ዋዜማ- በሀገሪቱ ካሉት 31 የንግድ ባንኮች ውስጥ 25ቱ አሁን ባለው ከባድ የገበያ ውድድር ውስጥ መቀጠል ስለማይችሉ ተዋህደው ጠንካራ ባንኮችን መፍጠር ብቸኛው አማራጭ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ ገለፀ፡፡

ብሔራዊ ባንክ የባንክ ኢንዱስትሪውን የገመገመበትን የፋይናንስ መረጋጋት (Financial Stability Report) ይፋ አድርጓል፡፡ ዋዜማ ሪፖርቱን ተመልክታ የሚከተለውን ዘገባ አዘጋጅታለች።

ሪፖርቱ 31ዱን ባንኮችን ለሦስት የከፈለ ሲሆን፣ እነዚህም ትልቅ (Large)፣መካከለኛ (Medium) እና ትንሽ (Small) ባንኮች ብሏቸዋል፡፡ 

ብቸኛው ትልቅ ባንክ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን፣ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ውስጥ ያለው የገበያ ድርሻ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በማደግ 50 ከመቶ ደርሷል፡፡

በ‹‹መካከለኛ›› ዘርፍ ስር አምስት ባንኮች ያሉ ሲሆን፣ እነሱም ከባንክ ዘርፍ ውስጥ ያላቸው የገበያ ድርሻ 29 በመቶ ነው፡፡ ቀሪዎቹ 25 ባንኮች ‹‹ትንሽ›› ተብለው የተመደቡ ሲሆን፣ ከባንክ ዘርፍ ያላቸው የጋራ የገበያ ድርሻ 22 በመቶ ብቻ ነው፡፡

ሪፖርቱ እንደሚገልጸው አጠቃላይ የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዙሪያ የተከማቸ ሲሆን ሌሎቹ የግል ባንኮች በንግድ ባንክ ጥላ ስር እያነሱ በመሄድ ላይ በመሆኑ ሌላ አማራጭ ማማተር ግዴታ እየሆነ መምጣቱን ያሰምርበታል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ አፈፃፀምና እድገት በዘርፉ ውስጥ የክምችት አደጋና ለትንንሽ ባንኮች እድገት አስጊ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ በዚህም ምክንያት ትንንሾቹ ባንኮች በመዋሃድ መጠናከር አለባቸው” ብሏል የግምገማ ሪፖርቱ።

በተለይ ካለፈው ዓመት ወዲህ ትንንሽ ባንኮች በብዛት የመዋሃድ አማራጭን እያጤኑ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያታቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባንክ ዘርፉን እየጠቀለለ ሲሆን በጣም እየጠበቀ በመጣው የባንኮች ውድድር ውስጥ መትረፍ የሚችለው እጅግ የጠነከረው ብቻ ይሆናል፤›› ይላል የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት፡፡ 

ሪፖርቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሲገልፀው ‹‹ከትልልቅ ችግሮች ተርፎ በኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት ወዲህ እጅግ አስፈላጊው የልማት ባንክ (Ethiopia’s only systemically important Bank)›› ይለዋል፡፡ 

በአንፃሩ ከ2017 ዓ.ም. ጀምሮ በመካከለኛና ትንሽ ዘርፍ ስር ያሉት ባንኮች ከብድር፣ ሀብት፣ ተቀማጭ፣ ካፒታልና ተያያዥ አመላካቾች አንፃር ከዘርፉ ያላቸው ጥመርታ እያነሰ መምጣቱን ሪፖርቱ ያትታል፡፡ በዚህም ምክንያት በተለይ ትንንሽ ባንኮች ለመዋሃድ እያጤኑ መሆናቸውን ሪፖርቱ ገልጿል፡፡ ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ የባንኮችን ውህደት (Merger and acquisition) የሚመራበት መመሪያ እያዘጋጀ መሆኑን በቅርቡ አይኤምኤፍ ገልፆ እንደነበር ይታወሳል፡፡ 

ያለፈው ዓመት የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት እንደሚለው ጠቅላላ ካፒታላቸው ከ10 ቢሊዮን ብር የተሻገሩ ባንኮች አዋሽ፣ ዳሸን፣ አቢሲንያ፣ የኦሮሚያ ኮፕሬቲቭ ባንክ፣ ፀደይ ባንክ እና ንብ ባንክ ናቸው፡፡ አብዛኛው የመጀመሪያ ትውልድ የሚባሉት ባንኮች በመካከለኛ ዕድገት ደረጃ ላይ ሲሆኑ ከ2000 ዓ.ም. ወዲህ ከተቋቋሙት ባንኮች ውስጥ የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ (CBO) ብቻ ከጠንካራዎች እንደሚመደብ ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡ 

እስካለፈው ሰኔ 2017 ዓ.ም. ድረስ የንግድ ባንኮች ጠቅላላ ሀብት በ44 በመቶ በማደግ 5 ትሪሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ጠቅላላ ብድር ቦንድን ጨምሮ 3 ትሪሊዮን ደርሷል፡፡ ጠቅላላ ተቀማጭ በ40 በመቶ አድጐ 3.5 ትሪሊዮን ደርሷል፡፡ የተበላሸ ብድር ጥመርታ 3.1 ከመቶ ነው፡፡ ጠቅላላ ገቢያቸው (በ2017 ዓ.ም. መጨረሻ) 646 ቢሊዮን ብር ሲሆን ጠቅላላ ወጪያቸው 526 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ንፁህ ትርፍ 93 ቢሊዮን ብር ሲሆን ይህም ከ2016 ዓ.ም. በእጥፍ ያደገ ትርፍ ቢሆንም በምንዛሬ ለውጡ የመጣ ነው፡፡ ከዚህም ትርፍ ውስጥ ግማሽ ያህሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡

በምንዛሬ ፖሊሲ ለውጡ ምክንያት የብር ዋጋ በ151.4 በመቶ መውረዱንም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ በምንዛሪው ምክንያት የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ በ209 በመቶ ማደጉንና የንግድ ባንኮችም የምንዛሬ ክምችት ወደ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

የትንሽ ባንኮች ያነሰ ድርሻ ሰበቡ ፣ ብድር በተወሰኑ ትልልቅ ደንበኞች መያዝ፣ የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የብድር በከተማና የንግድ ዘርፍ ላይ መከማቸት አደጋ (risk) መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጠቅላላ የባንክ ዘርፍ ሀብት ያለው ድርሻ 49.1 ከመቶ፣ ከጠቅላላ ብድርና ቦንድ ያለው ድርሻ 51.7 በመቶ፣ ከጠቅላላ ተቀማጭ ያለው ድርሻ 48.1 በመቶ፣ እንዲሁም ከባንክ ዘርፍ ካፒታል ያለው ድርሻ 43.1 በመቶ መድረሱን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

እንዲህም ሆኖ አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት አጠቃላይ የባንክ ዘርፉ በአስተማማኝና ጠንካራ መሠረት ላይ ቆሟል ሲል ይደመድማል፡፡ [ዋዜማ]