ዋዜማ- የኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውስ፣ እየተባባሰ የመጣው ግጭትና የሰብዓዊ መብት ይዞታ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ፣ የተካረረ የሀሳብ ልዩነት ማስከተል መጀመሩን ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ካሰባሰበችው መረጃ ለመረዳት ችላለች።
የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አስተዳደር የኢትዮጵያን ችግር መፍታት እና “አገሪቱን በቅጡ መምራት አዳግቶታል” በሚሉና፣ “የጠቅላይ ሚንስትሩን አስተዳደር በመደገፍ ኢትዮጵያን ወደመረጋጋት ማምጣት ይቻላል” ብለው በሚያምኑ ሹማምንት መካከል የበረታ ልዩነት መኖሩን እና ወጥ አቋም ለመያዝ አለመቻሉን ተረድተናል።
የአውሮፓ ኅብረት ዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ዩታ ኡርፒላይነን ወደ አዲስ አበባ ከማቅናታቸው በፊት ከኅብረቱ የስትራቴጂ፣ ፀጥታና ደኅንነት አማካሪዎች ጋር አዲስ አበባ በሚያደርጉት ቆይታ፣ አሉታዊ አስተያየት ከመስጠት እንዲቆጠቡና ከመንግስት ጋር የመተባበር መንፈስ እንዲገነቡ ምክረ-ሀሳብ ቀርቦላቸው እንደነበረም ሰምተናል።
ኮሚሽነሯም ኢትዮጵያ ችግሯን በራሷ እንድትፈታ፣ ተጠያቂነት እና ዕርቅም እንዲሰፍን የአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ እንደሚያደርግ በአደባባይ ተናግረዋል። ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቱን ደረጃ በደረጃ ቀድሞ ወደነበረበት ለመመለስ ዝግጁ መሆኑንና ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የኢኮኖሚ ድጋፍ ሊቀጥል የሚችለውም በአገሪቱ በሚኖረው የፖለቲካ ድባብ መሻሻል ላይ ተመርኩዞ እንደሆነ ገልፀዋል።
ሌላው የአውሮፓ ኅብረት ክንፍ፣ በተለይም የውጪ ግንኙነቱ እና አንዳንድ የኅብረቱ አባል አገር የምክር ቤት አባላት፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግስት “እንዳሻው እንዲሆን መፍቀድ” ኢትዮጵያንም ሆነ አውሮፓን አይጠቅምም የሚል አቋም መያዛቸውን ሰምተናል። እንደምንጮቻችን ገለፃ ከሆነም፣ እነዚህ ወገኖች ጠንካራ የዲፕሎማሲ እና የኢኮኖሚ ጫና በማድረግ በአገሪቱ ግጭት እንዲቆም፣ ድርድር እንዲጀመር እና የእስከ ዛሬዎቹ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተመርምረው ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ አገሪቱን ያረጋጋታል ባይ ናቸው።
በአዲስ አበባ ጉብኝት ያደረጉት የአውሮፓ ኅብረት ዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ዩታ ኡርፒላይነን፣ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የአውሮፓ አገራት አምባሳደሮች ጋር በነበራቸው ውይይት ላይም፣ ይህ የኅብረቱ ውስጣዊ ልዩነት የበለጠ ጎልቶ መታየቱን ሰምተናል።
ኅላፊዋ ውይይቱን ያዘጋጁት የኅብረቱን አቋም እና ከመንግስት ጋር የነበራቸውን ንግግር ለዲፕሎማቶቹ ለማብራራት ቢሆንም፣ አንዳንድ የአኁጉሩ ዲፕሎማቶች ኅብረቱ የያዘው አቋም “የኅብረቱንም ሆነ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት ዕውን ለማድረግ አይረዳም” ሲሉ ተከራክረዋል። አንድ የውይይቱ ተሳታፊ ዲፕሎማትም፣ “አገሪቱ ያለችበት የኢኮኖሚ ቀውስ ብቻውን አሳሳቢ ተደርጎ መወሰድ ያለበት ነው፤ ይባስ ብሎም በየዕለቱ እየሰፋ የሚሄድ ግጭት አለ።” ሲሉ አምርረው መናገራቸውን ዋዜማ ሰምታለች።
በዚህ ያላበቁት ዲፕሎማቱ፣ “የፖለቲካ አስተዳደሩ ወደ ድርድር እንዲመጣ ኅብረቱ ያደረገው ሙከራ በቂ የዲፕሎማሲ ጫና ስላልተደረገ ሊሳካ አልቻለም።” ከማለታቸው ባለፈ፣ “ችግሩን በጦርነት ለመፍታት መሞከር የኢትዮጵያን አንድነት አደጋ ላይ ጥሎታል።” ያሉት እኚኹ ዲፕሎማት፣ “ታንዛኒያ ድረስ ወስደን አወያይተናል። የመንግስት ባለስልጣናቱንም በግል ደጋግመን ብንነግራቸውም፣ ዝንባሌያቸው ችግሩን በጦርነት መፍታት ላይ ያተኮረ ነው” ሲሉ መደመጣቸውን ዋዜማ ለመረዳት ችላለች።
ኮሚሽነር ዩታ ኡርፒላይነን እና ሌሎች የኅብረቱ አምባሳደሮች በበኩላቸው፣ ከኢትዮጵያ ታሪክ እና ሥነ-ልቦና አኳያ ጠንከር ያለ ጫና የሚፈለገውን ውጤት አምጥቶ ካለማወቁ በተጨማሪ፣ ባይወደው እንኳን ብዙው ሕዝብ ማዕከላዊው መንግስት ላይ እምነት አለው የሚል አቋም እንዳላቸው መረዳት ችለናል።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ማዕከላዊው መንግስት “መሪ ሚና” የማይጫወትበት መፍትሄ ማምጣት አስቸጋሪ ከመሆኑ ባለፍ፣ ማዕከላዊ መንግስቱ ይበልጥ ከተዳከመ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃ ቀንድን ወደ ትርምስ የሚከት ቀውስ ይፈጠራል የሚል ዕይታ የያዙት እነዚኽ አምባሳደሮች፣ ይኽ ከተከሰተም አውሮፓ በስደተኞች የመጥለቅለቅ አደጋ ይጠብቃታል የሚል መሟገቻ ይዘዋል።
የተሻለው መንገድ ለግጭቶች የውይይት መፍትሄ እንዲፈለግ ማበረታታት እና ለዚህም ትይዩ የኢኮኖሚ የድጋፍ ማዕቀፍ ማዘጋጀት መሆኑን ማብራራታቸውን ለማወቅ ችለናል።
በአሜሪካ በኩልም የፕሬዝዳን ጆ ባይደን መንግስት፣ የዐቢይ አህመድ አስተዳደር ላይ የበረታ ጫና ማሳደር የሚፈለገውን ውጤት የሚያስገኝ አይደለም ብሎ እንደሚያምን ሰምተናል። የፕሬዝዳንቱ የፀጥታና የደኅንነት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ቀውስ “በዲፕሎማሲ ጫና ብዛት የሚፈታ አይደለም” የሚል እምነት እንዳለው የቅርብ ምንጮች ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ከገባችበት ቀውስ መውጣት የምትችለው “አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ምክክር” ሲደረግ እና ግጭቶቹ ሙሉ በሙሉ ሲቆም እንደመሆኑ፣ አሁን ባለው የግጭት አውድ፣ ሥልጣን ላይ ያለው መንግስት መሪነቱን እንዲያጣ ማድረግ የኅይል ሚዛኑን አፈንጋጭ ፍላጎት ወዳላቸው ቡድኖች ስለሚወስደው ውጤቱን አስከፊ ያደርገዋል፤ ይኽም የከፋ ደም መፋሰስ እና ቀጠናዊ አለመረጋጋትን ያመጣል የሚል ዕይታ እንዳላቸውም ዋዜማ ለመረዳት ችላለች። ይህ ማለት ግን የዐቢይ አስተዳደር ለሚፈፅመው ጥፋት ተጠያቂ አይሆንም ማለት አይደለም የሚል አስተያየትም እንዳላቸው ሰምተናል።
በቀደመው ነሀሴ ወር የአሜሪካ የደኅንነት ተቋማት ያዘጋጁት የስጋት ትንተና ሰነድ ላይ ግን፣ በኢትዮጵያ የሚታየውን አለመረጋጋት ለመፍታት ቀዳሚ ትኩረት መሆን ያለበት ማዕከላዊው መንግስት ችግሮችን በጉልበት ለመፍታት የሚያደርጋቸውን ሙከራዎች ትቶ፣ ፖለቲካዊ መፍትሄ ላይ እንዲተኩር ጫና ማሳደር ያስፈልጋል ሲል ከመጥቀሱ ባለፈ፣ ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ወሳኝ አጋር አገር የነበረች ቢሆንም፣ የዐቢይ አስተዳደር የአሜሪካንን ጥቅሞች የሚገዳደር ዘመቻ በማድረግ ተጠምዶ ሰንብቷል ሲል ያትታል።
ሪፖርቱ በዚህም ሳያበቃ፣ በራሱ ሕዝብ እና በዓለማቀፉ ማኅበረሰብ “ሙሉ ድጋፍና ይሁንታ” የነበረው የዐቢይ አህመድ አስተዳደር አሁን ቅርቃር ውስጥ ገብቷል፤ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎችም የፀጥታ ስጋት አለ፤ ኢኮኖሚውም ክፉኛ ተዳክሟል ሲል ጠንከር ያለ ሀተታ ማቅረቡን ዋዜማ መረዳት ችላለች።
የፀጥታ መዋቅሩ በብሄር ሽኩቻ እና በተራዘመ የፀጥታ ቀውስ ዝሏል ሲል ግምገማውን የቀጠለው ይኸው የአሜሪካ የጸጥታ እና የስጋት ትንተና ሰነድ፣ ኢትዮጵያን መርዳት ካስፈለገ ያልዘገየ የዲፕሎማሲ ጫና እና ትኩረት ያስፈልጋል ሲል ምክረ-ሀሳቡን ያቀርባል።
የዋዜማ ምንጮች እንደሚሉትም፣ የአሜሪካ ኮንግረስ የውጪ ግንኙነት ኮሚቴ አባላትም ይህንን የደህንነት ተቋማቱን ግምገማ ይጋሩታል። ቢያንስ ሁለት የኮንግረስ አባላትም ወደ አዲስ አበባ አቅንተው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይን ለማነጋገር ዕቅድ እንዳላቸውም መረዳት ችለናል።
የአውሮፓና የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ መወላወል የኢትዮጵያን ስብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲመረምር በተመድ የተቋቋመው ቡድን የስራ ዘመን እንዳይራዘም ምክንያት መሆኑ ይታወሳል። በተለይ የአውሮፓ ኀብረት የመርማሪ ቡድኑ የሰራ ዘመን እንዲራዘም ለተመድ ሰብዓዊ ምክር ቤት ድጋፍ ሳይሰጥ በመቅረቱ ከፍተኛ ወቀሳ ቀርቦበታል። [ዋዜማ]
To reach Wazema Editors, please write to wazemaradio@gmail.com