ዋዜማ ራዲዮ – ያለፉትን አራት ወራት በዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ ግዛቶች በመታየት ላይ ያለው “ፌስታሌን” (እያዩ ፈንገስ) የተሰኘ የአንድ ስው ሙሉ ተውኔት በአዳዲስ ከተሞችና በአንዳንድ አካባቢዎች በድጋሚ ለማሳየት መርሀ ግብር መዘርጋቱን አዘጋጆቹ አመለከቱ።
በላስ ቬጋስ በሲያትል በአትላንታ በዳላስ እንዲሁም በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢዎች በድጋሚ የሚታይ ሲሆን በሂዩስተን፣ ኦስትንና ቦስተን ከተሞችም መርሀግብር ተዘጋጅቷል። ምንም እንኳን የኢትዮጵያውያን ቁጥር በአንዳንድ ከተሞች አነስተኛ ቢሆንም ተውኔት የመመልከት ልዩ ፍቅር ላላቸው ለመድረስ መርሀግብር መዘጋጀቱን የቡድኑ አስተባባሪ አቶ በቀለ አማረ ለዋዜማ ገልፀዋል።
ባለፉት ወራት በርካታ ኢትዮጵያውያን ተውኔቱን የተመለከቱት ሲሆን በሲያትል ከተማ በነበረ መጥፎ የአየር ሁኔታ መመልከት ላልቻሉ በዚህ ሳምንት በድጋሚ ይታያል። በደቡባዊ የአሜሪካ ግዛቶች የሚደረገው ጉዞ ከተጠናቀቀ በኋላ በሰሜን ግዛቶች የተወሰኑ ከተሞች መርሀግብር እየተዘጋጀ መሆኑን አቶ በቀለ ተናግረዋል።
ቀጣዩ የቡድኑ እቅድ በካናዳ አጭር ቆይታ በማድረግ ከአጭር እረፍት በኋላ የአውሮፓና ሌሎች አካባቢዎችን ጉዞ ይጀምራል። ደራሲው በረከት በላይነህና ተዋናይ ግሩም ዘነበ በአሜሪካ የሚያደረጉት የተጨማሪ ሳምንታት ቆይታ ከየአካባቢው በሚቀርብላቸው የተመልካች የድጋሚ-ማየት ጥያቄ ሳቢያ በመሆኑ ስራቸውን በጋለ መንፈስ ለመቀጠል ተዘጋጅተናል ብለዋል። ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ በአዲስ ዙር ለሚያደርጉት ትርኢት እንደሚሰናዱ ተናግረዋል።
“እያዩ ፈንገስ” ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከሰባ ሺህ በላይ ተመልካች የታደመበት በሳቅና ሽሙጥ የሚመደብ ወቅታዊ የሀገሪቱን ህፀፅ የሚነቅስ ተውኔት ነው። “በሄድንባቸው ከተሞች ሁሉ በተደረገልን አቀባበል ተደስተናል” የሚሉት የተውኔቱ ፀሀፊና ተዋናይ በቀሪዎቹ ሳምንታት በተቻለ አቅም አዳዲስ ተመልካቾችን ለመድረስ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።