ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች የመረጃ ልውውጥ ስምምነት ካላቸው ሀገሮች አንዷ ናት። በተመሳሳይ ከቻይና ጋርም ቅርብ ወዳጅነት አላት። እንዳውም ኢትዮ ቴሌኮም ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ የቻይና ኩባን ያ መሳሪያዎችን ይጠቀማል። አሁን አሜሪካ የቻይናው ሁዋዌን መሳሪያዎች ከሚጠቀሙ ሀገራት ጋር የፀጥታና ደህንነት መረጃዎችን መለዋወጥ አቆማለሁ እያለች ነው። ጉዳዩ ኢትዮቴሌኮምን አጣብቂኝ ውስጥ ከቶት ስንብቷል። 

ቻይና ሰራሽ የኔትወርክ መስረተ ልማትን የሚጠቀመው ኢትዮቴሌኮም በአሜሪካና በቻይና የንግድ ውዝግብ ሳቢያ የገጠመውን ፈተና ከቻይና መንግስት ጋር በመነጋገር ለመፍታት እየሞከረ መሆኑን ለዋዜማ ገልጿል።

 አሜሪካ እና ቻይና በገቡበት የንግድ ጦርነት ሳቢያ ሁዋዌ የተሰኘው የቤይጂንግ ግዙፍ አለማቀፍ የቴሌኮም ኩባንያ ሰለባ እየሆነ መጥቷል።ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሀገራቸው የቴሌኮምና ኤሌክትሮኒክስ ምርት አምራች ግዙፍ ኩባንዮች ሁዋዌ ለግብአትነት የሚጠቀማቸው ምርቶች እንዳያቀርቡለት የስራ አስፈጻሚነት ስልጣናቸውን ጭምር እየተጠቀሙ ውሳኔ አሳልፈውበታል። የቻይናው ሁዋዌ በተለያዩ ሀገራት ለሚሰራቸው የቴሌኮም ስራዎች የአሜሪካ ኩባንዮች ምርቶችን እንደመጠቀሙ ከወዲሁ ቢሊዮን ዶላሮችን ከትርፉ እንደሚያጣ ታምኗል።

  ሁዋዌ ኢትዮጵያ ከአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2010 ጀምሮ በተገበረችው የሁለተኛው ዙር የቴሌኮም ኔትወርክ ማስፋፊያ ውስጥ ትልቁን ስራ የሰራ ነው።የአዲስ አበባን ኔትወርክ ማስፋፊያም ሰርቷል።ከሌላኛው የቻይና ዜድቲኢ ኩባንያ ጋር በመሆንም ትልቁን ድርሻ በመያዝ እስከ ሶስት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የኔትወርክ ማስፋፊያ ስራን አከናውኗል።

 ዋዜማ ራዲዮ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች እንደሰማችው ያለፉትን ወራት ኢትዮቴሌኮም ከሁዋዊ ጋር ያለውን የፕሮጀክት ግዥ በማዝግየት ጉዳዩን እስኪለይለት ሲጠብቅ ቆይቷል። አሜሪካ የቻይናን ቴክኖሎጂ ከሚጠቀሙ ሀገራት ጋር የፀጥታና ደህንነት ትብብር አቆማለሁ የሚል ማስጠንቀቂያ ብትሰጥም ለኢትዮጵያ ትልቁ ፈተና የሆነው ሁዋዌ የጀመረው በቢሊየን ዶላር የሚተመን ፕሮጀክት መስተጓጎሉ ነበር።

ሁዋዌ ለሚያቀርባቸው ቁሳቁሶች የአሜሪካ ምርቶችን ጭምር መጠቀሙ ማዕቀብ ከተጣለበት በኋላ ስራውን ማከናወን የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር።
በማዕቀቡ የአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ ጭምር የኪሳራ አደጋ በማንጃበቡ ለጊዜውም ቢሆን ዋሽንግተን ማዕቀቡን በከፊል እንድታላላ ተገዳለች።


የኢትዮቴሌኮም የውጭ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ጨረር አክሊሉ ለዋዜማ እንደገለፁት ችግሩ እንደተፈጠረ ወደ ቻይና በማቅናት ከቻይና የቴሌኮም ኩባን ያ ሁዋዌና ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር መነጋገራቸውን አመልክተዋል።
በውይይታችን ችግሮቹን በዝርዝር አንስተን በመነጋገር በስራችን ላይ ችግር እንዳያስከትሉ የሚያስችል መንገድ ቀይሰናል ብለዋል።


በቻይናና በአሜሪካ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ረግቧል ብለው የሚያምኑት ወሮ ጨረር ጉዳዩ ያን ያህል አሳሳቢ አይደለም ሲሉ አቃለውታል።
ይሁንና አሁንም በቻይናና በአሜሪካ መካከል ያለው የንግድ ውዝግብ ተካሮ ቀጥሏል።

የንግድ ጦርነቱን ለመቀጠል እያሴረች ያለችው አሜሪካ በቻይና ምርቶች ላይ ተጨማሪ ታሪፍ ለመጣልም እዕቅድ እንዳላት አስታውቃለች።
በተለይ በአለም የቴሌኮም ዘርፍ መሪነቱን እየያዘ የመጣውን ሁዋዌ ለማዳከም አሜሪካ ብርቱ ትግል እያደረገች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በጉዳዩ ላይ በዝርዝር የተዘጋጀውን ዘገባ ከታች ካለው የድምፅ ዘገባ ያድምጡ

https://youtu.be/G47ImtcGAG0