- ከአምስት ዓመት በኋላ መለያ ቁጥር መያዝ ግዴታ ይሆናል።
ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት አገልግሎት መስጠት የጀመረው ብሄራዊ መታወቂያ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ለአንድ መቶ ሺ ዜጎች የመታወቂያ ምዝገባ (የመለያ ቁጥር) አገልግሎት ሊሰጥ መዘጋጀቱን ዋዜማ ከመስሪያ ቤቱ ስምታለች።
አንድ ግለሰብ ብሄራዊ መታወቂያ መውሰድ የሚችለው ማንነቱን የሚገልጽ መደበኛ መታወቂያ በመያዝና የእጅ ጣት አሻራ፣ የዐይን አሻራና የፊት ገፅታን (ፎቶ) በመስጠትና ይህንን መረጃ ስለመስጠቱም ፈቃደኝነቱን በፊርማው ሲያረጋግጥ ነው። ከታወቁት የማንነት መለያ መታወቂያዎች ለየት የሚለው የብሄራዊ መታወቂያ ልክ እንደ ሌሎች የማንነት መግለጫ መታወቂያዎች ካርድ ሳይሆን በውስጡ የግለሰቡን ሙሉ መረጃ የያዘ የቁጥር መለያ ነው፡፡
ባለፈው ዓመት በአምስት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሙከራ ተደርጎ በዚህ ዓመት ስራ የጀመረው ብሄራዊ መታወቂያ እስከ አሁን ድረስ 2, 300 ገደማ ለሚሆኑ ግለሰቦች አገልግሎት መስጠቱን የመስሪያ ቤቱ የማመከር እና የድጋፍ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በረከት ገ/ሕይወት ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡
በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ኤጀንሲ ከ10 ዓመት በፊት እንደ አንድ የስራ ክፍል የተቋቋመው ይህ ተቋም በ2012 ዓ.ም ከኤጀንሲው ተነጥሎ የወጣ ሲሆን እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ በሰላም ሚኒስተር መስሪያ ቤት ውስጥ ቆይቶ በተያዘው ዓመት ከጥቅምት ወር ጀምሮ ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ዞሯል፡፡
መስሪያ ቤቱ አገልግሎቱን በራሱ የመስጠት አቅድ እንደሌለው የተናገሩት አቶ በረከት አገልግሎቱን ለመስጠት ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ፣ ባንኮች ፣ የኢትዮ ቴሌኮም እንዲሁም በሁሉም ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የወረዳ ጽህፈት ቤቶች ይህን አገልግሎት እንዲሰጡ ዝግጅት ተደርጓል።
በውስጡ 15 ብቻ ሠራተኞችን የያዘው ይህ መስሪያ ቤት ለባለድርሻ አካላት ስልጠና በመስጠት እንዲሁም ቴክኖሎጂ በማቅረብ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ይህንን መረጃ የሚሰበስበው እና የግለሰቦችን መረጃ በኮምፒውተር ላይ እንዲሰራ የሚደርገው ሶፍትዌር የተሰራው በመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ነው፡፡
ባንኮች ተጠቃሚዎቻቸው የባንክ ሂሳብ ሊከፍቱ በሚመጡበት ጊዜ አያይዘው የብሄራዊ መታወቂያ አገልግሎት የሚሰጧቸው ሲሆን፤ወሳኝኩነቶች፣ ኢትዮ ቴሌኮም እንዲሁም የወረዳ ጽህፈት ቤቶችም አገልግሎቶችን ፈልገው ለሚመጡ ተጠቃሚዎቻቸው አያይዘው አገልግሎቱን ይሰጣሉ፡፡
ልዩ የሆነው የብሄራዊ መታወቂያ የመለያ ቁጥር ብዛት 29 ሲሆን ይህም ረዥም በመሆኑ እና ለመያዝ አስቸጋሪ በመሆኑ መስሪያ ቤቱ ቁጥሮቹን ወደ አስር ዝቅ የማድረግ ስራ እየሰራ ነው፡፡
መስሪያ ቤቱ በቀጣይ አምስት አመታት ውስጥ እራሱን ባለስልጣን መስሪያ ቤት የማድረግ እቅድ ያለው ሲሆን ባለስልጣን መስሪያ ቤት ከሆነም በኋላ ብሄራዊ መታወቂያ ተመዝግቦ መያዝ ለነዋሪዎች ግዴታ ይሆናል ተብሏል፡፡ በ2019 ዓም 70 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች አገልግቱን የመስጠት እቅድ አለው፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]