ዋዜማ ሬዲዮ- በኢትዮጵያ ስርጭቱ በፍጥነት እየጨመረ በመጣው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተይዘው በፅኑ ለሚታመሙ ሰዎች የሚያገለግለው ቬንትሌተር (የትንፋሽ ማገዣ ማሽን) ከፍተኛ እጥረት ማጋጠሙንና ልውጥ የኮሮና ቫይረስ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን የመንግስት የጤና ዘርፍ ሀላፊዎች ለዋዜማ ተናግረዋል።፡፡
በሀገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በፈጣን እና በአስጊ ሁኔታ እየተሰራጨ ይገኛል፡፡ በዚህም ባለፉት 60 ቀናት ብቻ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 57 ሺህ 071 ደርሷል፡፡ ይህም ቁጥር እስካሁን ወረርሽኙ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ከተመዘገበው አጠቃላይ ቁጥር ውስጥ 16 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል፡፡
በፍጥነት እያሻቀበ ያለው የታማሚ ቁጥር ኢትዮጵያ ከአፍሪካ 4ኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ ማድረጉን ዋዜማ ሬዲዮ ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ያገኘችው መረጃ ያሳያል፡፡
አሁን በሀገሪቱ እየተስፋፋ ያለው የኮቪድ 19 ዴልታ ቫይረስ ሲሆን ይህም ቀድመው ሲታዩ ከነበሩት አልፋ እና ቤታ ቫይረሶች ስርጭቱ እጥፍ እንደሆነም ኢንስቲቲውቱ በሳምንታዊ ሪፖርቱ አካቷል፡፡
ከዚህ በፊት የታማሚዎች ቁጥር በተወሰነ መልኩ መጨመሩ ከኦክስጅን አምራቾችች ስራ ማቋረጥ ጋር ተደምሮ ሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የኦክስጅን እጥረት አጋጥሟት እንደነበር ይታወሳል፡፡
አሁን ላይ አስፈላጊ ጥሬ እቃዎችን ያለቀረጥ ከማስገባት ጀምሮ በተቻለው አቅም ሁሉ በቀን 3ሺህ ኪውቢክ ሜትር ኦክስጅን እየተመረተ መሆኑን የኮቪድ 19 መከላከያ ግብረ ሀይል ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር መብራቱ ማሴቦ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡት ታሚዎች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ በመምጣቱ ከኦክስጅን ባለፈ የትንፋሽ ማገዣ ማሽን ወይንም ቬንትሌተር እጥረት እንዳለ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በትንሹ 6ሺህ የትንፋሽ አጋዥ ማሽን ወይንም ቬንትሌተር ያስፈልጋታል ያሉት ዶ/ር መብራቱ አሁነን ላይ ስራ ላይ ያለው 1ሺህ 2 መቶ ብቻ መሆኑን እና ተጨማሪ 2 መቶ ቬንትሌተር በመተከል ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዚህም ምክኒያት ፅኑ ታማሚ ሆነው እና የማሽኑ እገዛ እያስፈለጋቸው ነገር ግን ወረፋ የሚጠብቁ ሰዎችሰዎች ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን ዶ/ር መብራቱ አብራርተዋል።
የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲውት ሳምንታዊ ሪፖርት ደግሞ የታየው እጥረት የቬንትሌተር ብቻ ሳይሆን የፅኑ ህሙማን አልጋም ጭምር መሆኑን አሳውቋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2013 ዓም ብቻ 5.7 ቢሊየን ብር በህክምና መሳሪዎች ግዢ ላይ አውላለች፡፡ ይህም ለለዘርፉ በታሪክ ተመድቦ የማያውቅ የገንዘብ መጠን መሆኑን ዶ/ር መብራቱ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ [ዋዜማ ሬዲዮ]