የዛሬው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የፊት ገጽ 78ኛ ዓመት፣ ቁጥር 161 ይላል፡፡ እድሜ ቁጥር እንጂ ሌላ ምንም እንዳልሆነ ተገለጠልኝ፡፡ ካተመው ይልቅ ያላተመው፣ ከጻፈው ይልቅ ያበለው ፊቴ ድቅን እያለብኝ፡፡
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት 95ኛ ዓመት ሰሞኑን ሲከበር እድሜ ቁጥር እንጂ ሌላ ምንም እንዳልሆነ ተገለጠልኝ፡፡ ከሞከረው ይልቅ ያልሞከረው፣ ካሳካው ይልቅ ያላሳካው ፊቴ ድቅን እያለብኝ፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ በ1967 ነው የተወለደው፡፡ የዘመን ጋዜጣም ኾነ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ታናሽ ወንድም ነው፡፡ ግማሽ ምዕተ ዓመት በሕይወት ሲኖር ታዲያ አበርክቶቱ ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ ከታላላቆቹም የላቀ ነው፡፡ የዕድሜውን ያህል ነው ባይባልም፡፡ እናም ጥሎብኝ በስስት እመለከተዋለሁ፡፡ ብዙ ምክንያቶች አለኝ፡፡
ዛሬም ድረስ አንድ ለናቱ ነው፡፡ 34ቱ ዩኒቨርስቲዎች የሕንጻ አጽም እንጂ የሕትመት አቅም አልገነቡም፡፡ ለሙሁራዊ ሙግት ገና ናቸው፡፡ የነ ቶሎ ቶሎ ቤት በመኾናቸው ቁሳዊው ማንነታቸው ይበልጥ ያስጨንቃቸዋል፡፡ ስላስገነቡት የቤተ መጻሕፍት ሕንጻ ስፋት እንጂ በዉስጡ መገኘት ስላለባቸው መጻሕፍት ግድ አይላቸውም፡፡
ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ የምሳሳውም በዚህ ረገድ አንድ ለናቱ በመኾኑ ነው፡፡
ምን ተፈጠረ?
ከሰሞኑ የዩኒቨርስቲውን ፕሬስ አስመልክቶ ከወደ 6ኪሎ የምሰማው ወሬ ኢህአዴግን ይሸታል፡፡ ዕዉቀት አትሞ ሲቸረችር የኖረው ይህ ፕሬስ ከመጻሕፍት ጎን ሻምፑና ኮንዲሽነርም አብረህ ለመቸርቸር ተሰናዳ ተብሏል አሉኝ፡፡ በቅርቡ የጥናት ወረቀትና 555 ጉለሌ ሳሙናን አንድ ሼልፍ ላይ ልናገኛቸው እንችላለን፡፡ ቀልዴን አይደለም፡፡ ነገሩ በከፊል እንኳ እውነት ቢኾን አዝማሚያው ስጋት ላይ የሚጥል ነው፡፡
ፕሬሱ ጭልጥ ወዳለ ንግድ እንዲንደረደር ግፊቱ በርትቶበታል የሚባለው ከአለቆቹ ነው፡፡ አገሪቱን እየናጠ ያለው የካድሬ መንፈስ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መውረዱን ተከትሎ ትልቁ ዩኒቨርስቲም ወደ ትንሽነት እየተንደረደረ ይመስላል፡፡ የፕሬስ ክንፉ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ቅርጽን ይዞ እንዲዋቀርና ከፊል ትኩረቱን ገንዘብ በማራባት ላይ እንዲያደርግ፣ ለዚህም አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲጀምር ተነግሮታል ይላሉ የዉስጥ አዋቂዎች፡፡
በሚያንጸባርቁት የነጻ ሐሳብ ልዕልና ሳቢያ ከተቋሙ የተገፉት የአደባባይ ምሁሩ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላያ ባሰፈሩት ሐተታ ዩኒቨርስቲውን በኢንዱስትሪ አምሳያ መተዳደሩን ተችተዋል፡፡ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንቱ በየንግግራቸው የሚያዘወትሯቸውን ቃላት አጣቅሰው ተሳልቀዋል፡፡ ነገሩ ስላቅ አይደለም፤ ደረቅ ሐቅ ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ ደጋግመው የሚጠቀሟቸው እዝሎችና ቅጽሎች ‹‹አደረጃጀት››፣ ‹‹ቅበላ››፣ ‹‹ግንባታ››፣ ‹‹የኃይል ትስስር››፣ ‹‹አንድ ለአምስት›› ከላይ የተዘረዘሩት ቅጽሎችና ሐረጎች፤ የኢንዱስትሪ የምርታማነትና የውጤት ደረጃ አመልካች መለኪያዎች፤ የአንድ ፋብሪካ የምርት ቁጥጥር ሓላፊ ወይም የሕንፃ ግንባታ ተቆጣጣሪ “ካቦ”፣ በሚያቀርበው ሪፖርት የሚጠቀማቸው ቃላት እንጂ፣ “ⷈሉ አመክሩ ወዘሠናየ አጽንዑ”(ኹሉን መርምሩ መልካሙንም አጽንታችኹ ያዙ) የሚለውን ታላቅ ኃይለ ቃል ይዞ የተነሣን፣ የማእምራን መዲና የኾነ ዩኒቨርሲቲን መንፈስ የሚወክል ወይም የሚመጥን አይደለም፡፡
ሲሉ አጥንት የሚሰብር ትችት አዝንበዋል፡፡ ዶክተር ዳኛቸው የጻፉት ፈጠራ እንዳልሆነ ለመረዳት አንድ ታክሲ መያዝ በቂ ነው፡፡ 6 ኪሎ ሽሬ ሜዳን ለመምሰል ምንም አልቀረመውም፡፡
ከሳምንት በፊት እግር ጥሎኝ ወደ 6ኪሎ ቅጥር ግቢው ባቀናሁ ጊዜ የተሰማኝን ቁጭትና የስሜት ስብራት ሁሉ በጽሑፋቸው ክሽን አድርገው ሕመሜን ስላሹልኝ ዶክተር ዳኛቸውን ዉጌሻዬ ብያቸዋለሁ፡፡
ከዩኒቨርስቲው ግርማ ሞገስ መገርሰስ ጋር ተያይዞ አብሮ መነሳት አለበት ብዬ የማነሳው ደግሞ የፕሬስ ክንፉን በመኾኑ በዚህ ጽሑፍ ስለዚሁ ተቋም አጭር ሐተታ አቀርባለሁ፡፡
የተፋሰስ ፖለቲካ ተመራማሪው ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖን ሳይጨምር ፕሬሱን እስከዛሬ ስድስት ዳይሬክሮች መርተውታል፡፡ መሥራቿን ሚስስ ኢነስ ማርሻልን ዉለታና ዘመን የሚደርስ ግን የለም፡፡ ለ24 ዓመት በዳይሬክተርነት ፕሬሱን በመምራት በአንዲት አነስተኛ ክፍል ፀንሰው፣ በራሱ ሕንጻ አዋልደው፣ ፕሬሱን በሁለት እግሩ እንዲራመድ ያደረጉ ትጉህ ሴት ናቸው፡፡
ከርሳቸው በኋላ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ (በተጠባባቂነት ለአንድ ዓመት)፣ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፣ ወይዘሮ መሰለች ሀብቴ (በተጠባባቂነት ለአንድ ዓመት)፣ ፕሮፌሰር ዳርጌ ወሌና ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ ተተካክተዋል፡፡ የአሁኑ ዳይሬክተር ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖም ከሰሞኑ በዶክተር በለጠ ሊተኩ እንደሚችሉ የዋዜማ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ላለፉት ጥቂት ዓመታት በከፍተኛ አርታኢነት ያገለገሉት አቶ ብርሃኑ ደቦጭም ከዩኒቨርስቲው ማኔጅመትን ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሥራቸውን በገዛ ፍቃዳቸው እንደለቀቁ ለፕሬሱ ቅርብ የኾኑ ምንጮች ነግረውኛል፡፡
ከፕሮፌሰር አንድሪያስ በኋላ በመጡት አመራሮች ዘንድ ፕሬሱ የጥቃቅንና አነስተኛ አደረጃጀት ኖሮት ወደ ኢንተርፕራይዝነት አድጎ ብዙ ገንዘብ እንዲያመጣ በተለይም በአሁኑ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት በኩል ከፍ ያለ ፍላጎት እንዳለ ይነገራል፡፡ ይህን ለማሳካትም የዩኒቨርስተው ማተሚያ ቤት ኃላፊና የዶክተር አድማሱ ጸጋዬ ዘመድ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሰው ዉጥኑን ወደ ተግባር ለማሸጋገር እየተጉ ነው፡፡
በዚህ አሠራር ተመርጠው የሚታተሙ መጻሕፍት እንደወትሮው ለጥራት ሲባል ከዩኒቨርስቲው ዉጭ ወደሚገኙ ማተሚያ ቤቶች ተወስደው እንዳይታተሙ ይደረጋል፡፡ በላቀ ይዘታቸው ከሚመረጡ ሥራዎች ጎን ለጎን ገበያ ተኮር የኾኑ የጽሕፈት ሥራዎች የቅድሚያ ትኩረት ያገኛሉ፡፡ የ2ኛ ደረጃ አጋዥ መጻሕፍት ጥሩ ገበያ ስለሚኖራቸው የተለየ ትኩረት ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡ ይህ ሁሉ ፕሬሱ ኪሱን እንዲያደልብ የተመታ መላ መኾኑ ነው፡፡ ለመኾኑ በየትኛው ዓለም ነው የዩኒቨርስቲ ፕሬስ ትርፍን ግብ አድርጎ የሚሠራ?
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ በግማሽ ክፍለ ዘመኑ በይዘታቸው ከፍ ያለ ደረጃ የሚሰጣቸው በርካታ መጻሕፍትን የንባብ ብርሃን እንዲያገኙ ማድረጉ የሚታበል አይደለም፡፡ ኾኖም በቅጂ ብዛት ብዙ ርቀት መሄድ አለመቻሉ ገቢውን እየተፈታተነው ቆይቷል፡፡ የሕይወት ተፈራ Tower in the Sky፣ የፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ History of Modern Ethiopia የብላቴን መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፣ የጌታቸው ኃይሌ ደቂቀ እስጢፋኖስ ተደጋግመው መታተም ከቻሉ የቤቱ ሥራዎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከነዚህ ዉጭ የቁጥር ስኬት ተሰምቶ አያውቅም፡፡ በፕሬሱ ከሚታተሙ ሥራዎች 98 ከመቶ የሚኾኑት የቅጂ ብዛታቸው ከ3ሺህ እና ከ5ሺህ አይዘልም፡፡ ይህ ግን ፕሬሱን ሊያሳስበው የሚገባ ነጥብ ሊሆን አይገባመው፡፡ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በሚሊዮን ኮፒ የተሸጡበት የዩኒቨርስቲ ፕሬስ ዓለም ዓይታ አታውቅም፡፡ ኬምብሪጅ፣ ኦክስፎርድ፣ ዬል፣ ዎርዊክ፣ ኤምአይቲ…እና ሌሎች ምዕራባዊ ከፍተኛ ተቋማትን እንኳ ብንወስድ የሕትመት ቁጥር ስኬታቸው በሺዎች የተገደበ ነው፡፡ የሚሊዮኖች ቅጂ የኮሜርሻል አታሚዎች ታሪክ ዉስጥ ብቻ የሚገኝ ቋንቋ ነው፡፡
እርግጥ ነው ብዙ ተደክሞበት፣ የበርካታ አርታኢዎችን ጊዜ ወስዶ፣ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ተለፍቶበት የሚታተም አንድ መጽሐፍ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ባላት አገር በ3ሺህ ቅጂ ብዛት ሲቀጭ የማንንም ስሜት የሚጎዳ መልዕክት አለው፡፡ ያም ኾኖ ሁሌም መዘንጋት የሌለበት ዩኒቨርስቲ ፕሬሶች በየትኛውም አገር ተመሳሳይ የተደራሽነት ፈተና እንደሚገጥማቸው ነው፡፡ ይህም የሚኾነው በአመዛኙ ይዘታቸው ሞያዊ፣ አቀራረባቸውም አካዳሚያዊ ከመሆን የሚመነጭ ነው፡፡ የአንድን የጥናትና ምርምር ሥራ በኅትመት ቁጥር ስኬቱ መለካት የጀመረ ፕሬስ ቤቱን ወደ ኪዮስክነት ቢለውጥ የሚገርም አይሆንም፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ እየተንደረደረ ያለውም ወደዚህ ቁልቁለት ነው፡፡
የወረቀት ሕትመት ዘርፍ በአያሌው ፈተና ዉስጥ መውደቁ አገራዊና አሕጉራዊ ክስተት ብቻ ሳይሆን ዓለማቀፋዊም ነው፡፡ ከወረቀት ዋጋ መናርም በላይ የቴክኖሎጂ መዘመንን ተከትሎ ጋዜጦችና መጽሐፍ አሳታሚዎች በተሸናፊነት እጅ ሰጥተዋል፡፡ ብዙዎች ከገበያ ሲወጡ ጥቂቶች ብቻ በግማሽ ሳንባ እየተነፈሱ ነው፡፡
የዩኒቨርስቲ ፕሬሶች በአመዛኙ ይህ ፈተና ያልደቆሳቸው በኢንዶውመንት፣ በቤተ መጻሕፍቶች በጀት፣ በእርስበርስ ግዢና ድጎማ፣ ለምርምር በሚለቀቁ የገንዘብ ድጋፎች፣ ዕዉቀትን በሚደግፉ ባለሀብቶች ችሮታ ሕይወታቸውን መምራት በመቻላቸው ነው፡፡ ቀዳሚ ግባቸውም እውቀትን እንጂ ንዋይን ማብዛት ስላይደለ ጦም ካላደሩ በስተቀር ዕለታዊ ተግባራቸው በትርፍ መቀነስ አይስተጓጎልም፡፡
አብዛኛዎቹ የዩኒቨርስቲ ፕሬሶች ከገዜው ጋር ለመራመድ በብርቱ እየለፉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የሚያትሟቸው መጻሕፍትና የጥናት ወረቀቶች ወደ ዲጂታል ቅርጽ በመለወጥ በኢሪደር፣ በታብሌቶች፣ በኪንድል፣ በስማርት ስልኮች መነበብ የሚችሉ ኾነው እንዲዘጋጁ ማድረግ አንዱ የሄዱበት መንገድ ነው፡፡ ይህ የሰለጠነ ባለሞያ ማዘጋጀትን ይጠይቅ ይሆናል፡፡ የማይቻልና ከብዶ መታየት ያለበት ሂደት ግን አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ለዚህ ሽግግር ገና ነኝ ብሎ መቀመጥ አይኖርበትም፡፡
የገቢ መመናመንን ተከትሎ ከፊል የዩኒቨርስቲ ፕሬሶች በሕይወት ለመቆየት ሁነኛ መላ ዘየዱ የሚባለው ቅጂን በትዕዛዝ ብቻ የማተም ስልትን በመከተል ነው፡፡ በፍላጎት ብቻ የማተም ስልት በእንግሊዝኛው (Print On Demand- POD) ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህ በተለይ በይዘታቸው እጅግ ጠቃሚ ኾነው ነገር ግን የብዙ ሺህ ሰዎች ፍላጎትና ምርጫ ሊኾኑ የማይችሉ ሞያ ተኮር ሕትመቶችን ወጪ ቆጣቢ በሆነ ዘዴ ለማተም የመሞከር ሂደትን ያካተተ ነው፡፡
ለአብነት ፋሺስት ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ የተጠቀማቸው የመርዝ ጋዝ ዓይነቶችን የሚተርክ ቴክኒካል መጽሐፍ በአገራችን የብዙኃንን ቀልብ ለመሳብ የሚቻለው ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ኾኖም የዚህ መጽሐፍ ፋይዳ ለዘርፉ ባለሞያዎች፣ ለታሪክ አጥኚዎች ከፍ ያለ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ይዘት ያላቸውን መጻሕፍት በመቶ ሺዎች ማባዛት የሚታሰብ አይደለም፡፡ በትንሽ ቁጥር ማባዛትም ዉጤቱ ኪሳራ ነው፡፡ ይህም የሚኾነው አንድ መጽሐፍ በአንድ ጊዜ ብዙ ሺሕ ቁጥር ካልታተመ የግብአት ወጪው ከፍ ስለሚል አዋጪ አለመሆኑ ነው፡፡ በተለመደው ዘዴ የሚታተሙ መጻሐፍት ቁጥራቸው በበዛ ቁጥር ደግሞ ዋጋቸው እያነሰ ይሄዳል፡፡ ትንሽ ቁጥር ሲታተም የአንዱ መጽሐፍ የተናጥል ዋጋ እጅግ ዉድ ስለሚሆን በየትኛውም ስሌት አክሳሪ ነው የሚኾነው፡፡
ለዚህም ነው Print On Demand ሁነኛው መፍትሄ የሚኾነው፡፡ ይህን ለማድረግ ዘመናይ ማተሚዎችን መትከል ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ማተሚያዎች ከኮምፒውተር በቀጥታ ወደ ማባዣ በሚላክ መልዕክት አንድ ቅጂ መጽሐፍም ቢኾን ሲፈለግ ብቻ አትመው ማውጣት የሚችሉ ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ነገሩን ሰምቶት የሚያውቅም አይመስልም፡፡
ዞሮ ዞሮ የማትመው ሥራ በይዘቱ ግሩም ቢኾንም ብዙ አንባቢ አላስገኘልኝም ብሎ የሥራ ዘርፍ መቀየር በየትኛውም ስሌት የቸርቻሪነት እንጂ የሙሁራዊነት መንፈስን የሚወክል አይደለም፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ አወቃቀር
የዩኒቨርስቲው ሴኔት ሰባት አባላት ያሉትን የፕሬስ ኤዲተሮች ቦርድ ይሾማል፡፡ ይህ ቦርድ ማንኛውንም ረቂቅ ሥራ ለኅትመት ብቁ ስለመሆኑ ቅድመ ግመገማ ያካሄዳል፡፡ ረቂቅ ሥራው የቦርዱን ቅድመ ግመገማ ማለፍ ከቻለ ብቻ ወደ ተመረጡ የዘርፍ ባለሞያዎች ይመራል፡፡
በዚህ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ የኤዲተሮች ቦርድ ኾነው በማገለግለግ ላይ ያሉት ዶክተር ጣሰው ወልደ ሐና፣ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ፣ ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም፣ ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ፣ ፕሮፌሰር ዳርጌ ወሌ፣ ዶክተር በከለ ጉተማ እና አቶ መስፍን ገዛኸኝ ናቸው፡፡
የቦርድ አባላቱ በበርካታ አስተዳደራዊና የግል ሥራዎች ስለሚወጠሩ ለፕሬሱ የሚሰጡት ጊዜ እምብዛምም እንደሆነ ይነገራል፡፡ የአካዳሚክ ነጻነታቸውን ለማስከበር የሚሄዱበት ርቀትስ እስከምን ደረጃ ነው የሚለውም ሌላው የመነጋገሪያ ነጥብ ነው፡፡
አሁን አሁን በመንግሥት ላይ መልካም ገጽታ ማጎናጸፍ ባልቻሉና ከዚህ በተቃራኒ ለቆሙ የምርምርና የሐተታ ጽሑፍ ዉጤቶች ለቦርድ አቅርቦ ማሳለፍ ግመልን በመርፌ ቀዳዳ ለማሳለፍ እንደመሞከር ያለ ነው ብለው የሚናገሩ ደራሲዎች አልጠፉም፡፡ ብዙዎቹ የፕሬሱ ቦርድ አባላት በግል ስለነጻነት የሚዘምሩ ቢኾኑም በጠቅላላው የመንግሥት ጥርስ ዉስጥ መግባት የሚያሰጋቸው በመሆኑ አንዳንድ ሥራዎችን ጎመን በጤና ብለው ገሸሽ ማድረግን ይመርጣሉ፡፡
ሥራዎቻቸው ገለል የተደረጉባቸው ተመራማሪዎች በበኩላቸው ወደ ግል አታሚዎች ፊታቸውን ከማዞር ዉጭ አማራጭ ያጣሉ፡፡ የግል አታሚዎች ይዘትን ተመልክተው ደፍሮ በማተም የተሻለ ነጻነት ቢኖራቸውም በኅትመት ጥራት፣ የጠራ አርትኦት ሂደትን በመከተል፣ በተደራሽነት ረገድ ዉስንነት የሚታይባቸው ናቸው፡፡ ግርማና ቁመናቸውም ቢኾን ከዩኒቨርስቲው ፕሬስ ጋር ሲነጻፀር ኮሳሳ ነው፡፡
አብዛኛዎቹ ቱባ የምርምር ሥራዎች ወደ ዩኒቨርስቲው ፕሬስ የሚያመሩትም ከተደራሽነት ይልቅ ሞገስን በመሻት ሊሆን ይችላል፡፡ በዩኒቨርስቲ ፕሬስ ማሳተም ከፍ ያለ ማዕረግን የሚሰጥ ከመሆኑ አንጻር ማለቴ ነው፡፡ ይህ ብቸኛ ምክንያት ነው ማለት ግን አይደለም፡፡
አታሚውን በማየት የመጽሐፉን ከፍታ መገመት በየትኛውም ዓለም የተለመደ ነው፡፡ ይህ እውነታ ደራሲዎች ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ እንዲተሙ ግፊት ቢፈጥር የሚገርም አይሆንም፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ የታተሙ ሥራዎች ተራ ኾነው የማያውቁትም ለዚሁ ነው፡፡
ነገሩን በንዋይ መነጽር ስንመለከተው ግን አንድን የጽሑፍ ሥራ በዩኒቨርስቲው ፕሬስ ማሳተም የሚያመረቃ ገቢን አምጥቶ አያውቅም፡፡ ዩኒቨርስቲው ለደራሲዎች ከመጽሐፍ የሚከፈለው የትርፍ ህዳግም ቢኾን ከግል አታሚዎች ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ መኾኑ እርግጥ ነው፡፡
ለምሳሌ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ለደራሲ እስከዛሬ የሰጠው ከፍተኛ ድርሻ ከትርፍ 15% ብቻ ሲኾን የትርፉ 90 ከመቶ ወደ ዩኒቨርስቲው ኪስ የሚገባ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በግል አታሚዎች ዘንድ ተቃራኒ መልክ አለው፡፡ የግል አታሚዎች ለደራሲዎች እስከ 50 ከመቶና ከዚያም በላይ የትርፍ ድርሻን ይቸራሉ፡፡ በተደራሽነትም የግል አታሚዎች ከፍ ያለ የቅጂ ክብረ ወሰን በማስመዝገብ ይታወቃሉ፡፡ ኾኖም የግል አታሚዎች ገበያ እንጂ ይዘት አይመራቸውም፡፡ የዩኒቨርስቲ ፕሬሶች ወሳኝ የሚኾኑትም ለዚሁ ነው፡፡
እንደ ማጠቃለያ
በየትም ዓለም የሚገኙ ዩኒቨርስቲ ፕሬሶች ራሳቸውን ቢችሉ አይጠሉ ይሆናል እንጂ ግባቸውን ትርፍ ማካበት አድርገው አይቋቋሙም፤ ተልእኳቸውም የሚኾነው የዩኒቨርስቲ ማኅበረሰቡን በዕውቀት ማጠላለፍ፣ ከዚያም አልፎ ሰፊውን ኅብረተሰብ ከአዳዲስ ግንኝቶች ጋር ማስተዋወቅ ነው፡፡ ለንዋይ ሳይኾን ለዕዉቀት የሚተጉ በመኾናቸው ነው ክብር የማይለያቸው፡፡
አሁን አገሪቱ ዉስጥ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ለብሔር ብሔረሰቦች በኮታ የተከፈቱ ጥቃቅንና አነስተኛ የክልል ዩኒቨርስቲዎችም ሆነ ሰፊው ማኅበረሰብ ከጉምቱው ፕሬስ ተጠቃሚ እየሆነ እንዳልሆነ መገመት ይቻላል፡፡ አንድም በስርጭት መገደብ፣ አንድም በስርጭት መንገዱ አባጣ ጎርባጣ መሆን፣ አንድም ለጥናትና ምርምር የሚሰጠው ቦታ እያነሰ መምጣት እንደምክንያት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ በግለ ታሪክ እና በታሪክ መጽሐፍት ዘርፍ ድንቅ የኾኑ ሥራዎችን አበርክቶልናል፡፡ ጠባብ ርዕሰ ጉዳይን የያዙ በሞያ የተገደቡ፣ ለብዙኃን የማይኾኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ ብዙም ርቀት አልተጓዘም፡፡ ማጣቀሻ መጽሕፍትም ላይ እንዲሁ፡፡ በቀጣይ ዓመት በርካታ ብሉይ (ጊዜ አይሽሬ) መጽሐፍትን በአዲስ ለማተም እቅድ መያዙም ተስፋን የሚያለመልም ነው፡፡ የስኳርና የሳሙና ግብይቱን ግን አይመጥነውምና እርግፍ አድርጎ ቢተወው እላለሁ፡፡
በወጪ ራሱን መቻል የሚለው ምክንያትም ቢኾን ዉኃ አይቋጥርም፡፡ የዩኒቨርስቲ ፕሬሶች በገቢ ራሳቸውን መቻል አይጠበቅባቸውም፡፡ ይልቅ ተዝቆ ከማያልቀው የዩኒቨርስቲው በጀት አስራት ወደ ፕሬሱ ቢገባ የሚያስኮንን ሐሳብ አይሆንም፡፡
ራሱን ይቻል በሚል ካድሬያዊ ዉሳኔ ተቋሙን ወደ ኪዮስክነት ከመለወጥ ይልቅ ከፕሬሱ የሚወጡ የጥናት ወረቀቶችና ምርምሮች በቀጥታ ሕዝቡን የሚደርሱበት መንገድ ማመቻቸት መቅደም ይኖርበታል፡፡ እርግጥ ነው የሕዝብ ቤተ መጻሐፍት በሌሉበት ሁኔታ ይህን ማድረግ ፈተናው ብዙ ነው፡፡
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዓመታዊ ግዢ ላይ መጻሕፍት እንደ የሶፍት ወረቀት በመደበኛነት እንዲገቡ ማድረግም አንድ አማራጭ ነው፡፡ እንደነገሩ በተቋቋሙ የመሥሪያ ቤት ቤተ መጻሕፍቶች አዲስ ርዕይ፣ የአዲስ ልሳን፣ የዘመን መጽሔትና የአዲስ ዘመን ጋዜጣን በአስገዳጅነት ማስገባት ቢቀር ማንም አይጎዳም፡፡
ከዚያ ይልቅ በየዓመቱ የፕሬሱን የኅትመት ዉጤቶች በክፍያ መሥሪያ ቤቶች ወደ ቤተ መጻሕፍቶቻቸው እንዲያስገቡ ቢደረጉ የምንሳሳለትን ፕሬስ ሊታደጉት ይቻላቸዋል፡፡
ዞሮ ዞሮ መሠረታዊው ችግር የአመለካከት ነው ባይ ነኝ፡፡ የዩኒቨርስቲው ፕሬስ ራሱን እንደ አንድ መጽሐፍ ቸርቻሪ ያየ ለታ ነው ነገሩ ሁሉ የሚያበቃለት፡፡
ሙሴ -ለዋዜማ ራዲዮ