Ethiopia Federal Parliament -FILE

ዋዜማ- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፌዴራል እና የክልል ሕዝብ ተወካዮች በመረጣቸው ሕዝብ አመኔታ በሚያጡበት ጊዜ ውክልናቸው ስለሚሻርበት ሁኔታ መመሪያ ማርቀቁን ዋዜማ ተረድታለች፡፡

ቦርዱ ያረቀቀው መመሪያ ሕዝብ ይወክለኛል ብሎ በመረጠው የምክር ቤት አባል ላይ አመኔታ ባጣ ጊዜ፣ “የይውረድልኝ”  ጥያቄ የሚያቀርብበትን ሁኔታና ውሳኔ የሚሰጥበትን ስርዓት ለመደንገግ ነው፡፡

መመሪያው የሕዝብ ተወካዮች ከመረጣቸው ሕዝብ የይውረድልም ጥያቄ ሲቀርብባቸው ቦርዱ በሚያካሂደው የይውረድልን ምርጫ ውጤቱ መሰረት የተሰጣቸው ውክልና እንዲነሳ ወይም እንዲጸና የሚያደርግ ነው፡፡ 

“የይውረድልን” ጥያቄ የተነሳበት የሕዝብ ተወካይ ምርጫ ክልል የሚገኙ መራጮች ያቀረቡት “የይውረድልን” ጥያቄ በቦርዱ ተቀባይነት ካገኘ፣ መራጩ ሕዝብ ውሳኔ እንዲሰጥ የይውረድልን ምርጫ እንደሚካሄድ መመሪያው ያዛል፡፡

መራጩ ሕዝብ የምክርቤትአባልከምክርቤትአባልነትመነሳትንእደግፋለሁወይምአልደግፍም”  በማለት ቦርዱ በሚያካሂደው ምርጫ ድምጽ እንደሚሰጥም ዋዜማ የተመለከተችው ረቂቅ መመሪያ ያስረዳል፡፡

ቦርዱ በሚያስፈጽመው ምርጫ ሁለት ሦስተኛው መራጭ የምክር ቤት አባሉ መነሳት አለበት የሚለውን አማራጭ ከደገፈ፣ የምክር ቤት አባሉ በምርጫ ቦርድ ተሰጥቶት የነበረው የአሸናፊነት መታወቂያ ወዲያውኑ እንዲመክን ይደረጋል።  

የምክር ቤት አባሉ የሕዝብ ውክልና በመራጩ አብላጫ ድምጽ መነሳቱ ተረጋግጦ በይፋ ከተወሰነ በኋላ፣ በተሻረው ተወካይ ምክትል የምርጫ ክልሉ ሕዝብ ተተኪ የሟሟያ ምርጫ በማካሄድ ተወካዩን ይመርጣል፡፡ 

“የይውረድልን” ጥያቄ የቀረበበት የምክር ቤት አባል በተወዳደረበት ምርጫ ክልል ተመዝጋቢ የነበረ መራጭ ድምጽ የመስጠት መብት የተሰጠው ሲሆን፣  የይውረድልን ምርጫ እንዲደረግ ውሳኔ ከሰጠበት ቀን በኋላ ባለው አራት ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንደሚካሄድ መመሪያው ያመላክታል፡፡

መራጩ ሕዝብ በሕግ በተሰጠው መብት መሰረት በተወካዩ ላይ ያለውን የአመኔታ መሸርሸር ለማረጋገጥ፣ በወከላቸው የይውረድልን ጥያቄ አቅራቢዎች በኩል ለቦርዱ ጥያቄ የማቅረብና ጥያቄውን ተፈጻሚ ማድረግ ይችላል፡፡

የይውረድልን ጥያቄ አቅራቢዎች የተወካያቸውን ከምክር ቤት አባልነት ይውረድልን የሚለውን ጥያቄ ተፈፃሚ ለማድረግ፣ የይውረድልን ጥያቄ የቀረበበት የምክር ቤት አባል በተወዳደረበት ምርጫ ክልል በመራጭነት ተመዝግበው የነበሩ 100 መራጮች የተፈራረሙበትን ማመልከቻ ለቦርዱ ማቅርብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የመራጩን ሕዝብ የይውረድልኝ ጥያቄ ለቦርዱ የሚያቀርቡ ተወካዮች በሚያቀርቡት ማመልከቻ ላይ፣ የምክር ቤት አባሉ እንዲነሳ ለመጠየቅ ያበቃቸውን ምክንያት ማቅረብ እንዳለባቸው መመሪያው አካቷል፡፡

ቦርዱ ከመራጩ ሕዝብ የሚቀርብለትን የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤት አባል የይውረድልን ጥያቄ፣እንደየቀረበበት ጊዜና እንደተቀረበው ገፊ ምክንያት መርምሮ ጥያቄውን ተቀብሎ የማስፈጸም ወይም ውድቅ የማድረግ ሥልጣን አለው፡፡

የቀረበው የይውረድልን ጥያቄ ያስነሳውን ምክንያት መሰረት በማድረግ ቦርዱ በልዩ ሁኔታ፣ ጥያቄው በምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት ላይ ጭምር ቢቀርብለት እንደሚቀበል በመመሪያው ተፈቅዶለታል፡፡ 

ይሁን እንጂ ጥያቄው በምክር ቤቱ የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን፣ እንዲሁም የመጨረሻ ዓመት የቀረበ ከሆነ እንዳግባብነቱ በቦርዱ ውድቅ ማድረግ የሚችልበት ዕድል መኖሩን በመመሪያው ላይ ተጠቅሷል፡፡

የመመሪያው ዓለማ ሕዝብ በመረጠው የምክር ቤት አባል ላይ አመኔታ በሚያጣና “የይውረድልኝ” ጥያቄ በሚያቀርብ ጊዜ፣ የሂደቱን የአፈፃፀም ሥርዓት በመደንገግ አመኔታ በማጣት ምክንያት የሚቀርብን የይውረድልን ጥያቄ ግልፅ፣ አሳታፊ እና ተአማኒ በሆነ መንገድ ምላሽ መስጠት መሆኑ ተገልጿል፡፡

 ቦርዱ ያረቀቀው መመሪያ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ቀርቦ ግልጽ ውይይት እንደሚደረግበት ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች፡፡ የጉዳዩ ቀዳሚ ባለቤት የሆኑት ፖለቲካ ፓርቲዎች የፊታችን መስከረም 30/2016 በመመሪያው ላይ ውይይት እንዲያደርጉ በቦርዱ ጥሪ እንደቀረበላቸው ተረድተናል፡፡

ስለ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 54 ንዑስ አንቀጽ ሰባት፣ “ማንኛውም የምክር ቤት አባል የመረጠው ሕዝብ አመኔታ ባጣበት ጊዜ በሕግ መሰረት ከምክር ቤት አባልነቱ ይወገዳል” በማለት ደንግጓል፡፡ 

በ1989ቱ አዋጅ መሰረት አንድ የፌዴራል ወይም የክልል ምክር ቤት የሕዝብ ተወካይ ተደጋጋሚ የስነ ምግባር ግድፈት የተገኘበት እንደሆነ፣ በሁለት ሦስተኛ በምክር ቤቱ ውሳኔ ከሕዝብ ተወካይነቱ ሊነሳ ይችላል፡፡

ዋዜማ የተመለከተችው የቦርዱ ረቂቅ መመሪያ በሰባት ምዕራፎችና በ41 አንቀጾች የተደራጀ ሲሆን፣ በመመሪያው ከተደነገጉ አሰራሮች በተጨማሪ ለአፈጻጸም ሲባል ቦርዱ ያወጣቸው የተለያዩ የምርጫ ማስፈጸሚያ መመሪያዎች እንደ አግባብነታቸው “በይውረድልኝ”  ምርጫ አፈጻጸም ላይም ተፈጻሚ እንደሚሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ከመመሪያው ጋር የሚቃረን ማንኛውም መመሪያ ወይም አሰራር በዚሁ መመሪያ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው ተመላክቷል፡፡ እንዲሁም ማንኛውም ሰው ወይም አካል የሕዝብ ተወካዮች የሕዝብ አመኔታ መመዘኛ መመሪያው የያዘቸውን ድንጋጌዎች ተግባራዊ ለማድረግ የመተባበር ግዴታ ተጥሎበታል፡፡

ቦርዱ መመሪያውን ያረቀቀው ስልጣንና ተግባሩን ለመወሰን በአዋጅ ቁጥር 1133/2011 እና በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 በተሰጠው ስልጣን ነው፡፡ እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በመራጮቻቸው አመኔታ በሚያጡበት ጊዜ ስለሚወሰድ እርምጃ በወጣው አዋጅ ቁጥር 88/1989 መሰረት መሆኑን በረቂቁ ላይ አስረድቷል፡፡ [ዋዜማ]

Wazema Editors are available on wazemaradio@gmail.com