ዋዜማ ራዲዮ- ላለፉት ሁለት ዓመታት ቀውስ ያልተለየውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ አንስቶ ለመነጋገር የአሜሪካ ከፍተኛ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ እንደሚጓዝ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት አመለከተ።
የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪቃ ጉዳዮች ተጠባባቂ ረዳት ሀላፊ ዶናልድ ያማማቶ ከወራት በፊት ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር መግባባት የተደረሰባቸው የፖለቲካ ማሻሻያዎች ባለመተግበራቸው የአሜሪካ መንግስትን ቅሬታ ያስረዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝን ማሻሻልና ሁሉንም የፖለቲካ ሀይሎችን ያሳተፈ ውይይት መጀመር እንዲቻል ቀደም ሲል በአዲስ አበባ በሚገኙ ዲፕሎማቶችና በመንግስት ባለስልጣናት በኩል በዝግ ውይይቶች መካሄዳቸውን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የዋዜማ ምንጮች ይናገራሉ።
በቅርቡም የአሜሪካ ኦክላህማ ግዛት ሴናተር ጂም ኢንሆ ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ደሳለኝንና የክልል ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ በሀገሪቱ ባለው የፖለቲካ ቀውስ ዙሪያ ሰፊ ምክክር ማድረጋቸው ይታወሳል።
አሁን ዶናልድ ያማማቶ የሚያደርጉት ጉብኝት በተለይ በገዥው ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረው አለመግባባት በቶሎ እልባት እንዲያገኝና ከዚህ ቀደም የቀረቡ የፖለቲካ ማሻሻያዎች እንዲተገበሩ ለማበረታታት ነው ተብሏል።
ያማማቶ በ 1997 ዓ.ም ምርጫ ወቅት የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮችን ከገዥው ፓርቲ ጋር በዝግ በማወያየት ፖለቲካዊ መፍትሄ ሲያፈላልጉ የነበሩ ዲፕሎማት ናቸው።
በጣም ምስጢረኛ ናቸው የሚባሉት ያማማቶ በአሜሪካ አስተዳደር ውስጥ በተለይ የምስራቅ አፍሪቃን ጉዳይ በጥልቀት የመረዳትና መፍትሄ የመጠቆም ብቃት እንዳላቸው ይነገርላቸዋል።
በዚህ ጉብኝታቸው በፀረ ሽብር ትብብር ጉዳዮችና በሌሎችም አጀንዳዎች ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ውይይት ያደርጋሉ።
በቀጣዩ ወር መጨረሻ ላይ የአፍሪቃ ህብረት ሊቀመንበርነቱን ከሚረከቡት የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ጋር በኪጋሊ ቆይታ የሚያደርጉ ሲሆን በኬንያና ሶማሊያም አጭር ቆይታ በማድረግ በፀጥታ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ዕቅድ እንዳላቸው ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።