ዋዜማ ራዲዮ- የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሐሙስ ምሽት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት የአፍሪቃ ሀገራትን Africa Growth Opportunity Act (Agoa) የቀረጥና ታሪፍ ነፃ መብት መሰረዛቸውን ይፋ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ በትግራዩ ጦርነት ሳቢያ ከንግድ ፕሮግራሙ የተሰረዘች ሲሆን ማሊና ጊኒም ከንግድ መብት ተጠቃሚነቱ ተሰርዘዋል።
ኢትዮጵያ የተሰረዘችው ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ተፈፅሟል ለተባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ከአማፅያን ጋር ድርድር እንድትቀመጥ ለማስገደድ ያለመ መሆኑንና ሁለት ወራት የማሰቢያ ጊዜ ገደብ ተሰጥቷት ነበረ።
የኢትዮጵያ መንግስት ለአሜሪካ ጫና ባለመንበርከኩ እገዳው ተግባራዊ እንዲሆን ፕሬዝዳንት ባይደን በፊርማቸው አፅድቀውታል። ከፈረንጆቹ አዲስ አመት ጀምሮም ውሳኔው ይፀናል።
ለሀያ አመታት አልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ ወደ አሜሪካ በመላክ ተጠቃሚ የነበረችው ኢትዮጵያ በየአመቱ አንድ መቶ ሚሊየን ዶላር ያህል ታገኝ የነበረ ሲሆን በርካታ ዜጎችም በዘርፉ ተቀጥረው በመስራት የስራ ዕድል አግኝተው ቆይተዋል።
የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያን ከንግድ ፕሮግራሙ እንዳይሰርዝ ጥቂት የኮንግረስ አባላት ለፕሬዝዳንት ባይደን ጥያቄ ቢያቀርቡም ፕሬዝዳንቱ ጥያቄውን ቸል ብለው ኢትዮጵያን ማሊንና ጊኒን በመሰረዙ ፀንተዋል።
አጎዋ የቀረጥና የታሪፍ መብት ለ38 የአፍሪቃ ሀገራት የተሰጠ ዕድል ሲሆን እንዲቀጥል ካልተወሰነ ከሶስት ዓመት በኋላ ሙሉ ፕሮግራሙ ይጠናቀቃል።
አሁን በኢትዮጵያ ላይ የተወሰደው እርምጃ የአልባሳትና ጨርቃጨርቅ እንደስትሪው ባለፉት አመታት ያሳየውን ዕድገት የሚገታና የባለሀብቶችን እንቅስቃሴ የሚገድብ ነው።
በአንፃሩ ቻይና 300 ቢሊየን ዶላር ለሚገመት ንግድ ለአፍሪቃ ሀገራት በሯን ክፍት ለማድረግ በቅርቡ መወሰኗ ለአንዳንድ ሀገራት ተስፋ ሰጪ ሆኖ ታይቷል። [ዋዜማ ራዲዮ]