ዋዜማ- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በመጋቢት 02/2015 ዓ.ም. ባደረገው 2ኛ መደበኛ ጉባዔው ያቋቋመው ግብረ ኃይል ያዘጋጀውን የጥናት ሰነድ ዛሬ ሚያዚያ 28/ 2015 ይፋ እንደሚያደርግ የዋዜማ የመረጃ ምንጮች ጠቁመዋል።
ኢዜማ ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ መሥራቱ በትግል መስመሩ ፣በድጋፍ መሠረቱ እና በታአማኒነቱ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ የጥናቱ ተቀዳሚ የትከረት አቅጣጫ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ፓርቲው በተጓዘበት የትብብር መንፈስ የተነሳ ለሀገር ያበረከተው ፋይዳ በኮሚቴው ሰነድ ለይ ተመላክቷል።
በመሆኑም ከብልጽግና መራሹ መንግሥት ጋር እስካሁን የመጣበትን ተቀራርቦ የመስራት ልምድ ለማስቀጠል ወይም በአዲስ ሥርነቀል የትግል መስመር ለመሰለፍ የሚያስችለውን ውሳኔ በግብረ ኃይሉ አማካኝነት ለአባላቱ እና ለደጋፊዎቹ ነገ ሚያዚያ 28/ 2015 ያስውቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ኣኢዜማ ሀገሪቱ ያለችበትን ስሱ የፖለቲካ ሁኔታ በመንገንዘብ ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ መስራት የተሻለ መሆኑን አምኖ የካቢኔ ስልጣን እስከመጋራት የደረሰ ቅርርብ ከመንግስት ጋር ፈጥሯል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ስልጣን በያዙ ማግስት ወደ አሜሪካ በተጓዙበት ወቅት የግንቦት ሰባት አመራር ከነበሩት ብርሃኑ ነጋና ጓዶቻቸው ጋር በዋሽንግተን ዲሲ በተደረገ ምስጢራዊ ውይይት ግንቦት ሰባት ወደ ሀገር ቤት ተመልሷል። አስከትሎም ኢዜማ ሲመሰረት ከመንግስት ጋር ትብብሩን የበለጠ አጠናክሯል።
ኢዜማ በምርጫ የፓርላማ ወንበር ባይቀናውም በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ብልፅግና ፓርቲ ፈቃደኝነት ለተቃዋሚዎች ከተቸሩ ያካቢኔ ወንበሮች አንዱን ወስዷል።
ይህ ኢዜማና የብልፅግና ቅርርብ ፓርቲው ቆሜለታለሁ ከሚለው አላማ ጋር አብሮ አለመሄዱ በተለይ በሀገሪቱ ስር የሰደደውን የመብት ረገጣና ሞት በተመለከተ የጠራ አቋም አለመያዙ በአባላቱ መካከል ብርቱ ጥያቄ ሲያስነሳ ቆይቷል።
ፓርቲው በህዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ከመሸርሸሩም በላይ በአባላቱ መካከል እየበረታ የመጣው ልዩነት የፓርቲውን ህልውና አደጋ ውስጥ ጥሎታል።
አንዳንድ አባላትና አመራሮቹም በተመሳሳይ ቅሬታ ፓርቲውን ለቀው እስከመውጣት መድረሳቸው ይታወቃል።
ኢዜማ ያቋቋመው ግብረኀይል ዛሬ የሚያቀርበው ምክረ ሀሳብ የፓርቲውን ቀጣይ ህልውና የሚወስን ይሆናል። [ዋዜማ]