- በብር ላይ ያለው መተማመን እያሽቆለቆለ ነው
- ከውጪ የሚላክ ገንዘብ ከባንክ ይልቅ ወደ ትይዩ ገበያ እያመዘነ ነው
ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ገበያ በባንኮች እና በትይዪ ገበያ ( በጥቁር ገበያ) መካከል ያለው ልዩነት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሰፋ መጥቷል።
ዋዜማ ራዲዮ የአሜሪካ ዶላር በባንኮች እና በጥቁር ገበያ ያለውን ዋጋ ለማወዳደር ቅኝት አድርጋለች።ባደረግነው ቅኝትም አንድ የአሜሪካ ዶላር በኢትዮጵያ የተለያዩ ንግድ ባንኮች በሚገዛበትና በጥቁር ገበያ ያለው የዋጋ ልዩነት ከ20 ብር አልፏል።
ሰኞ በነበረ ዋጋ አንድ የአሜሪካ ዶላርን የንግድ ባንኮች 44 ብር ከ36 ሳንቲም ሲገዙ ነው የዋሉት።ሆኖም በህገ ወጥነት በተፈረጀው የጥቁር ገበያ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች በተመሳሳይ በሰኞ እለት አንዱን የአሜሪካ ዶላር በ65 ብር ሲገዙ እንደነበር የዋዜማ ሪፖርተር በተለያዩ ቦታዎች ባደረገው ቅኝት ተረድቷል።በዛ ያለ ዶላር ለሚያቀርብ ግለሰብም ከ65 ብር በላይ ዋጋ እንደሚሰጠውም ነው ያስተዋለው። የዋጋው ልዩነት ማክሰኞም በተመሳሳይ የታየ ነው።
በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ገበያ ውስጥም በይፋዊ እና በጥቁር ገበያ መካከል እንዲህ አይነት የዋጋ ልዩነት ሲታይ የአሁኑ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።ከሶስት አመታት በፊት በባንኮች እና ትይዩ ገበያ መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት ከሁለት ብር አይበልጥም ነበር።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት ስልጣን ከያዘ በሁዋላ መንግስት ከለጋሾች መጠኑ በዛ ያለ ምንዛሬን አግኝቶ ለተጠቃሚዎች በማቅረቡ የሁለቱ ገበያዎች የምንዛሬ ዋጋ ከመቀራረብ አልፎ በባንኮች በኩል ያለው ዋጋ ብልጫን እስከማሳየት ደርሶ ነበር።ሆኖም ብዙ ሳይቆይ ልዩነቱ እየሰፋ መጥቷል።
የውጭ ምንዛሬ ገበያው ላይ እየታየ ያለው መናር የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያለበት የበረታ ቀውስ ምን ያህል ስር የሰደደ እንደሆነ አስረጅ መሆኑን ባለባቸው ሀላፊነት ምክንያት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኢኮኖሚክስ ምሁር የገለጹልን። ኢትዮጵያ በዚህ አመት ላለፉት አመታት ባልታየ ደረጃ 3.6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬን ከወጪ ንግድ ማግኘቷ ቢገለጽም የትግራዩን ጦርነት ጨምሮ ሀገሪቱ የገባችበት የፖለቲካ ውጥንቅጥ የምንዛሬ ግኝቱ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣቱ ላይ መተማመንን የሚያስችል አልሆነም።።
ወርቅ ለክፉ ቀን ደርሶልናል!
የወጪ ንግድ ላይ የገቢ መሻሻል የታየውም በጥቅል ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ላይ እድገት ስለታየ ሳይሆን በማዕድን በተለይም በወርቅ የወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ እድገት ስለታየ ነው።የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው የማዕድን ዘርፍ የ2013 አ.ም የወጪ ንግድ አፈጻጸም 102 በመቶ ነው።
የትኛውም ዘርፍ እንዲህ ያለ አፈጻጸም አላሳየም። ይህም ለተገኘው 3.6 ቢሊየን ዶላር ገቢ አስተዋጽኦውን ትልቅ አድርጎታል።የ2012 አ.ም የወጪ ንግድ ገቢ 3.02 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ነው።በ2013 አ.ም የ600 ሚሊየን ዶላር ጭማሬ አሳይቷል ።ከ600 ሚሊየን ዶላር ጭማሬ ውስጥ የማዕድን የወጪ ንግድ ብቻውን የ475 ሚሊየን ዶላር ጭማሬውን ድርሻ አበርክቷል።
በ2012 አ.ም ከማዕድን የተገኘው የውጭ ምንዛሬ 207.6 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ሲሆን በዚህ አመት ደግሞ 682.2 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።በዚህ አመት ከተገኘው 682.2 ሚሊየን ዶላር ውስጥ ወርቅ ብቻውን 671 ሚሊየን ዶላርን አስገኝቷል።ይህም ባለፈው አመት ከተገኘው 196 ሚሊየን ዶላር ጭማሬን አሳይቶ ነው። ይህም በማዕድን ላይ የተገኘውን የገቢ ጭማሬ ሙሉ ለሙሉ የወርቅ ጭማሬ እንደሆነ ይጠቁማል።
የምርት መጠን ማደግና የአለማቀፍ ዋጋ ጭማሬም ለወርቅ የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ ገቢ አስተዋጾው ላቅ ያለ ሆኗል።ከማዕድን ውጭ ያለው የሀገሪቱ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ብዙም ለውጥ ያልታየበት ነበር።
2013 በትግራዩ ጦርነት ሳቢያ እንደ ሰሊጥ ያሉ እና የአምራች ኢንዲስትሪ ምርቶች ለወጪ ንግድ ማሽቆልቆል የተጋለጡበት አመትም ነበር ። የስነምጣኔ ባለሙያዎች እንደነገሩን መንግስት ታሪካዊ ሲል የገለጸው የ3.6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ግኝትም ሀገሪቱ በዚህ አመት ከገባችበት የፖለቲካ ውጥንቅጥ አንጻር ለኢኮኖሚ መረጋጋቱ አስተዋፅዖ ያደርጋል ተብሎ አይጠበቅም።
በስውር ከውጪ የሚላክ ገንዘብ
አጠቃላይ ሀገሪቱ ውስጥ ከሚንቀሳቀሰው የውጪ ምንዛሪ 78 በመቶ ያህሉ ይፋዊ ባልሆነው የጥቁር ገበያ እንደሚንቀሳቀስ ከሶስት አመት በፊት በአለማቀፉ የሰደተኞች ድርጅት የወጣ አንድ ጥናት ያትታል።
ባለፈው አንድ አመት ከውጪ ሀገር ወደ ሀገር ቤት የሚላከው የውጪ ምንዛሪ (remittance) በህጋዊ ባንኮች በኩል እየቀነሰ በጥቁር ገበያ እየጨመረ መሆኑን ያሰባሰብነው መረጃ ያመለክታል።
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክና ከዳሸን ባንክ ያገኘነው ግርድፍ መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፈው አንድ ዓመት በአማካይ በውጪ ከሚኖሩ ዜጎች ወደ ሀገር ቤት በሕጋዊ መንገድ የሚላከው የገንዘብ መጠን በ20 በመቶ እየቀነሰ ነው።
ባንኮች ከሚሰበስቡት አጠቃላይ የውጪ ምንዛሪ በአማካይ 27 በመቶ ያህል በውጪ ከሚኖሩ ዜጎች ሀገር ቤት ላሉ ዘመዶች የሚላክ (remittance) ነው። በአለማቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝ ያስከተለው ተፅዕኖ ለችግሩ መባባስ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ከሁለት አመት በፊት ሀገሪቱ ከወጪንግዷ ካገኘችው 3 ቢሊየን ዶላር ገደማ ምንዛሪ የበለጠ በውጪ ከሚኖሩ ዜጎች ያስገባችው 5 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ደርሶ ነበር።
ቀውስ ውስጥ ባለ ሀገር ማን ስለትርፍ ሊያስብ ይችላል?
የውጭ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በ2013 አ.ም 3 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ኮምሽነሯ ለሊሴ ነሚ መናገራቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ከሶስት ቀናት በፊት አስነብቧል። ገቢው የኢትዮቴሌኮም ከፊል አገልግሎትን በመሸጥ የተገኘውን 800 ሚሊየን ዶላር ይጨምራል። ይህ ገቢ ሀገሪቱ ከገጠማት ተግዳሮት አንፃር ትልቅ ስኬት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው። የሀገሪቱን የምንዛሪ ዕጥረት ለማቃለል አንፃር ግን ዋስትና መሆን የሚችል አይደለም።
ከቅርብ ወራት ወዲህ በሀገሪቱ ያለው ጦርነት ተለዋዋጭነትና የምዕራቡ አለም መገናኛ ብዙሀን የፈጠሩት አሉታዊ ምስል ባለሀብቶች ንዋያቸውን ወደ ሀገራችን ይዘው እንዲመጡ የሚያደፋፋር አልሆነም።
ወገብ ሰባሪው የዋጋ ንረት
ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋነኛው አሳሳቢ ጉዳይ የሆነው የዋጋ ንረትም በአመዛኙ በዚሁ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ጭማሬ ሳቢያ የተከሰተ ነው።በተለይ በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት በየወሩ ሪፖርት እየተደረገ ካለው 20 በመቶ አካባቢ አማካይ የዋጋ ንረት በእጅጉ ለመብለጡ ዋናው ምክንያት የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ እና አስመጭዎች በጥቁር ገበያ በውድ ዋጋ ሰብስበው ያስመጡት ምርት ላይ ወጪያቸውን እና ትርፋቸውን ታሳቢ ያደረገ ዋጋን በመተመናቸው ነው።
በውጭ ምንዛሬ ዋጋ ጭማሬ ሳቢያ ለተከሰተው የምርቶች ዋጋ ንረት መንግስትም በፖሊሲ የተደገፈ አስተዋጽኦ እያደረገ እንዳለ እምነታቸው እንደሆነ ለዚህ ዘገባ ያነጋገርናቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ባለሙያ።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከ2012 አ.ም መጀመርያ አንስቶ የሀገሪቱ መገበያያ ብር ከንግድ ሸሪክ ሀገራት መገበያያ አንጻር ትክክለኛ ዋጋውን እንዲያገኝ እና ኤክስፖርተሮችን በማበረታታት ከወጪ ንግድ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ያግዛል በሚል በየእለቱ የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን እንዲዳከም ማድረጉ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያተረፈለት የዋጋ ግሽበት ብቻ መሆኑንም ይገልጻሉባለሙያው ።ይህም የሆነው አስመጭዎች የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት የሚጠየቁት ብር በየእለቱ በጨመረ ቁጥር የሚያስመጡት ምርት ላይ ዋጋን በመጨራቸው ነው። መንግስት እየተከተለ ያለው የውጭ ምንዛሬ ተመን ፖሊሲ ውጤቱ ለዋጋ ንረት ያጋደለ ሆኗል ባይ ናቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ።
ከዚህ ቀደም ብሄራዊ ባንክ ጥቂት ሳንቲሞችን በውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ ለመጨመር ወራት ይወስዱበት ከነበረው አሰራር ለውጥ አድርጎ ሁለት አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአንድ የአሜሪካ ዶላር ላይ ብቻ የ16 ብር ጭማሬን አድርጎም በጥቁር ገበያ እና በባንኮች የውጭ ምንዛሬ ተመን መካከል ልዩነትን ማጥበብ ካልተቻለ ምናልባትም የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን ከዚህም በላይ መዳከም አለበት የሚል አማራጭን ብቻ መፍትሄ አድርጎ ወደማየት ያመራል።
የዋጋ ንረቱ አቅም ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ገንዘቡን ንብረት ላይ ወይንም በውጭ ምንዛሬ ቀይሮ ማስመጥ ላይ እንዲያተኩር እያደረገው እንደሆነ ከበቂ በላይ አብነቶች አሉ ይላሉ ባለሙያው።።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለረጅም ጊዜ አቋርጦት የነበረውን ለግል የውጭ ምንዛሬ ጠያቂዎች ምንዛሬ ማቅረብን ከሰሞኑ መጀመሩ የይፋዊ እና የጥቁር ገበያውን የዋጋ ልዩነት በጊዜያዊነት በጥቂቱ ሊያጠበው ይችላል ሆኖም ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም ብለውናል የኢኮኖሚክስ ባለሙያው። [ዋዜማ ራዲዮ]