ዋዜማ ራዲዮ- በኦሮሚያ ክልል ዝዋይ (ባቱ) ከተማ ከትናንት ጀምሮ በተቀሰቀሰ ብሄርን ያማከለ ግጭት ቢያንስ አስራ አንድ ሰዎች መገደላቸውን የዋዜማ ምንጮች አረጋግጠዋል።በርካታ ሰዎች ቆስለዋል፣ተፈናቅለዋል።
በሁለት ግለሰቦች መካከል የተቀሰቀሰ ፀብ ወደ ሰፊ ግጭት መቀየሩን የከተማው የፖሊስ ምንጮች ተነግረዋል።
ሌሎች እማኞች በበኩላቸው በቡድን የተደረጁ ወጣቶች በከተማዋ እየተዘዋወሩ በርካታ የሌላ ብሄር አባላትን እየመረጡ ሲደበድቡና ሲያዋክቡ ተመልክተናል ይላሉ።
ከከተማዋ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመልክተው ግጭቱ በተቀሰቀሰበት ወቅት የፖሊስ ሀይል በበቂ ባለመኖሩ አደጋውን መከላከል ሳይችል ቀርቷል።
ዛሬ ተጨማሪ ሀይል ተመድቦ መረጋጋት ለማስፈን እየተሞከረ መሆኑንም ስምተናል።
በግጭቱ በየመንደሩ ተደብቀው ያሉና ሸሽተው በመንግስት ተቋማት ግቢ ውስጥ ለተጠለሉ የምግብና የህክምና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር ነግሮናል።
በግጭቱ በርካታ በጉልበትና በንግድ ስራ የሚተደደሩ እንዲሁም በከተማዋ ለረጅም ዘመናት የኖሩ የአንድ ብሄር አባላትን “ውጡልን – እኛ እየሞትን እናንተ አትኖሩም” የሚሉ ወጣት ስልፈኞች ቤት በማቃጠልና ንብረት በማውደም ጉዳት አድርሰውብናል ይላል በስልክ ያነጋገርነው የጉዳቱ ሰላባ።
“ወጣቶቹ ሊያጠቁ የፈለጉትን ብሄር አባላት በቅጡ መለየት ስለተሳናቸው እኔ ጉዳዩ የማይመለከተኝን የመንገድ ዳር ንግድ በምሰራበት አስፓልት ላይ ደብድበው ሊገሉኝ ሲሉ የሚያውቁኝ ሰዎች አስጥለውኛል” ብሏል።