PHOTO-DW

ዋዜማ ራዲዮ- በደቡባዊ ትግራይ ኦፍላ ወረዳ አውሸራ በተባል ስፍራ በትናንትናው እለትና ዛሬ ከ80 በላይ የሚሆኑ የሕወሓት ታጣቂዎች በመከላከያ ሰራዊት እና በአማራ ክልል ልዩ ሀይል መገደላቸውን ያገኘነው መረጃ አመለከተ።

የሕወሓት ታጣቂዎች ኮረም ከተማ አካባቢ ሰፍሮ የነበረው የአማራ ክልል ልዩ ሃይልን ድንገት ለማጥቃት ሙከራ ማድረጋቸውን ተከትሎ የአማራ ክልል ልዩ ሀይል በወሰደው አጸፋ በርካታ ታጥቂዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል

የአገር መከላከያ ሰራዊት በደረሰው መረጃ መሰረት ወደ ስፍራው በመሄድ ከአማራ ክልል ልዩ ሀይል ጋር በጥምረት በወሰዱት እርምጃ ከ80 ያላነሱ የሕወሓት ታጣቂዎች ተገድለዋል ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለዋዜማ ገልጸዋል ።

የተቀናጀው የመከላከያ ሰራዊት እና የአማራ ክልል ልዩ ሀይል የሕወሓት ታጣቂዎች ወደ መሸጉበት ተከታትሎ በመግባት ጥቃት መፈጸሙን ስለጉዳዩ የሚያውቁ የመንግስት መስተዳድር አካላት ነግረውናል።

ትናንት ቅዳሜ ጀምሮ እስከ እሁድ (ዛሬ) ድረስ በከባድ መሳሪያ በታገዘ ተኩስ ከአሽንጌ ሃይቅ በስተ ምዕራብ በኩል 20 ኪሎ ሜትር ገባ ብሎ በሚገኝ ተራራማ አካባቢ በዋሻ ውስጥ ተደብቀው የነበሩ የሕወሓት ታጣቂዎች መደምሰሳቸውን እና የቡድኑ አዝዦች መማረካቸውን ምንጮቻችን ተናግረዋል። በንፁሀን ዜጎች ላይ ስለደረሰ ጉዳት የተነገረ ነገር የለም።


ከተማረኩት ውስጥ ቀደም ሲል የመከላከያ ሰራዊቱን የከዱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እንደሚገኙበትም ለማወቅ ተችሏል። አካባቢው ተራራ እና ገደላማ በመሆኑ በርካታ የሕወሓት ታጣቂዎች መሽገውበት እንደነበር ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
የፌደራል መንግስቱና የሕወሓት አማፅያን ውጊያ መጀመርን ተከትሎ በራያ ግንባር በኩል ከአላማጣ እስከ ዋጅራት ሒዋነ ድረስ ሰፍሮ የነበረው የሕወሓት ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ አብዛሀኛው ሃይል ሸሽቶ የገባው ወደዚሁ ተራራ እና ገደላማ ስፍራ ነበር።

ከአማፂው ሕወሓት በኩል ስለጉዳዩ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።


በዚህ አካባቢ ተቆርጦ የቀረው የሕወሓት ታጥቂ ቡድን ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ በሚወስደው መንገድ ከኮረም እስከ ሒዋነ ባለው መስመር የሚተላለፍውን የትራንስፖርት አገልገሎት ሲያውኩ ቆይተዋል ይላሉ ነዋሪዎቹ ።ከመሸጉበት አውሸራ አካባቢ ወደ ዋናው መስመር በመውጣት ድንገት አጥቅቶ በመመለስ ጉዳት ሲያደርሱ ነበር።

ባሳለፍነው የካቲት 11 /2013 ዓ/ም በዚያው አቅራቢያ አዲ መስኖ ከተባለች የገጠር ከተማ ወጣ ብሎ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ስድስት የአዲግራት ዩኒቨርስቲ ተመራቂ ተማሪዎች እና ሁለት የፌዴራል ፖሊሶች መገደላቸው ይታውሳል ። [ዋዜማ ራዲዮ]