የኢትዮዽያን የኢኮኖሚ ዕድገት ያሞካሹ ተቋማት ሳይቀር ማሳሰቢያ እየሰጡ ነው።በስብዓዊ ልማት ረገድ ሀገሪቱ አሁንም በአለም ላይ ብዙ ደሀ የሚኖርባት ናት። ቻላቸው ታደስ በቅርቡ የወጡ ሪፖርቶችን ተመልክቷል
ከአስር ዓመታት በላይ አስር በመቶ አካባቢ ኢኮኖሚያዊ እድገት በተከታታይ እንዳስመዘገበች የሚነገርላት ኢትዮጵያ ባሁኑ ወቅት ብዙ ሳንካ የበዛበትንና በብዙ ወገኖች የተጋነነ እንደሆነ የሚነገርለትን የመጀመሪያውን የአምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዷን አጠናቃ ወደ ሁለተኛው ለመሸጋገር እየተዘጋጀች እንደሆነ ይታወቃል። መንግስትም በእነዚህ ተከታታይ እቅዶች ሀገሪቱን እኤአ በ2025 ዓመተ ምህረት መካከለኛ ገቢ ላይ አደርሳታለሁ ይላል።
ሆኖም ሀገሪቱ አሁንም ጤናን፣ ትምህርትን፣ የነፍስ ወከፍ ገቢን፣ እድሜ ርዝማኔን፣ ድህነት ቅነሳን፣ ስራ ፈጠራንና ሌሎችንም ማህበራዊ መሻሻሎችን በሚያቅፈው ሰብዓዊ ልማት እድገት ረገድ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንዳለች ብቻ ሳይሆን ወደፊትም በርካታ ፈተናዎችም እንደሚጠብቋት መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ የሰብዓዊ ልማት ሁኔታዋም ስለ ሀገሪቱ ፈጣን ኢኮኖሚ እድገት ነጋ ጠባ ለሚለፍፈው የኢሕአዴግ መራሹ መንግስት ከባድ ፈተና ሆኖበታል።
ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የተባበሩት መንግስታት ልማት ድርጅትና አለማቀፉ የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ደርጅት በጋራ የሁለት ሺህ አስራ አምስት ዓመተ ምህረት የአፍሪካ አህጉርን ኢኮኖሚያዊ ገፅታ የሚያሳይ ሪፖርት አውጥተው ነበር።
የኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ግምገማ ሪፖርቱ ከሚሊኒዬሙ መባቻ ጀምሮ እስካሁን ያለውን የአህጉሪቱን የአስራ አምስት ዓመታት አፈፃፀም የሚዳሥስ ነው። ሪፖርቱ የሰብዓዊ ልማትንም የዳሰሰ ሲሆን አሕጉሪቷም ወደ መካከለኛ ሰብዓዊ ልማት እድገት ምዕራፍ ለመግባት በመንደርደር ላይ መሆኗን አብስሯል።
እንደ ሪፖርቱ ግኝት ከሆነ በአፍሪካ የሚታየው የእኩልነት ክፍተት ጎልቶ የሚታየው ከነፍስ ወከፍ ገቢ ሳይሆን በትምህርትና ጤና ረገድ መሆኑ በሰብዓዊ ልማት ከበለፀጉት ሌሎች ሀገሮች ለየት ያደርገዋል። ሆኖም ከፈረንጆቹ ሁለት ሺህ ዓመተ ምህረት ጀምሮ ከሌሎቹ የዓለም አካባቢዎች ጋር ሲነፃፀር አፍሪካውያን ሀገሮች በሁሉም ሰብዓዊ ልማት መስኮች አመርቂ ውጤት አስመዝግበዋል ይላል ሪፖርቱ። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በሁለት ሺህ አስራ አራት ዓመተ ምህረት ብቻ ከሀምሳ ሁለቱ ሀገሮች አስራ ሰባቱ ከፍተኛና መካከለኛ ሰብዓዊ ልማት ለማስመዝገብ እንደቻሉም ሪፖርቱ ያስረዳል።
ኢትዮጵያ ከ1990ዎቹ ጀምሮ ፈጣን የሰብዓዊ ልማት እድገት ካሳዩት አራት የምሰራቅ አፍሪካ ሀገሮች መካከል አንዷ እንደሆነች ሪፖርቱ መስክሮላታል። ያም ሆኖ ባለፈው አስርት ዓመት ያስመዘገበችው የሰብዓዊ ልማት የእድገት ደረጃዋ በተናጥል ሳይሆን በንፅፅር ሲታይ ግን ዝቅተኛ እንደሆነ ሪፖርቱ ያሰምርበታል። የተባበሩት መንግስታት ልማት ፕሮግራም ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ ያወጣው ሁለተኛው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ልማት ሪፖርት እንደሚያሳየው ሀገሪቱ በሰብዓዊ ልማት እድገት ጠቋሚ ከ 187 ሀገሮች ውስጥ 173ኛ ደረጃ ይዛ ትገኛለች። ለዚህም ዝቅተኛ ደረጃ ከክልል ክልል የሚስተዋለው ሰፊ ልዩነት በተለይም በታዳጊ ክልሎች የሚታየው በጣም ዝቅተኛ ሰብዓዊ ልማት ተጠቃሽ እንደሆነ ተጠቁሟል።
የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ብዙ ቢባልለትም ኢኮኖሚ እድገቱ የተወሰኑ የህብረተስብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረገ እንጂ ሁሉን ዓቀፍና አካታች እንዳለሆነ ባለፈው ዓመት ላይ የተባበሩት መንግስታት ልማት ፕሮግራም በኢትዮጵያ ላይ ያወጣው የሰብዓዊ ልማት ሪፖርት ክፉኛ መተቸቱ ይታወሳል። ሪፖርቱ አካታችና ሁሉን ዓቀፍ እድገት ለዘላቂ ሰብዓዊ ልማት ባለው አስፈላጊነት ላይ እንዲያተኩር የተደረገውም በዚሁ ምክንያት መሆኑን የተመድ ልማት ፕሮግራም ኣስታውቆ ነበር።
በእርግጥም የአምናው የተመድ ልማት ፕሮግራም ሪፖርትም ሆነ የዘንድሮው ኣህጉራዊ ሪፖርት የሰብዓዊ ልማት ዋነኛ አላባ የሆነው የሰዎች እድሜ ርዝመት በሁለቱም ፆታዎች መሻሻል ማሳየቱን ይመሰክራሉ። ሀገሪቱም በበርካታ ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በሚታገዘውና በአንድ ለአምስት አደረጃጀት የተደራጀው የጤናው ዘርፍ በሚለኒዬሙ ልማት ግቦች የተቀመጠውን የህፃናት ሞት ቅነሳን በማሳካት ረገድም ሆነ በሌሎች የጤና አገልግሎቶች ተደራሽነትና በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እመርታ እንዳስመዘገብች ይገልፃሉ። ሆኖም ግን ባለፉት አስር ዓመታት በደንብ የሰለጠኑ ጤና ባለሙያዎች እጥረት፣ የእናቶች ሞትና የህፃናት ያልተመጣጠነ አመጋገብና የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆን ቀጥሏል ይላሉ ሪፖርቶቹ።
በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እድገት ከፍተኛ እመርታ ቢመዘገብም የከፍተኛ ሁለተኛ ትምህርት ደረጃ ቅበላና ተደራሸነት ግን በገጠሩና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አካባቢ ኣሁንም ዝቅተኛ እንደሆነና የፆታ አለመመጣጠንም ቢሆን መቀነስ የጀመረው ከአምስት ዓመታት ወዲህ መሆኑንም ይጠቁማሉ። በሃገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የሚታየው የሰብዓዊ ልማት እድገት አለመመጣጠንም አንዱ ዋነኛ ምክንያት በትምህርት አቅርቦትና ጥራት ረገድ ያለው ልዩነት መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ። ዘ ጋርዲያን የተባለው ታዋቂው የብሪታኒያ ጋዜጣም በቅርቡ የሀገሪቱ የትምህርት ጥራት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን መዘገቡ ይታወሳል።
መንግስትና የተመድ ልማት ድርጅቱ የተፋጠጡበት የኣምናው የሰብዓዊ ልማት ሪፖርት ከድህነት ወለል በታች ያለው ህዝብ እንደ ኣውሮፓውያን አቆጣጠር በ2004 ከነበረበት ስላሳ ስምንት በመቶ በሁለት ሺህ አስራ ሶስት ዓመተ ምህረት ወደ ሃያ ስድስት በመቶ ዝቅ ማድረግ እንደተቻል ቢመሰክርም ሀገሪቱ አሁንም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ድሃ የሚኖርባት ከመሆን እንዳልተላቀቀች ገልፆ ነበር። ባለፉት አስር ዓመታት የድህነት መጠንና የድህነት ተጋላጭነት ጭማሪ ከማሳየቱም በላይ በፍፁም የከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኘውን ሀያ አምስት ሚሊዮን ያህል ህዝብ ቁጥር መቀነስ እንዳልቻልችም ያስረዳል። ለዚህም አንዱ ተጠቃሽ ምክንያት የህዝብ ብዛት መጨመር መሆኑ ተገልጿል።
መንግስት ሀገሪቱን በ2025 መካከለኛ ገቢ ላይ ለማድረስ ላለፉት አስራ ኣምስት ዓመታት ያልተማከለ ውሳኔ አሰጣጥን ጨምሮ አዳዲስ ተቋማዊ አደረጃጀቶችንና ድሃ ተኮር የሆኑ ፖሊሲዎችን ነድፎ ተግባራዊ ማድረጉን ሪፖርቶቹ ያሞካሻሉ። ሀገሪቱም ለአስር ዓመት ያህል በሰብዓዊ ልማት ለተመዘገበው መሻሻልም ዓይነተኛ ሚና የተጫወተው መንግስት ለአገልግሎት ዘርፉ የሰጠው ትኩረት እንደሆነም ይጠቀሳሉ። ሆኖም ግን የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ በተለይም በሰብዓዊ ልማት ውስጥ ያለው ሚና አነስተኛነት እንዲሁም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ አሁንም በግብርና ላይ ጥገኛ በመሆኑ የሰብዓዊ ልማቱ ፈተና እንደበዛበት የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።
የፋይናንስ ተቋማት እጥረት፣ በፋይናንስ ተቋማት የሚገለገሉ ዜጎች ብዛት አንስተኛ መሆንና አበረታች የቁጠባ ፖሊሲ አለመኖር በሰብዓዊ ልማቱ ላይ ጋሬጣ ፈጥረዋል። የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው የመንግስታዊ ኢንቨስትመንት ድርሻ በከፍተኛነቱ በዓለም ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲሆን የግል ባለሃብቶች ኢንቨስትመንት ድርሻ ግን በዝቅተኛነቱ ከዓለም በስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ለዚህም ምክንያቱ የመንግስት የመሬትና ፋይናንስ ፖሊሲዎች ጥብቅ መሆን ሀገሪቱን ለግል ቢዝነስ የማትመች ሰላደረጓት እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።
መንግስት የግልፅነትና ተጠያቂነት ችግር ስላለበትም በያዝነው ዓመት መባቻ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት በዓለም ባንክና በሌሎች እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች የሚታገዘውንና የሰብዓዊ ልማት ዋነኛ ምሰሶ ለሆነው የመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ማጎልበት ፕሮግራምን (Basic Services Promotion program) የተመደበውን ባጀት በጋምቤላ ክልል ሰብዓዊ መብቶችን ለሚጨፈልቀው ኣስገዳጅ ሰፈራ (resettlement) ፕሮግራም ማስፈፀሚያ አውሎታል የሚል ክስ ሲቀርብበት እንደነበር ይታወሳል። በዚህም ሳቢያ የዓለም ባንክ ክፉኛ ሲተች ቆይቷል። እንደሚታወቀው የመንግስት የሰብዓዊ መብት ይዞታ አሳሳቢ ስለመሆኑ በርካታ አለም አቀፍ ስብአዊ ተመጋቾችና ታዛቢዎቸ ሁሌም የሚናገሩት ነው። የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ደግሞ ዋነኛ የሰብዊ ልማት ምሰሶ መሆኑ ይታወቃል።
መንግስት ድህነት-ተኮር ልማት መከተሉ ቢነገርለትም በመጀመሪያው የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ (Growth and Transformation Plan- I) በታላላቆቹ ጊቤ ሶስት ሃይል ማመንጫና የታላቁ ህዳሴ ግድብ (Grand Renaissance Dam)፣ ስኳር ልማትና ባቡር ሃዲድ ዝርጋታን ጨምሮ በርካታ ግዙፍ ፕሮጄክቶችን ስለጀመረ የገንዘብ እጥረት እያጋጠመው እንደሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ይገልፃሉ። ፕሮጄክቶቹ የሚጠይቁት ከፍተኛ ወጭም ለሰብዓዊ ልማት የሚሰጠውን ትኩረት መቀነሳቸው የማይቀር ነው። እስካሁንም በመተግበር ላይ ያለው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከ77 ቢሊዮን ዶላር በላየ እንደሚፈጅ ተገምቷል።
በጥቅሉ ሲታይ ኢትዮጵያ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ያስመዘገበች ሆና ሳለ በሰብዓዊ ልማት እድገት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ለመገኘቷ ዋናኛው ምክንያት እድገቱ ሰብዓዊ ልማትን ያላማከለ በመሆኑ እንደሆነ የሚያከራክር አይደለም። ሰብዓዊ ልማትን ያላማከለ ዕድገት ደግሞ ዘላቂነት ሊኖረው እንደማይችል ከታመነበት ቆየታል። በዚህም ሳቢያ በበርካታ ሰብዓዊ ልማት ዘርፎች የሚታዩት መሻሻሎች በአብዛኛው በያዝነው የፈረንጆች ዓመት የሚጠናቀቁትን የሚሊኒየም ልማት ግቦች ለማሳካት የሚያስችሉ አልሆኑም።
ስለሆነም ዓለም ዓቀፍ ተቋማት “አንገብጋቢ የሰብዓዊ ልማት ጉዳዮች” (daunting human development issues) በማለት የሚገልጿቸውን ችግሮች ለመቅረፍ መንግስት በመጭዎቹ ዓመታት የጤናና ትምህርት ጥራትና ቀጣይነት ችግሮችን በሚቀረፉ፣ ስራ አጥነትን በሚቀንሱ፣ በልማት እቅድ የዜጎችን ተሳታፊነት በሚጨምሩ፣ ድህንትን በሚቀንሱና የምግብ ዋስትናን በሚያረጋግጡ ፖሊሲዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንዲያደርግ የዓለም ዓቀፍ ተቋማቱ ሪፖርቶች ያሳስባሉ። ሀገሪቱ የሰብዓዊ እድገት ደረጃዋን ለማሻሻል ሰብዓዊ ልማትን ያማከል ሁሉን ዓቀፍ የሆነ የእድገትና ልማት ፖሊሲ መከተል እንዳለባትም ዓለም ዓቀፍ ተቋማቶቹ አፅናኦት ሰጥተው በመከራከር ላይ ናቸው።
ሆኖም መንግስት ነባር ፖሊሲዎቹንና የትኩረት አቅጣጫዎቹን በመመርመር በሰብዓዊ ልማት ረገድ የቀረቡለትን ማሳሰቢያዎች ተግባራዊ ስለማድረጉ ወደፊት ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባር ላይ ሲውል የሚታይ ይሆናል።