ዋዜማ ራዲዮ – ከሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ ሀይል ለማመንጨት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዋዜማ ራዲዮ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች አረጋግጣለች።


እነዚህ ምንጮች እንደነገሩን ሰኔ 12 ቀን 2013 አ.ም ሁለተኛ ዙር የውሀ ሙሌቱን ያጠናቀቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአንድ የሀይል ማመንጫ ተርባይን ሀይል እንዲያመነጭ በብርቱ እየተሰራ ነው። ቀሪ ስራዎችና የሙከራ ጊዜን ጨምሮ ሀይል ማመንጨቱ እስከ ሶስት ወራት ሊወስድ እንደሚችል ባለሙያዎቹ ይገምታሉ።


አሁን በግድቡ የተያዘው ውሀ በሁለት ሀይል ማመንጫ ተርባይኖች የኤሌክትሪክ ሀይልን ለማመንጨት የሚያስችለው እንደሆነ መገለጹ ይታወሳል።


በህዳሴው ግድብ ግንባታ ስፍራ የሀይል ማመንጫ ተርባይን እና ጀነሬተር ተከላዎች እየተከናወኑ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።
በመጀመርያው የሀይል ማመንጫ ተርባይን በስኬት የኤሌክትሪክ ሀይልን የማመንጨቱ ስራ ከተከናወነ የተቀሩት የሀይል ማመንጫዎችን ወደ ስራ ማስገባትን ቀላል እንደሚያደርገው ባለሙያዎች ያብራራሉ።


 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚኖሩት የሀይል ማመንጫ ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይልን የማመንጨት አቅም አላቸው። ይህ ማለት ግን የመጀመርያው ሀይል ማመንጫ 375 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክን ያመነጫል ማለት እንዳልሆነ ምንጫችን ያስረዳሉ።


የግድቡ የሀይል ማመንጫዎች በሙሉ አቅማቸው የኤሌክትሪክ ሀይልን የሚያመነጩት የግድቡ ቁመት ከባህር ጠላል በላይ 640 ሜትር ላይ ሲደርስና ግድቡ በመሉ አቅሙ ውሀ ሲይዝ ነው።


የመጀመርያው ሀይል ማመንጫም የህዳሴው ግድብ በደረሰበት ቁመትና በያዘው ወሀ ልክ ሀይልን እንደሚያመነጭ ይጠበቃል። የመጀመርያውን የሀይል ማመንጫ ተርባይንን ስራ ማስጀመር እጅግ ውስብስብ ስራዎችና ጥንቃቄ የተሞላበትን ሂደት የሚጠይቅ እንደሆነ የነገሩን ባለሙያዎች ይህም አጠቃላይ ቀሪ የግድቡን ስራ ለማጠናቀቅ ልምድ የሚወሰድበት ምዕራፍ ነው ነው ብለውናል።


ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ በአዲሱ አመት 2014 አ.ም መግቢያ ላይ ከህዳሴው ግድብ ኤሌክትሪክን ለማመንጨት መርሀ ግብር የነበረ ቢሆንም በአንዳንድ የማጠናቀቂያ ስራዎች መዘግየት ሳቢያ የሳምንታት መዘግየት ተከስቷል።


በከፍተኛ አለማቀፍ ጫና ውስጥ ሆና ሁለተኛውን ዙር የታላቁ ህዳሴ ግድብን ውሀ የሞላችው ኢትዮጵያ ግድቡን በፍጥነት ወደ ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጨት ማስገባቷ ዲፕሎማሲያዊ ድል ተደርጎ የሚታይ ነው ። [ዋዜማ ራዲዮ]