ዋዜማ- የቀድሞ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ፌደራል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የተሰኘ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት መመስረታቸውን ዋዜማ ሰምታለች።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፓርቲ የቀድሞ የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት የመሰረቱት ፌደራል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የተሰኘ ሃገራዊ የፖለቲካ ድርጅት ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የምዝገባ ፍቃድ ለማግኘት ማሟላት ያለበትን የ10 ሺህ አባላት ፊርማ የማሰባሰብ ስራ እያጠናቀቀ መሆኑን ዋዜማ ከመስራቾቹ አረጋግጣለች።

በአዲሱ ፓርቲ ውስጥ ያሉት የቀድሞ የኦፌኮ ፓርቲ ማእከላዊ ኮሚቴ አባላትን በዝርዝር ባይገልፁም፤ የሃሳቡ አመንጪ እና ዋና መስራች ግን የኦፌኮ ከፍተኛ አመራር እንዲሁም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ደስታ ዲንቃ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የምዝገባ ፍቃድ ለማግኘት በ 7 ክልሎች ፊርማ ማሰባሰብ እንደሚያስፈልግ ፤ ነገር ሁሉንም ክልሎች ለማዳረስ የገንዘብ እና የፀጥታ ችግር ፈታኝ ሆኖብናል ያሉት መስራቾቹ፤ ፓርቲውን የመመስረት እንቅስቃሴው የተጀመረው በኦፌኮ ፓርቲ በሃላፊነት ላይ በነበሩበት ወቅት እንደሆነም አስረድተዋል።

የምስረታ ጠቅላላ ጉባኤ ከመካሄዱ በፊት ቢያንስ 500 ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ አባላት መሰብሰብ ያለባቸው ሲሆን ፤ ታህሳስ 4 ቀን፤ 2018 ዓ.ም በሆሳእና ከተማ 5 መቶ 60 አባላት የተገኙበት የመስራች ጉባኤ ለማካሄድ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፍቃድ ጠይቀው ነበር። ሆኖም፤ “የምስረታ ውይይት እንዲፈቀድ” በሚል ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የገባው ፍቃድን የሚመለከት ደብዳቤ ግልፅነት የጎደለው በመሆኑ፤ ከቦርዱ “አስተካክሉ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው እና ጉባኤውም ሳይካሄድ መቅረቱን ተናግረዋል።

ከ1 ሳምንት በፊትም በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃዲያ ዞን የመስራች ጉባኤ ለማካሄድ ለክልሉ መንግስት በተጠየቀው ፍቃድ መሰረት ፍቃድ አግኝተው በሃዲያ ልማት ማህበር አዳራሽ ስብሰባውን ለማካሄድ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም፤ የከተማ አስተዳደሩ ሃላፊዎች “ስለ ስብሰባው አናውቅም በማለታቸው ስብሰባው ተበትኗል” ብለዋል።

በምርጫ ህጉ መሰረት በምስረታ ሂደት ላይ ያለ ፓርቲ በቅድሚያ የአባላቱን ፊርማ ለምርጫ ቦርድ ማስገባት እንዳለበት ቢደነገግም፤ አስገዳጅነት እንደሌለው አስበው በመንቀሳቀሳቸው የመስራች ጉባኤው መጨናገፉን አስረድተዋል።

የኦፌኮ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ደስታ ዲንቃ በፓርቲው ውስጥ ተፈጠረ የተባለውን ሰፊ የሃሳብ ልዩነት ተከትሎ ከ1 ወር በፊት ከኦፌኮ መልቀቃቸው ይታወሳል።

በመጪው ምርጫ ላይ “መሳተፍ አለብን” እና “ራሳችንን እናግልል” በሚለው አቋም ዙሪያ በፓርቲው ውስጥ አለመግባባት መከሰቱንና ይህም ለተወሰኑ አመራር አባላት ከፓርቲው መልቀቅ ምክንያት መሆኑን ሰምተናል። በፓርቲው ውስጥ ሌሎች የሰነበቱ “አለመግባባቶች” እንደነበሩም አባላቱ ይናገራሉ። [ዋዜማ]