ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያ ዋና ዋና አለምዓቀፍ አበዳሪዎች ያራዘሙላት የዕዳ መክፈያ ጊዜ ገደብ በቅርብ ሳምንታት ይጠናቀቃል ። ያለፉትን ዓመታት በፖለቲካ አለመረጋጋት አሁን በቅርቡ ደግሞ በጦርነት ፈተና ላይ ያለችው ኢትዮጵያ ለዚህ ዓመት የሚጠበቅባትን ከ5 ቢሊየን ዶላር በላይ ዕዳ ለመክፈል አልያም ዳግም እንዲራዘምላት ለመጠየቅ ምቹ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ቁመና ላይ አይደለችም። እንዳውም ለባዕዳኑ አበዳሪዎች ተፅዕኖ ተጋላጭ አድርጓታል። ዋዜማ ራዲዮ ስለጉዳዩ የሚከተለውን ዘገባ አሰናድታለች

ዋዜማ ራዲዮ ከታማኝ ምንጮቿ መስማት እንደቻለችውም ኢትዮጵያ የውጭ ብድር አከፋፈል ጫና እፎይታን ለማግኘትና የተያዘባትን ብድር ለማስለቀቅ ከአለም ባንክና የአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ጋር ሰፊ ውይይት እያደረገች ነው። ከእነዚህ አለማቀፍ ተቋማት ጋር እየተደረገ ባለው ውይይት ቀድሞ ለኢትዮጵያ ይቀመጡ የነበሩ ቅድመ ሁኔታዎች አሁንም ጠንክረው መቅረባቸውንም ሰምተናል።

አለም ባንክና አይኤምኤፍ ባለፈው አመት መጀመርያ አካባቢ ኢትዮጵያ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን ለመተግበር እቅዷን ይፋ ስታደርግ ቅደመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ በጥቅሉ ወደ ስድስት ቢሊየን ዶላር ብድር እንደሚሰጡ ገልጸው ነበር። ሆኖም ብድሩን ሳይለቁት ለሶስት አመታት ይተገበራል የተባለው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መተግበሪያ ጊዜ ተጋምሷል። ለኮሮና ወረርሽኝ ለግብርና እና ለማህበራዊ አገልግሎት የዓለም ባንክ ከዚህ ቀደም ቃል የገባው በመጠኑ አነስተኛ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ ቢለቅም ለኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሀግብሩ የሚጠበቀው ግዙፍ ብድር አሁንም ድንግዝግዝ ውስጥ ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ አሁን ላይ በጥቅሉ ከ30 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚልቅ የውጭ ብድር አለባት። ከዚህ ውስጥ 22 ቢሊየን ዶላሩ ከሀገራትና እና ከብዙሀን አበዳሪዎች (bilateral and multilateral) የተወሰደ ብድር ነው። 3.3 ቢሊየን ዶላሩ ደግሞ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2014 በዩሮ ቦንድ ከግል አበዳሪዎች የወሰደችውን አንድ ቢሊየን ዶላርን ጨምሮ ከሌሎች የግል አበዳሪ ተቋማት የወሰደችው ነው። 2.3 ቢሊየን ዶላሩ ደግሞ በመንግስት ዋስትና ሰጭነት እንደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አይነት ተቋማት የወሰዱት ሲሆን ቀሪው 3.3 ቢሊየን ዶላሩ ደግሞ ያለ መንግስት ዋስትና በኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ ቴሌኮም አይነት ኩባንያዎች ከውጭ አበዳሪዎች የተወሰደ ነው።

ኢትዮጵያ አሁን የገባችበት የእዳ ቅርቃር የሚጀምረው እዚህ ጋር ነው። ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው ሀገሪቱ ከአጠቃላይ 30 ቢሊየን ዶላር ብድሯ ውስጥ የአምስት ቢሊየን ዶላር ብድሩ መክፈያ ጊዜም በሚቀጥለው አንድ አመት ውስጥ ነው። ይህም ለግል አበዳሪዎችና ለአለማቀፍ አበዳሪ ተቋማት የሚከፈል እዳ ነው።

ኢትዮጵያ ይህን አምስት ቢሊየን ዶላር የመክፈል አቅሟ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ዕዳውን መክፈሏን እርግጠኝነት የጎደላት ኢትዮጵያ የቡድን ሀያ ሀገራት በኮሮና ምክንያት የኢኮኖሚ ጫና ለደረሰባቸው ሀገራት የብድር ማራዘሚያ ፕሮግራምን ለመቀላቀል አመልክታለች። ፕሮግራሙ ከአለማቀፍ ተቋማትና የግል አበዳሪዎች የተወሰደ ብድርን የመክፈያ ጊዜ ማራዘምን ይመለከታል።

የኢትዮጵያ ብድር ይራዘምልኝ ማመልከቻ ግን ለኢትዮጵያ ብድር የሰጡ የግል አበዳሪዎች በሀገሪቱ ብድር የመክፈል አቅም ላይ የነበራቸውን እምነት ሸርሽሮታል። እንደነ ፊች (Fitch) ባሉ የሀገራትን የእዳ ከፋይነት አቋም በሚመዝኑ ተቋማት የተሰጣት ደረጃ በአንዴ የወረደውም በዚህ ምክንያት መሆኑ ይታወቃል። ስታንዳርድ ኤንድ ፑር (S&P) የተባለው ሌላው የብድር አቅም መዛኝ ተቋምም ኢትዮጵያን ዝቅ አድርጎ ደረጃ ስጥቷል። የግል አበዳሪዎችም ለኢትዮጵያ የብድር መክፈያ ጊዜ እፎይታ የመስጠታቸው ነገር በእጅጉ አጠራጣሪ እንደሆነም ነው የሰማነው።

የአለም ባንክ ኢትዮጵያ በያዝነው አመት እንደተፈራው ሳይሆን 6.4 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ይኖራታል ብሏል። የአለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ግን የኢኮኖሚ ዕድገቱን ከሁለት በመቶ በታች ነው ሲል ገምቷል። ከሰሞኑ የአለም ባንክ ቀደም ሲል የነበረውን ተስፈኛ አቋም ከልሶ የሀገሪቱ ያለፉት አመታት የኢኮኖሚ ዕድገት መቀመቅ ሊወርድ ይችላል፣ ይህን ለማስቀረትም በፖለቲካዊ ጉዳዮችና በትግራዩ ቀውስ ላይ መፍትሄ ሊፈለግለት ይገባል ሲል አሳስቧል።

ኢትዮጵያ ከአለማቀፍ ተቋማት የወሰደቻቸው ብድሮች መክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላትና ተጨማሪ ብድር ለማግኘት የአለም ባንክን እና የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) መዋቅራዊ ለውጥን ለመተግበር በድርድር ላይ እንድትቀመጥ ጫና ውስጥ እንደጨመሯት ከምንጫችን ሰምተናል። አሁንም ከሁለቱ የገንዘብ ተቋማት ጋር ኢትዮጵያ እያደረገችው ባለው ውይይት፥

  • የመገበያያ ብሯን የውጭ ምንዛሬ ተመን አሁን እያደረገችው ካለው እለታዊ የማዳከም ፍጥነትም በላይ እንድታዳክምና በቅርቡ የምንዛሬ ተመኑን ለገበያ እንድትተው :
  • የመንግስት የንግድ ተቋማትን ወደግል ማዞር (ፕራይቬታይዜሽን) ሂደቱንም እንድታፋጥን :
  • የመንግስት ወጭም በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ :
  • እንዲሁም የኢትዮጵያ ወቅታዊ ቁመናንም በደንብ ለማወቅ ብዙ ጊዜ ግልጽነት የሚጎድለውን ከቻይና የወሰደችውን ብድር በዝርዝር እንዲቀርብላቸው ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠውላታል።

ከነዚህ መካከል ግን የብር የውጭ ምንዛሬ ተመንን በፍጥነት ማዳከም የሚለው ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል። የኢትዮጵያ ብር ከሀገሪቱ የንግድ ሸሪክ ሀገራት መገበያያ አንጻር አሁንም ጠንካራ ነው ብለው እነ አይኤምኤፍ ያስባሉ። ይህም ኤክስፖርትን ስለማያበረታታ የሀገሪቱን እዳ የመክፈል አቅም ያዳክማል የሚል እምነት አላቸው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ይህን በተደጋጋሚ ሞክራ የወጪ ንግድ ገቢዋ ላይ ይሄ ነው የሚባል ለውጥ አላመጣም። እንዳውም የገቢ እቃዎችን በማስወደድ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትን እያስከተለባት ነው።

በትግራዩ ጦርነት ብርቱ ዲፕሎማሲያው ጫና የበረታባት ኢትዮጵያ በአበዳሪዎች ፊት ቆሞ ለመከራከር ቢያንስ ወቅቱ የደረሰውን ዕዳዋን መክፈል ይኖርባታል። ለዚህ አሁንም ተስፋ የተጣለው የአለም ባንክና የአለም የገንዘብ ድርጅት ቃል የገቡትን ገንዘብ እንዲለቁ ማግባባት ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]