መንግስት ዕርዳታ እያቀረብኩ ነው ብሏል
ዋዜማ – የኢትዮጵያ መንግስት ከዕርዳታ ጥገኝነት ለመውጣት ዘመቻ በጀመረበት፣ የአሜሪካ መንግስት ከፍ ያለ የገንዘብ ድጋፍ ባቋረጠበት በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ተፈናቅለው በመጠለያ የሚገኙ ዜጎች የረሀብ ፈተና ተርጋርጦባቸዋል።
ዋዜማ በተለያዩ የተፈናቃይ መጠለያዎች ያሉ ዜጎችን ያነጋገረች ሲሆን፣ እየተባባሰ በመጣው የምግብ እጥረት የሰው ህይወት እንዳይቀጠፍ ስጋት የገባቸው ተፈናቃዮች መንግስት መፍትሄ እንዲያበጅ ተማፅነዋል።
በአማራ ክልል ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉልና እና ሶማሌ ክልሎች ባሉ በርካታ የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለአመታት የቆዩ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ነግረውናል።
መንግስት ሀገሪቱ ከምግብ ተረጂነት መውጣቷን ለማወጅ አቅዶ እየተቀሳቀሰ ባለበት በዚህ ወቅት ተፈናቃዮች በሚኖሩባቸው መጠለያዎች እየተባባሰ ያለ የምግብ እጥረት መኖሩን ተመልክተናል። የምግብ እጥረቱ አንዱ ምክንያት ባለፉት ሶስት ወራት በመንግስታቱ ድርጅትና በሌሎች ሰብዓዊ ድርጅቶች በኩል ይሰጥ የነበረው የዕርዳታ ምግብ ሙሉ በሙሉና በከፊል በመቋረጡ ነው። የመንግስታቱ ድርጅት ለስድስት መቶ ሀምሳ ሺ እናቶችና ለሕጻናት የሚሰጠውን የአልሚ ምግብ ዕደላ ማቆሙንም ከሁለት ወራት በፊት አስታውቆ ነበር።
ሰባት መቶ ሀምሳ ሺ የጎረቤት ሀገር ስደተኞች በኢትዮጵያ ሲኖሩ የሚሰጣቸው የምግብ መጠን ወደ አርባ በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል። የዚህ ሁሉ ስበብ በሚጠናቀቀው የፈረንጆች አመት የአሜሪካ መንግስት ሶስት መቶ ዘጠና ሚሊየን ዶላር ያህል የምግብ ድጋፉን በማስቀረቱ መሆኑን ከስብዓዊ ድርጅቶቹና ከጥናት ድርጅቶች የተመለከትነው መረጃ ያመለክታል።
ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ዝርፊያና የፀጥታ ችግሮች የሰብዐዊ ድጋፍ አቅርቦቱን የበለጠ ፈታኝ አድርጎታል።
አማራክልል
በአማራ ክልል በደብረ-ብርሃን፣ በማእከላዊ ጎንደር እና በሰሜን ወሎ ዞን ጃራ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች መሰረታዊ የሚባሉ እርዳታዎች እንደተቋረጡባቸው በመግለጽ፤ በተለይም የምግብ እርዳታ ላለፉት 3 ወራት በመቋረጡ የከፋ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ዋዜማ ከተፈናቃዮቹ ሰምታለች፡፡
ደብረብርሃን
አቶ አክሊሉ ጌታቸው ነዋሪነታቸውን በደብረ-ብርሃን መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ካደረጉ ከ 5 አመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ያሉ ተፈናቃዮች አስተባባሪነት ሚናን በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ የምግብ እርዳታ ወደ መጠለያ ጣቢያው የገባው መስከረም 6 እና 7 ቀን ፤ 2018 ዓ.ም እንደሆነ የሚገልጹት አስተባባሪው፤ እርዳታው እስከገባበት ጊዜ ድረስም ከዚህ ቀደም ይሰጥ የነበረው የስንዴ፣ በቆሎ እና ዘይት ጥቅል ድጋፍ ቀርቶ የበቆሎ ዱቄት ብቻ ይሰጥ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ከ 5 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ከእነዚህ መካከል 4 መቶ 43 የሚሆኑት እንደ ልብ መንቀሳቀስ የማይችሉ አረጋውያን ፣ 1 መቶ 88 አካል ጉዳተኞች እንዲሁም ነፍሰ-ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች እንደሚገኙበት አስረድተዋል፡፡
‹‹አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን እና ነፍሰ-ጡሮቹ ተንቀሳቅሰው መስራት አይችሉም፤ አሁን ባለንበት ሁኔታ ቁጭ ብለው ሞታቸውን ነው የሚጠባበቁት፤ ርሃብ በአንድ ጊዜ አንፈራፍሮ ባይገድልም ቀስ በቀስ ህይወት መንጠቁ አይቀርም›› ብለዋል፡፡
በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ከመንግስትም ሆነ ከሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች የሚደረግ የምግብ ድጋፍ እንደሌለ የገለጹት አቶ አክሊሉ፤ ‹‹ጉልበት ያለው የቀን ስራ ሰርቶ ካገኘ ለሌላው እያካፈለ ነው ኑሮ እየተገፋ ያለው›› በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል፡፡
2017 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በዚሁ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች እንዲመለሱ ቢጠየቁም፤ ባላቸው የደህንነት ስጋት ምክንያት ወደ ቀደመው መኖሪያቸው ለመመለስ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው እርዳታ የተከለከሉበት ሁኔታ እንደነበርም አቶ አክሊሉ ነግረውናል ፡፡
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሌላኛው በመጠለያው የሚገኙ ተፈናቃይ በበኩላቸው፤ ከተፈጠረው የምግብ እጦት ባሻገር ዘላቂ መፍትሄ እስከሚበጅ ድረስ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሁም የስራ እድል ፈጠራ ላይ መሰራት እንዳለበት ጠቅሰው፤ ‹‹አሁን ባለው ሁኔታ ግን ወጣቱ እድሜውን እዚሁ እየፈጀ ነው›› በማለት ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሰሜንወሎ
በሰሜን ወሎ ዞን ጃራ መጠለያ ጣቢያም የምግብ እርዳታ ከተቋረጠ ከ 3 ወራት በላይ ማስቆጠሩንና ለዚህም አንዱ ምክንያት የትራንስፖርት ችግር መሆኑ እንደተገለጸላቸው ተፈናቃዮቹ ተናግረዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ምግብን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ እያደረጉላቸው ቢቆዩም፤ ‹‹አሁን ላይ ግን ህዝቡም ሰልችቶታል›› ይላሉ፡፡
ጎንደር
በማእከላዊ ጎንደር ዞን ‹‹አዘዞ ቀበሮ ሜዳ›› ተብሎ በሚጠራው የመጠለያ ጣቢያም ወደ 2 ሺህ 25 የሚጠጉ ከትግራይ፣ ከኦሮሚያ ምስራቅ ወለጋ እና ምእራብ ሸዋ እንዲሁም ከቤንሻንጉል የመጡ ተፈናቃዮች ያሉ ሲሆን ከጭልጋ፣ ዳንሻ እና ማይካድራ ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች በጥቅምት ወር፤ 2017 ዓ.ም እንዲመለሱ በመደረጉ የተፈናቃዮች ቁጥር በተወሰነ መልኩም ቢሆን መቀነሱን ዋዜማ ተረድታለች።
በአሁኑ ወቅት በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ከመኖሩ በተጨማሪ የውሃ መስመር ላይ ብልሽት በማጋጠሙ አሳሳቢ በሚባል ደረጃ የውሃ ችግር ተፈጥሯል ተብሏል፡፡
‹‹በቀን ለአንድ ጀሪካን ከ25 እስከ 30 ብር እየከፈሉ ነው›› ያሉት ተፈናቃዮቹ፤ የክልሉ መንግስት መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
በእዚሁ መጠለያ ጣቢያ ያሉ ሌሎች ተፈናቃዮችም የምግብ እርዳታ ካገኙ 3 ወራት እንዳለፉ በመጥቀስ፤ ‹‹ከሰሞኑ ሰው እንዳይሞትብን በጣም ፈርተናል›› በማለት ስጋታቸውን አጋርተዋል፡፡
ጉዳዩ የሚመለከታቸው የአማራ ክልል የዞን እና የከተማ ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶችን ምላሽ ለማካተት ዋዜማ ለሳምንታት የስልክ ሙከራ ብታደርግም ሃላፊዎች ስልክ ባለማንሳታቸው አልተሳካም፡፡
የአማራ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሠርክአዲስ አታሌ፤ በጉዳዩ ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ‹‹ይህ የተዛባ መረጃ ነው፤ ሰፋ ያለ መረጃ እሰጥበታለሁ›› ቢሉም ለሳምንታት ስልክ ሳይመልሱ ቀርተዋል፡፡
ምክትል ኮሚሽነሯ የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን 5 ሺህ 404 ሔክታር መልማቱን እና የደረሰው ሰብልም እየተሰበሰበ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህም 216 ሺህ 160 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ መናገራቸውን ኢዜአ ከቀናት በፊት ዘግቧል፡፡
ምርቱ የለማው ክልሎች ሰብዓዊ ድጋፍን በራሳቸው አቅም እንዲሸፍኑ በተላለፈ ውሳኔ መሰረት እንደሆነም አክለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ባጋጠመው የገንዘብ ድጋፍ መቋረጥ ምክንያት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች እና ስደተኞች የሚያደርገውን የምግብ እርዳታ በከፍተኛ መጠን የሚቀንስ በመሆኑ የተፈናቃዮች ህይወት አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል በፈረንጆቹ ጥቅምት 10 ፤ 2025 አሳውቋል፡፡
በሃገሪቱ 27 መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚያደርገውን የ60 በመቶ ድጋፍ ወደ 40 በመቶ ዝቅ ለማድረግ መገደዱን ጠቅሶ፤ ለቀጣዮቹ 6 ወራት 230 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልገኛል ብሏል፡፡ይኸው የገንዘብ ድጋፍ መቋረጥ ከቀጠለ የሚያደርገውን የምግብ እርዳታ ሙሉ በሙሉ ሊያቋርጥ እንደሚችልም ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡
ትግራይ
ከሁለት አመታት በላይ የተካሄደውን የሰሜኑ ጦርነት ተከትሎ ከፍተኛ ተፋናቃዮች የሚገኙበት ትግራይ ክልል ጉዳይም አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል። ዋዜማ ያነጋገረቻቸው በተምቤን ዓብይ ዓዲ እና መቐለ 70 ካሬ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች እንዳሉት፤ ከ 4 አመታት በላይ በመጠለያ ጣቢያዎቹ ውስጥ የቆዩ ሲሆን በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።
በጣቢያው ውስጥ ለመጠለያነት ከተወጠረው ድንኳን አለመቀየር አንስቶ፣ የምግብ፣ የህክምና እና መድሃኒት እጥረት እየተፈራረቁ ተፈናቃዮችን ለሞት እየተዳረግን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ያሰማሉ። “ስለችግሩ አሳሳቢነት ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ተደጋጋሚ ስሞታ ብናቀርብም ሰሚ አጥተናል” ሲሉ ተናግረዋል።
በተለይም በመቀለ 70 ካሬ መጠለያ ጣቢያ ባለፈው 1 አመት ውስጥ 73 ሰዎች በምግብና ህክምና እጦት ሳቢያ ለህልፈት መዳረጋቸውን የተናገሩት ተፈናቃዮች፣ የእርዳታ መቋረጥ ለከፋ ችግር እንዳጋለጣቸው ገልፀው ፤ ተወካዮቻቸውን ወደ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በተደጋጋሚ መላካቸውን ጠቁመዋል።
ከምግብና መድሃኒት እጦቱ በተጨማሪ የዱር እንስሳት በብዛት ወደ መጠለያው የሚመጡ መሆናቸው ለደህንነታቸው አስጊ እንደሆነባቸው በመጥቀስ፤ ባለፉት 5 ወራት ብቻ 2 ከ 5 አመት በታች የሆኑ ህፃናት በጅብ መበላታቸውን አስረድተዋል።
“ሜዳ ላይ ወድቀን ስለ እኛ ግድ የሚሰጠውም ሆነ ሃላፊነት የሚሰማው አካል የለም፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩም የማይተገብረውን ቃል እየገባ እስካሁን አቆይቶናል፣ በየቀኑ ሞትን እየተጋፈጥን ነው” ሲሉም ወቅሰዋል።
ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ መነጋገሪያ የሆነው በክልሉ ሰሜን ምእራባዊ ዞን አስገደ ወረዳ የሚገኘው ህፃፅ መጠለያ ጣቢያ ከሌሎቹ የመጠለያ ጣቢያዎች በበለጠ ከፍተኛ ሞት የተመዘገበበት እንደሆነ ዋዜማ በመጠለያው የተፈናቃዮች አስተባባሪ ከሆኑት አቶ ሃጎስ ግርማይ ሰምታለች።
ለበርካታ አስርት አመታት ለኤርትራውያን ስደተኞች መጠለያነት ሲያገለግል የቆየው ይኸው ስፍራ ፤ ከመስከረም ወር ጀምሮ ወደ 80 የሚጠጉ ሰዎች ህይወት ማለፉን ተናግረዋል፡፡
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ባሉት 5 አመታት ውስጥ በአጠቃላይ 330 ሰዎች በምግብ እጦትና ተያያዥ ችግሮች ሳቢያ መሞታቸውን በመጥቀስ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ብዛት ያላቸው ተፈናቃዮች ከሞት አፋፍ እንደሚገኙ ነው ያስረዱት፡፡
በዚሁ የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ህይወታቸው ያለፈ ተፈናቃዮች አሃዝ ከፍተኛ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጹም፤ በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት አረጋውያን በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡
ከጦርነቱ በፊት በትግራይ ክልል ስር የነበረውና አሁን ላይ በአማራ ክልል ስር የሚገኘው ምእራብ ትግራይ አካባቢዎች የተፈናቀሉ መሆናቸውን የሚገልጹት አስተባባሪው፤ በመንግስት በኩል የሚደረግላቸው ድጋፍ እንደሌለ ነው የገለጹት፡፡
የማሽላ ድጋፍ የሚደረግባቸው አንዳንድ ጊዜያት ቢኖሩም ጥራት የሌለውና ለጤና ጎጂ እንደሆነ የገለጹት ተፈናቃዮቹ፤ የክልሉ መንግስት አይቷቸው እንደማያውቅ ተናግረዋል።
ችግሩ ከቀናት በፊት በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ትኩረት ካገኘ በኋላ ግን የክልሉ መንግስት እንደጎበኛቸውና ሌሎች ግለሰቦችና ተቋማት ርብርብ እያደረጉ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ የ
ኢትዮጲያ የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዶ/ር አለማየሁ ወጫቶ ችግሩ ከክልሉ አቅም በላይ መሆን አለመሆኑ መረጋገጥ እንዳለበት ለአንድ የሃገር ውስጥ ሚድያ ተናግረዋል። ሆኖም ኮሚሽኑ ታህሳስ 16 ቀን፤ 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፤ ለተፈናቃዮች ድጋፍ እየተደረገላቸው አይደለም የሚለው መረጃ የተሳሳተ ነው ብሎ፤ ከዘንድሮ መስከረም ወር ወዲህ ብቻ 257 ሚሊየን ብር የሚገመት ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ሳይቆራረጥ ማቅረቡን አሳውቋል።
በትግራይ በሕጻጽ ጊዜያዊ መጠለያ ለተፈናቃዮች የሚቀርበው የምግብ እርዳታ እንዳልተቋረጠና ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳልደረሳቸው ተደርጎ ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሠራጨው መረጃ “የተሳሳተ” እና “የመጠለያ ጣቢያውን አጠቃላይ ሁኔታ የማይገልጽ” ነው ያለው ኮሚሽኑ፣ ሕጻጽን ጨምሮ “በመደበኛነት ዓመቱን ሙሉ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው” ወገኖች የምግብ ሥርጭት ሳይቆራረጥ እየደረሠ ይገኛል ብሏል። በሕጻጽ ባለፉት አራት ወራት ለ14 ሺሕ 413 ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉንም ኮሚሽኑ ገልጧል። ኮሚሽኑ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ለተፈናቃዮች ተጨማሪ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ቢያሳውቅ ኖሮ፣ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁነት እንደነበረውም አውስቷል።
ኦሮሚያ
በኦሮሚያ ክልል ያለው ሁኔታ ግን በአማራና ትግራይ ክልሎች ክልሎች ካለው ሁኔታ የተለየ ነው። በክልሉ ውስጥ የተደራጁ የመጠለያ ጣቢያዎች ብዙ አይደሉም። ይልቁንም በየጊዜው በግጭት እና በድርቅ ምክንያት የሚፈናቀሉ ሰዎች በትምህርት ቤቶች፣ ጎዳናዎች፣ ዘመድ ቤት ተጠግተው ለመጠለል እንደሚገደዱ የእርዳታ ድርጅት ሰራተኞች ነግረውናል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስትም ለአደጋ ለተጋለጡ ዜጎች ምላሽ ለመስጠት ፈጣን እርምጃዎች በመውሰድም የተሻለ መሆኑን የረድዔት ሰራተኞች ይናገራሉ።
ከሌሎቹ የክልሉ አካባቢዎች አንፃር የተሻለ ነው የሚባለው በምስራቅ ቦረና ዞን ዱብሉቅ ወረዳ የሚገኘው መጠለያ ጣቢያ ውስጥ 10 ሺህ 582 ተፈናቃዮች የሚገኙ ሲሆን አብዛኞቹ በድርቅ ምክንያት የተፈናቀሉና 4 አመታትን ያስቆጠሩ ናቸው። [ዋዜማ]
