- ትናንት ማምሻውን ቦሌ የባለሥልጣናት መንደር ግርግር ተፈጥሯል
- ደኅንነት መሥሪያ ቤት ባልደረቦች መሐል አለመግባባት እንዳለ እየተነገረ ነው፡፡
- ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ትናንት ሊሰጠው የነበረውን መግለጫ ተሰርዟል
- ዛሬ ረፋድ ላይ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ጌታቸው አምባዬ ከጋዜጠኞች ጋር ይገናኛሉ
ዋዜማ ራዲዮ- በከፍተኛ ሙስና ተጠርጥረው የሚታሰሩ የመንግሥት ኃላፊዎች ቁጥር ወደ 40 ማሻቀቡን ተከትሎ ትናንት ማምሻውን ቦሌ ኖቪስ ራማዳ ሆቴል ጀርባ በልዩ ኃይሎች ተከቦ ነበር፡፡ ዋዜማ የሰፈሩን ነዋሪዎች የአይን እማኝነት በመንተራስ ባገኘችው መረጃ ብርበራ ለማካሄድ በመጡ የልዩ አቃቤ ሕግ ባልደረቦችና በድኅነነት መሥሪያ ቤት ባልደረቦች መሐል መነሻው ያልታወቀ አለመግባባት ተፈጥሮ ቆይቷል፡፡ ፍጥጫው በግምት ለ45 ደቂቃቆች ከቆየ በኋላ መንገዱ ለተሸከርካሪዎች ክፍት ተደርጓል፡፡ ኾኖም ዋዜማ የየትኛውም ባለሥልጣን መኖርያ ቤት ሲበረበር ይህ ችግር ሊፈጠር እንደቻለ መረጃ ማግኘት አልቻለችም፡፡
በአካባቢው እስከ አትላስ በሚዘልቀው መንገድ ወይዘሮ አዜብ መስፍንን ጨምሮ ከ12 የማያንሱ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግሥት ሹመኞች መኖርያ ቤት ይገኛል፡፡
ለደኅንነት መሥሪያ ቤት ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንደሚሉት ‹‹ቅድሚያ ማን ይታሰር፣ ማን ይቆይ›› በሚለው ጉዳይ ደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ዉስጥ ባሉ ኃላፊዎች ወጥ አቋም አይታይም፡፡ በአቃቤ ሕግና በደህንነቱ ኃይሎች መካከልም የእዝ ሰንሰለቱ ላይ መግባባቱ እምብዛምም ነው፡፡
ይህ በእንዲህ ሳለ ትናንት አርብ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በቀናት ልዩነት አዲስ መግለጫ ለመስጠት ጋዜጠኞችን ጠርተው የነበሩት የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ ጋዜጠኞች ቦታው ከደረሱ በኋላ ባልታወቀ ምክንያት መግለጫውን ሰርዘውታል፡፡ ጋዜጠኞች ከተበተኑ በኋላም የልዩ አቃቤ ሕግ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬና ባልደረቦቻቸው በተጠርጣሪዎች ጉዳይ ሰፋ ያለ መግለጫ እንደሚሰጡ ተነግሮ ጋዜጠኞች ለዛሬ ቅዳሜ አራት ሰዓት ተመልሰው እንዲመጡ ተነግሯቸዋል፡፡
ዋዜማ ባገኘቸው ሌላ ተጨማሪ መረጃ በሳምንታት ዉስጥ ከ50 የማያንሱ የነጋዴው ማኅበረሰብ አባላት የእስር ዘመቻውን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ በፋይናንስ ደህንነት መሥሪያ ቤት፣ በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በዋናው ኦዲተር እንዲሁም ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ ባልደረቦች የተውጣጣ ኮሚቴ ከ120 በላይ ነጋዴዎችን በተጠርጣሪነት በጥቁር መዝገቡ አስፍሯል፡፡ ለወራት ያህልም የሂሳብ ባለሞያዎቻቸውን በመጥራት፣ ስልካቸውን በመጥለፍ፣ ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግ መረጃ ሲያሰባስብ እንደነበር ተነግሯል፡፡ ከነዚህ መሐል በመጀመርያ ዙር የእስር ማዘዣ ይወጣባቸዋል ተብለው የሚገመቱት 18 የሚሆኑ ከፍተኛ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ የብዙዎቹ ክስ ከታክስ ስወራ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡