ዋዜማ ራዲዮ- በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ተይዞ ግንባታው እጅግ የተጓተተው የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ በቅርቡ የፕሮጀክቱ አንድ አካል የሆነው የማቀፊያ ግንብ መደርመሱን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ይህ የማቀፊያ ግንብ የመስንጠቅ አደጋ ገጥሞት በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲፈለግለት የፓርላማ አባላት ጭምር ጥያቄ ሲያቀርቡ የቆዩ ቢሆንም ምላሽ ባለመገኘቱ በሐምሌ ወር መገባደጃ ላይ የመደርመስ አደጋው መድረሱን ስምተናል።
ስድስት መቶ ሜትር ያህል የግንቡ አካል መሰጠቁን በመግለፅ የመፍትሄ እርምጃ እንዲወስዱ የተነገራቸው የቀድሞው የሜቴክ አመራሮች የተከሰተው የአፈር መደርመስ እንጂ የከፋ አደጋ ስለማያደርስ ሀላፊነቱን እንደሚወስዱ ሲናገሩ ቆይተዋል።
በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ ተገቢ የአፈርና አካባቢያዊ ጥናት ባለመደረጉ የተለያዩ የግንባታው ክፍሎች መዛባትና መስመጥ እየታየባቸው መሆኑን የፕሮጀክቱ ስራተኞች ነግረውናል።
አሁን የተከሰተው የማቀፊያ ግንብ መደርመስ ለረጅም ጊዜ የተጓተተውን የያዩ ማዳበሪያ ፕሮጀክት የበለጠ ሊያጓትተው ይችል እንደሆነ የጠየቅናቸው የድርጅቱ ሰራተኞች በቂ የምህንድስና ዕውቀት ስለሌለን የጉዳቱን ተፅዕኖ መናገር ይከብደናል ብለዋል።
የማዳበሪያ ፋብሪካውን የሚያሰራው ብሄራዊ የኬሚካል ኮርፖሬሽን በፕሮጀክቱ መጓተት ሳቢያ ዋናውን ብድር ሳይጨምር እስከ 2009 ድረስ ብቻ አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊየን ብር ወለድ ለመክፈል ተገዷል።
ከዚህ በኋላ ፕሮጀክቱ ቢጠናቀቅ እንኳን ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱ አጠያያቂ መሆኑንም የኬሚካል ኮርፖሬሽን ስጋቱን ይገልፃል።
ኬሚካል ኮርፖሬሽን ስልሳ በመቶ ያህል የፕሮጀክቱን ክፍያ የፈፀመ ሲሆን የፕሮጀክቱ ግንባታ ግን ከአርባ በመቶ በታች ነው። ሜቴክ ተጨማሪ ክፍያ ካልተሰጠኝ ፕሮጀክቱን ማካሄድ አልችልም በሚል ያነሳው ጥያቄም ሲያወዛግብ ቆይቷል።
በወቅቱ የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ ኮርፖሬሽኑ ላይ ለሚመጣ ተጠያቂነት እርሳቸው ብቻ ተጠያቂ መሆን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ” በተጠቀሱት ችግሮች ሁሉ መጠየቅ ካለብኝ እኔ ልጠየቅ፡፡ ከእኔ ውጪ ማንም እንዲጠየቅ አልፈልግም፡፡ እኔ የሚፀፅተኝ ነገር የለም፡፡ መታወቅ የተፈለገው ይህ ከሆነ ለዚህ ዝግጁ ነኝ፤” ብለው ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የሚቴክ ዋና ዳይሬክተሩን በማንሳት በዶ/ር ግርማ አመንቴ እንደተኳቸውም ይታወቃል፡፡ ሜቴክን የተመለከተ ተጨማሪ ዘገባ እዚህ ያንብቡ – CLICK
[ዋዜማ ራዲዮ]