ዋዜማ ራዲዮ- የዓባይ (ናይል) ተፋሰስ ሀገሮች የትብብር ማዕቀፍ ካሉት ሶስት የቴክኒክና የፕሮጀክት ቢሮዎች መካከል አንዱ የምስራቅ ናይል የቴክኒክ ቀጠናዊ ጽህፈት ቤት (ENTRO) በኢትዮጵያ ይገኛል። ይህ ጽህፈት ቤት የኤሌክትሪክ ሀይል መሸጥን ጨምሮ በተፋሰሱ ሀገራት በትብብር የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን ሲመራና ሲያስተባብር ቆይቷል።
በሱዳን የውሀ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ ከአባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ በከፍተኛ ሀላፊነቶች ላይ ሲሰሩ የነበሩት ሳሊህ ሀማድ ሀሚድ በአዲስ አበባ መቀመጫውን ያደረገውና ከናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ሶስት ተቋማት አንዱ የሆነውን የምስራቅ ናይል የቴክኒክ ቀጠናዊ ጽህፈት ቤትን (ENTRO) ከጥር ወር ጀምሮ በዋና ዳይሬክተርነት መምራት ጀምረዋል።እኚህ ሰው ጽህፈት ቤቱን ከስድስት አመት በላይ ሲመሩ ከነበሩትና የሀላፊነት ጊዜያቸውን ካጠናቀቁት ኢትዮጵያዊው አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ ነው የተረከቡት።በሱዳን የውሀ ተቋማት ውስጥ በተለይ ከአባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ በከፍተኛ ሀላፊነት ከመስራታቸውም ባለፈ ሱዳንን ወክለው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙርያ ሲደራደሩ የነበሩ ናቸው።በአሜሪካ ዋሽንግተን በተደረገው ድርድር እንዲሁም አዲስ አበባ የምስራቅ ናይል የቴክኒክ ቀጠናዊ ጽህፈት ቤትን ተረክበው መምራት እስኪጀምሩም ድረስ በህዳሴው ግድብ ድርድር ላይ ሱዳንን ወክለው ተሳትፈዋል።
ሱዳናዊው ሳሊህ ሀማድ የሚመሩት የምስራቅ ናይል የቴክኒክ ቀጠናዊ ጽህፈት ቤት የተቋቋመው በፈረንጆቹ 2002 ሲሆን ግብጽ ሱዳንና ኢትዮጵያ በጋራ ያቋቋመት ተቋም ነው።ግብጽ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማእቀፍ በተፋሰሱ ሀገራት እንደ አውሮፓውያኑ በ2010 ሲፈረም አኩርፋ ለቃ ወጥታለች። በወቅቱ ሱዳንም ከግብጽ ጋር ከቀጠናዊ የቴክኒክ ጽህፈት ቤቱ አባልነት የለቀቀች ቢሆንም በፈረንጆቹ 2013 ወደ አባልነቷ ተመልሳለች።ከዚያ ጊዜ በሁዋላም የቴክኒክ ጽህፈት ቤቱን አዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ተጨምራበት ኢትዮጵያና ሱዳን ናቸው በባለቤትነት የያዙት። ጽህፈት ቤቱ በአባይ ወንዝ ላይ በአባል ሀገራቱ በጋራ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን ይቀርጻል ፤ ያስተባብራል ፤ ይተገብራል። የኢትዮ ሱዳን የሀይል ትስስር ፕሮጀክት ከዚህ ጽህፈት ቤት ስራዎች የሚጠቀስ ነው።
የጽህፈት ቤቱ መደበኛ ወጪ የሚሸፈነው ኢትዮጵያ ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን እያንዳንዳቸው በየአመቱ ማዋጣት ባለባቸው 333 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በጥቅሉ አንድ ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ነው። የፕሮጀክት ወጭዎች ደግሞ አለም ባንክን ጨምሮ በተለያዩ አለማቀፍ ተቋማት የገንዘብ አቅርቦት ይሸፈናል።
አሁን ተቀማጭነቱ አዲስ አበባ ላይ የሆነው የምስራቅ ናይል የቴክኒክ ቀጠናዊ ጽህፈት ቤትን አመታዊ መዋጮ እየከፈለች ያለችው ኢትዮጵያ ብቻ ናት። ሱዳን አመታዊ ክፍያን ከከፈለች ሶስት አመት እንዳለፋት ከውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ምንጮቻችን ሰምተናል። ደቡብ ሱዳን ደግሞ የፖለቲካ ችግር ውስጥ ከገባች ጀምሮ ከፍላ አታውቅም። እናም የቴክኒክ ጽህፈት ቤቱን የደሞዝን ጨምሮ የተለያዩ ክፍያዎችን በውጭ ምንዛሬ ጭምር እየከፈለች ያለችው ኢትዮጵያ ነች። የቢሮው ሐላፊ ሳሊህ ሀማድም በወር በውጭ ምንዛሬ ተቀይሮ እስከ 400 ሺህ ብር የሚከፈላቸውም ከኢትዮጵያ ካዝና ነው። ይህም በኢትዮጵያ የውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሰራተኞች ዘንድም ጥያቄ እየተነሳበት ያለ ጉዳይ ሆኗል።
በዚህ ሳምንት የአባል ሀገራት ሚንስትሮቹ ማለትም ኢትዮጵያ ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን አዲስ አበባ ላይ ስብሰባ አድርገው ነበር። ተቋሙ የገጠመው ችግርም ተነስቶ ውይይት ተደርጎበት ነበር። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ያለባቸውን የመዋጮ ዕዳ በሶስት ወራት ጊዜ ለመክፈል ቃል ገብተዋል። ሀገራቱ መዋጮውን በቃላቸው መሰረት የማይከፍሉ ከሆነ የድርጅቱ ህልውና ዳግም በኢትዮጵያ እጅ ላይ ይወድቃል። [ዋዜማ ራዲዮ]