ዋዜማ ራዲዮ- በቅርብ ወራት የተባባሰውን የአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካዊ ትኩሳት ተከትሎ ሱዳንና ኢትዮጵያ የጋራ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመራቸውን የሱዳን ወታደራዊ ምንጮች አስታወቁ።
የቀድሞ የሱዳን ከፍተኛ ወታደራዊ ሹም ስሞኑን በአዲስ አበባ ባደረጉት ቆይታ ወቅት ለዋዜማ ዘጋቢ እንደነገሩት ሁለቱ ሀገሮች የጋራ ድንበራቸው ላይ የተቀናጀ ወታደራዊ እንቅስቃሴ የጀመሩ ሲሆን የአየር ቅኝትና የጋራ ወታደራዊ ልምምድን ያካተተ ስምምነት በሁለቱ ሀገሮች ተደርሶ ወደ ተግባር ተገብቷል።
የሱዳን ወታደሮች ቀደም ባሉት ወራት ጀምሮ በድንበር አካባቢ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የኢትዮጵያ አየር ሀይልና እግረኛ ሀይል የሱዳን ድንበርን ዘልቆ እንቅስቃሴ ማድረጉን ተናግረዋል።
የወታደራዊ እንቅስቃሴው አላማ የድንበር ላይ የፀጥታ ችግሮችንና የኢትዮጵያና የሱዳን የጋራ ጠላቶችን መመከት ነው ያሉት ወታደራዊ መኮንኑ ስለዝርዝር ተልዕኮው ከመናገር ተቆጥበዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የሱዳን ኤምባሲ ምንጮች በበኩላቸው ወታደራዊ ትብብሩ የቆየ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አዳዲስ አካባቢያዊ ክስተቶችን በመንተራስ ትብብሩን ማጠናከር እንዳስፈለገ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ ጥቃት እንዳይደርስ ከመመከት ጀምሮ በስም ያልተጠቀሱ የጋራ ጠላቶችን መመከት የትብብሩ አላማ መሆኑን ያሰምሩበታል።
ሱዳን በቅርቡ ከግብፅና ከኤርትራ ጋር ወደ ወታደራዊ ፍጥጫ ያደገ ውዝግብ ውስጥ የገባች ሲሆን ከኢትዮጵያ ጋር በማበር በድንበር አካባቢ ሰፊ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ስታደርግ ስንብታለች።
ኢትዮጵያም ሆነች ሱዳን ከኤርትራ የሚንደረደሩ ተቃዋሚዎችን የመመከትና ከግብፅ አልያም ከኤርትራ በኩል ጥቃት ሊኖር ይችላል የሚለው ስጋት ውስጥ ውስጡን ሲናፈስ ሰንብቷል።
የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በሰጡን ምላሽ የኢትዮጵያና የሱዳን የፀጥታ ትብብር ስምምነት ለዓመታት የቆየ ሲሆን የሁለቱ ሀገሮች የጋራ የድንበር ኮምሽንም ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።
በተለይ ተዋሳኝ ክልሎች የሚተገብሩት የድንበር አካባቢ የፀጥታ ትብብርም አለ። የጋራ ጦር የማስፈር እንቅስቃሴ ግን አልተካሄደም ብለዋል አቶ መለስ።
ዋዜማ ባገኘችው መረጃ ድንበር አካባቢ ቀደም ሲል የህዳሴውን ግድብ እንዲጠብቅ ከተመደበው ስራዊትና የአየር መከላከያ ምድብተኛ በተጨማሪ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ወታደሮች ከሱዳን አቻዎቻቸው ጋር በድንበር እንዲሰፍሩ ተደርጓል።
የሱዳን የኢትዮጵያና የኤርትራ አዋሳኝ ድንበር ከመቼውም ጊዜ ከፍ ያለ ወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚታይበት መሆኑንም ከአካባቢው ነዋሪዎች ይሰማል።
በዓባይ ውሀ ዙሪያ በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው ውዝግብ ይበልጥ የተካረረ ሲሆን ግብፅ ጉዳዩ እልባት ካላገኘ ህልውናዬ አደጋ ላይ ነው ስትል የችግሩን ግዝፈት እየተናገረች ነው። በዚህ ሳምንት ግብፅን የጎበኘው በጠቅላይ ሚንስር ሀይለማርያም ደሳለኝ የተመራው የልዑካን ቡድን የተለያዩ የትብብር ስምምነቶችን በመፈራረም የሁለቱን ሀገሮች መተማመን ለመመለስ ቢሞክርም ግብፃውያኑ ኢትዮጵያን ማስገደድ የሚቻልበት መላ ካልተፈጠረ ግብፅ የከፋ አደጋ ሊገጥማት ይችላል እያሉ ነው።
ግብፅ የዓለም ባንክ ሁለቱን ሀግሮች እንዲያደራድር ሃሳብ ብታቀርብም ኢትዮጵያ ሳትቀበለው ቀርታለች። [ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ያድምጡ]
https://youtu.be/RsDgaVhdxSg