ዋዜማ ራዲዮ- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ባሉ አመታት ብዙ ኪሳራ ካደረሰበት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሶስት ሺህ አውቶብሶችን ሊገዛ መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማውን የትራንስፖርት ችግር ያቃልላሉ ያላቸውን ሶስት ሺህ አውቶብሶችን በዚህ 2012 አ.ም ነው ለመግዛት ያቀደው። አውቶብሶቹን ቢሸፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንደስትሪ ከተባለው የሜቴክ አንድ አካል ከሆነው ቅርንጫፍ ነው የሚገዛው።
ዋዜማ ራዲዮ ከአንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅትና ከሸገር ባስ ምንጮቿ ያገኘቸው በደብዳቤ ጭምር የተደገፈ መረጃ እንደሚያሳየው ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ባለስልጣን ጠያቂነት ነው ለሁለቱ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ሰጭ ድርጅቶች ማለትም ለሸገር ባስና ለአንበሳ አውቶብስ አገልግሎቶ ድርጅት በመስከረም 23 2012 አ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ሶስት ሺህ ባሶቹ እንዲገዙላቸው የጠየቀው።
“ይህ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ባለስልጣን ጥያቄ የከተማው ካቢኒ በጠየቀው መሰረት ይፈጸምለት” ሲል ትእዛዝ የሰጠበትን የከንቲባ ጽህፈት ቤት ደብዳቤም አግኝተናል።
ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ መስከረም ወር ላይ ከሜቴክ የተገዙ አንድ መቶ አውቶብሶችን ለአንበሳ አውቶብስ ድርጅት ሲያስረክቡ በዚህ አመት የሚገዙት ሶስት ሺህ አውቶብሶች ከአውሮፓ ሀገራት ኩባንያዎች እንደሚገዙ ተነግሮ ነበር።
ከ2004 እስከ 2006 አ.ም ለአንበሳ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 550 አውቶብሶችን ከሜቴክ ገዝቶለት ነበር።ሆኖም ወዲያው ነበር 361ዱ አውቶብሶች በተለያየ ምክንያት ከጥቅም ውጭ የሆኑት። ሌሎቹ 189 አውቶብሶች ደግሞ በመለዋጫ አለመገኘት ምክንያት እስካሁን ጥቅም መስጠት አልቻሉም።
በ2010 አ.ም እንዲሁ ለአንበሳ አውቶብስ ከሜቴክ ሌላ 453 አውቶብሶች ተገዝተው በአንድ አመት ውስጥ 48ቱ ከጥቅም ውጭ ሆነዋል። ይሄ አመት ከገባ መስከረም ወር ላይ እንኳ ከሜቴክ ተገዝተው ለአንበሳ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ከተሰጡት 100 አውቶብሶች ውስጥ ሶስቱ ከወዲሁ ተበላሽተው ቆመዋል።ሁለቱ ደግሞ ወርም ሳያገለግሉ እቃ ተቀይሮላቸዋል።
የአንበሳ እና የሸገር ባስ የስራ ባልደረቦች እንደሚሉት አውቶብሶች ከውጭ ሲገዙ እያንዳንዳቸው ከሶስት እስከ አራት ሚሊየን ብር ነው የሚጠይቁት ፣ የሜቴኩ ቢሸፍቱ አውቶሞቲቭ ግን ከ4.1 እስከ 4.3 ሚሊየን ብር ለእያንዳንዱ አውቶብስ ዋጋን ይቆርጣል። ሜቴክ ክፍያ ሲጠይቅም በአንዴ 100 ፐርሰንት ነው የሚያስከፍለው ፣ ከውጭ ሲገዛ ግን እስከ አምስት አመት የተከፋፈለ ክፍያን የሚያስፈጽሙ ኩባንያዎችን ማግኘት ይቻላል።
በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከዚህ በፊት የደረሱ ኪሳራዎች ከግምት ውስጥ ሲገቡ የአሁኑ ግዥ ተመራጭ የሆነበት ምክንያት ግልጽ አልሆነሞ። ሜቴክ ባለፉት አመታት በተለያዩ ግዥዎችና የፕሮጀክት መጓተት ችግሮች ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ እና እዳ ውስጥ የተዘፈቀ ተቋም መሆኑ ይታወቃል። አሁን አስተማማኝ ኮርፖሬሽን ስለመሆኑም ያሳየው መተማመኛም የለም። [ዋዜማ ራዲዮ]