ዋዜማ – ከትግራይ ክልል ውጪ ሆነው በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲደረግባቸው ውሳኔ በተሠጠባቸው (በአማራ እና ትግራይ ክልሎች መካከል የይገባኛል ውዝግብ ያለባቸው አካባቢዎች) የሚገኙ የምርጫ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ አለመሆኑን ዋዜማ ተረድታለች፡፡
በአወዛጋቢዎቹ አካባቢዎች ምርጫ ይደረጋል የሚል ግምት እንደሌላቸው መንግስታዊ ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል።
ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ግንቦት ወር ለማካሄድ ላቀደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከትግራይ ክልል በስተቀር በመላ አገሪቱ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28 እሰከ መጋቢት 28፣ 2018 ዓ፣ም እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ከትግራይ ክልል ውጪ ሆነው በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲካሄድባቸው በተወሰነባቸው የምርጫ ክልሎች የድምጽ ሠጪዎች ምዝገባ እስካሁን አልተጀመረም፡፡
በአማራ እና ትግራይ ክልሎች መካከል ውዝግብ ያለባቸው የወልቃይት፣ ጠለምት እና ራያ አካባቢዎች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በቀጥታ ምርጫ አካሂደው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲወከሉ ምርጫ ቦርድ ቀደም ሲል መወሠኑ ይታወሳል፡፡ ምርጫ ቦርድ የፌደሬሽን ምክር ቤት በሰጠው ውሳኔ መሠረት፣ በአምስት የምርጫ ክልሎች በቀጥታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫን እንደሚያስፈጽም ገልጦ ነበር፡፡ በእነዚሁ አካባቢዎች ሁለቱ ክልሎች ያነሱት የይገባኛል ጥያቄ እሰኪፈታ፣ ከትግራይ ክልል ውጪ ሆነው የፌደራሉ ምክር ቤት ምርጫ እንዲካሄድባቸው የተወሠነላቸው፣ የሁመራ፣ አዲረመጽ፣ ኮረም ኦፍላ፣ የጠለምት እና ራያ አላማጣ የምርጫ ክልሎች ናቸው፡፡
የምርጫ ቦርድን ውሳኔ የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪ ጌታቸው ረዳ የሚመሩት ተቃዋሚው የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ስምረት ፓርቲ (ስምረት) ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርቦ እግድ አስጥሎበት የነበረ ቢሆንም፣ ፓርቲው ‘ምርጫ ቦርድ ለውሳኔው መነሻ ያደረገው የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ከጅምሩም ሕገመንግሥታዊ አሠራሩን የተከተለ እንዳልነበር ተረድቻለሁ’ በማለት አቤቱታውን በማንሳቱ፣ ፍርድ ቤቱ በተጠቀሱት የምርጫ ክልሎች ከትግራይ ውጪ ምርጫ እንዳይካሄድ በምርጫ ቦርድ ላይ የጣለውን እገዳ ማንሳቱ ይታወሳል፡፡
በዚህ ስሱ ጉዳይ ላይ ከመጋረጃ ጀርባ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት የተሳተፉበት ተከታታይ ምክክር ሲደረግ እንደነበረና የፌደሬሽን ምክር ቤትም ሆነ የምርጫ ቦርድ ውሳኔም ችግሩን ያባብሳል፣ ለጉዳይ ፖለቲካዊ ዕልባት ይፈለግለት የሚል መስማማት ላይ መደረሱን ከመንግስታዊ ምንጮች ሰምተናል። በአወዛጋቢዎቹ አካባቢዎች ምርጫ ይደረጋል የሚል ግምት እንደሌላቸውም መንግስታዊ ምንጮቹ ነግረውናል።
ኾኖም የእገዳውን መነሳት ተከትሎ፣ በአምስቱም የምርጫ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ ሳይጀመር መቅረቱን መረዳት ተችሏል። በወልቃይት እና ጠለምት የምርጫ ክልሎች እስከ መጋቢት 21፣ 2018 ዓ፣ም ድረስ የመራጮች ምዝገባ አለመጀመሩን የአካባቢዎቹ ባለሥልጣናት ለዋዜማ አረጋግጠዋል፡፡
በተመሳሳይ የፌደራል መንግሥቱ ማዕከላዊ የጸጥታ ዕዝ (ኮማንድ ፖስት) ለቅቆ ከወጣ በኋላ በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በገቡት የራያ አካባቢ የምርጫ ክልሎችም ምንም ዓይነት የቅድመ-ምርጫ እንቅስቃሴ አለመጀመሩን ተረድተናል፡፡
ቦርዱ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት የቀሩት ቢሆንም፣ በአካባቢው ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አልተጀመረም ፡፡ ምርጫ ቦርድ በወልቃይት እና ጠለምት ምንም ዓይነት የቅድመ-ምርጫ ዝግጅት አልጀመረም ያሉት ምንጮች፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት እና የምርጫ ቦርድ ውሳኔ አፈጻጸም ላይ ጥርጣሬ እንደገባቸው ገልጸውልናል፡፡
በአማራ ክልል ሥር የተዋቀረው የወልቃይት-ሁመራ-ጠገዴ ዞን አመራሮች በጉዳዩ ላይ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረባቸውንም ሠምተናል፡፡ ለቦርዱ በአካል ቀርቧል የተባለው ይሄው ጥያቄ፣ በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ላይ የተጣለው የፍርድ ቤት እግድ ከተነሳ በኋላ፣ የመራጮች ምዝገባ ለምን አልተጀመረም? የሚል ነው ፡፡
ለቦርዱ ጥያቄ ላቀረቡት የወልቃይት-ሁመራ-ጠገዴ አካባቢ ባለሥልጣናት፣ የምርጫ ቦርድ ሃላፊዎች “በውሳኔው አፈጻጻም ላይ የምንወያየበት ጉዳይ አለ” የሚል ምላሽ እንደሠጧቸው ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ምንም እንኳ ቦርዱ ከውሳኔው በኋላ በምን ጉዳይ ላይ እንደሚወያይ የሠጠው ፍንጭ ባይኖርም፣ ቦርዱ የአወዛጋቢ አካባቢዎችን ምርጫ ከሕግ አግባብ አንጻር እየመረመረ እንደሚያስፈጽም የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ በቅርብ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጠቆም አድርገዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት በወልቃይት፣ ጠለምት እና ራያ አካባቢዎች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በቀጥታ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲወከሉ መወሠኑ፣ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ከክልሉ የተለያዩ ወገኖች በኩል ብርቱ ተቃውሞ እንደገጠመው አይዘነጋም። በአንጻሩ በአማራ ኃይሎች በኩል የቦርዱ ውሳኔ ድጋፍ እግኝቷል፡፡
የፌደሬሽን ምክር ቤት ለምርጫ ቦርድ መመሪያ የሠጠው፣ የአወዘጋቢ አካባቢዎችን የምርጫ ውክልና በተመለከተ ከወልቃይት ጠገዴ፣ ከወሎ ራያ አማራ እና ከጠለምት አማራ ማንነትና ወሠን አስመላሽ ኮሚቴዎች ጥያቄ ከቀረበለት በኋላ ነበር፡፡ ለፌደሬሽን ምክር ቤት የቀረበው ጥያቄ ምንም እንኳ የይገባኛል ጥያቄው እልባት ያላገኘ ቢሆንም፣ የአካባቢው ሕዝብ ግን በፌደራሉ ሕግ አውጪ ምክር ቤት ውክልና ማግኘት ይገባዋል የሚል ነው።
የማንነትና ወሠን አስመላሽ ኮሚቴዎቹ ይህንኑ ጥያቄ ያቀረቡት፣ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ጭምር እንደነበር ዋዜማ ተረድታለች፡፡
ምርጫ ቦርድ ከአስመላሽ ኮሚቴዎቹ ለቀረበለት ይሄው ጥያቄ፣ “በሚመለከተው አካል አስወስኑ” የሚል ምላሽ እንደሠጠ ዋዜማ የተመለከተችው ደብዳቤ ያስረዳል። [ዋዜማ]
