸው ባለሀብት ሊኖር ስለማይችል መንግስት እዳውን መሸፈን ወይ መሰረዝ የሚጠበቅበት ሆኗል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ ልማት ባንክን የተበላሸ ብድር አብዛኛውን ከመሰረዝ ውጭ አማራጭ የሌለ መሆኑን የመንግስት ምንጮች ይጠቁማሉ። ልማት ባንክ ካባደረው 46 ቢሊየን ከሚደርስ ብር 40 በመቶው ወይንም 18.4 ቢሊየን ብሩ የተበላሸ ብድር መሆኑን ባንኩም አምኗል። ልማት ባንኩ ይህንን መመለሱ አጠራጣሪ የሆነ ብድርን ለማስመለስ እያደረኩ ነው ያለው ጥረትም ብዙም ስኬታማ አልሆነም። “በሰፋፊ እርሻ አልሚዎች” የተወሰደው ብድር ሊመለስ ያልቻለ መሆኑን ዋዜማ ራዲዮ ከዚህ ቀደም ዘግባለች።
መንግስት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለልማት ባንኩ ድጋፍ ለማድረግ ተቋሙ ያለበትን ችግር ማስተካከል አለበት ሲል ግዴታ አስቀምጦ ነበር ።ሆኖም ባንኩ በአመራር የሰው ሀይል ለውጥ ሊያመጣ ይችል ይሆናል እንጂ የተበላሸ ብድሩ ላይ ብዙም ተስፋ የሚጣልበት አልሆነም። ስለዚህ የልማት ባንኩን የተበላሸ ብድር ሰርዞ እንደ አዲስ ማደራጀት ከፊት ያለ አማራጭ ሆኗል። [ዋዜማ ራዲዮ]