ዋዜማ- ከ10 ወራት በፊት የሀገሪቱ የህክምና ባለሙያዎች የመብትና የስራ ላይ የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች አንስተው መንግስት ምላሽ እንዲሰጣቸው ሲሟገቱ ነበር። አስከትለውም ግንቦት ወር ላይ ሀገር አቀፍ አድማ በማድረግ በመንግስት ላይ ግፊት ለማድረግ ሞክረዋል። መንግስት የባለሙያዎቹን ጥያቄዎች በሂደት እንደሚፈታ በመናገር ጉዳዩን ለማርገብ ከመሞከር ጎን ለጎን አድማ ያደረጉና ያስተባበሩ ባለሙያዎች ላይ የእስርና ማስፈራራት እርምጃዎችን ወስዷል። መንግስት ከአድማው ጋር በተያያዘ ወንጅሎ ያሰራቸውን ባለሙያዎች ቀስ በቀስ ከእስር ለቋል።
አድማው ከበረታ በኋላ መንግስት ባለሙያዎች ላነሷቸው 12 ያህል ጥያቄዎች በደረጃ ምላሽ እንደሚሰጥ ቃል ገብቶ ነበር። ከስድስት ወራት በኋላ የህክምና ባለሙያዎቹ አንስተዋቸው ከነበሩት ጥያቄዎች ምን ያህሉ ምላሽ አገኙ? ብለን አድማውን ካስተባበሩና ከተሳተፉ ባለሙያዎች፣ ከህክምና ተቋማት አመራሮች ጋር ዋዜማ ውይይት አድርጋለች።
ከአድማው በኋላ የተመለሱ ጥያቄዎች መኖራቸውን፣ አንዳንዶቹም በአጭር ጊዜ ይፈታሉ ብለው እንደሚጠብቁ፣ አንዳንድ ጥያቄዎች ላይ ግን መንግስት ምላሽ ለመስጠት ፍላጎትም ሆነ ዝግጁነት እንደሌለው መረዳታቸውን ነግረውናል። አሁንም ድረስ መንግስትና የአድማው አስተባባሪዎች ፊትለፊት ተገናኝተው ለመነጋገር አለመቻላቸውንና ጥያቄዎቻቸውን በፅሁፍ ከማስገባት ባለፈ መድረክ አለመፈጠሩን ተረድተናል።
የህክምና ባለሙያዎቹ ዋና ዋና ጥያቄዎች ምን ነበሩ?
- ከአፍሪቃ ሀገራት የሚተካከል የደመወዝ ጭማሪና ትርጉም ያለው የትርፍ ሰዓት ክፍያ
- የቤት ኪራይና የስራ ላይ በሽታ ተጋላጭነት አበል፣ ለአደጋ ለሚጋለጡ ደግሞ የካሳ ክፍያ
- ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት አልያም የትራንስፖርት አበል፣ አቅም ላላቸው ከቀረጥ ነፃ መኪና ማስገባት የሚችሉበት መብት ይከበር
- የትርፍ ሰዓት ክፍያ በሁሉም የጤና ተቋማት ደንብ ወጥቶለት እንዲተገበርና በወቅቱ እንዲከፈል
- መብታቸውን በጠየቁ የህክምና ባለሙያዎች ላይ እስር ማስፈራሪያና እንግልት የፈፀሙ የመንግስት አካላት ተለይተው ምርምርራ እንዲደረግና በህግ እንዲጠየቁ
- የህክምና ባለሙያዎችና ቤተሰቦቻቸው በግልም ሆነ በመንግስት ተቋማት ነፃ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ፣ ለውጪ ሀገር ህክምና ደግሞ መንግስት ግማሽ ወጪ እንዲሸፍን
- የህክምና ባለሙያዎች የመኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው የቤት መስሪያ መሬት እንዲያገኙ አልያም ቤት ለመግዛት የረጅም ጊዜ ብድር የሚያገኙበትን አስራር ማመቻቸት
- የጤና ባለሙያዎች በዓለማቀፍ ደረጃ ተቀጥረው ለመስራትና ሙያቸውን ለማዳበር የብቃት ምዘና ፈተና የሚሰጥበት ማዕከል በሀገር ቤት እንዲቋቋም መንግስት ሁኔታዎችን እንዲያመቻች
- የጤና ተቋማት አመራሮች በሹመት መመደባቸው ቀርቶ በሙያዊ መስፈርት በውድድር የሚመረጡበት አሰራር እንዲኖር
- የጤና ዘርፉን የተለዩ ባህሪያት በመገንዘብ የሚተዳደረው በሲቪል ሰርቪስ ስር መሆኑ ቀርቶ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም የሚሉት ይገኙበታል።
======================
የተመለሱ ጥያቄዎች
የደሞዝ ማሻሻያ
የህክምና ባለሙያዎች በተለይም ዶክተሮች የደሞዛቸው መነሻ ክፍያ ከጎረቤት ሀገራት ትይዩ ከፍ እንዲል ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም መንግስት ለሁሉም የጤና ባለሙያ መጠነኛ የደሞዝ ጭማሪ በማድረግ ምላሽ ስጥቷል። ይህን የመንግስት እርምጃ የህክምና ባለሙያዎች ከገንዘቡ መጠን ይልቅ ለጥያቄው መልስ ለመስጠት ፈቃደኝ ነቱን የገለፀበት እርምጃ ነው በሚል በበጎ ተቀብለውታል።
የትርፍ ሰዓት ክፍያና የተጨማሪ ስራ ክፍያ
ከዚህ ቀደም የትርፍ ሰዓት ክፍያ የማይከፈልባቸው፣ በወቅቱ የማይከፈልባቸውና ክፍያው እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ቅሬታ ሲቀርብበት ነበር። አሁም መንግስት በወሰደው እርምጃ የክፍያ ማሻሻያ ተደርጓል፣ ክፍያው ወቅቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከፈል አስራር ወጥቷል።
ነፃ የህክምና አገልግሎት
በጤናው ዘርፍ ለሚሰሩ ባለሙያዎች እና ከፌዴራል እስከ ታችኛው መዋቅር ላሉ የሴክተሩ ሠራተኞች ነጻ የህክምና አገልግሎት ወይም የጤና መድኅን ሽፋን ለመስጠት መንግስት ወስኖ ወደተግባር ተሸጋግሯል። ዋዜማ ከጤና ሚንስቴር ሠነድ ለመመልከት እንደቻለችው ከሆነ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት የጤና ዘርፍ ሠራተኞች፣ የትዳር አጋሮቻቸው እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ 18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆቻቸው መሆናቸውን ያብራራል።
=================
መንግስት እስካሁን ያልመለሳቸው ጥያቄዎች
የተጋላጭነት ክፍያ
የህክምና ባለሙያዎች በስራ ላይ ለሚያጋጥሟቸው የአደገኛ ተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭነት የካሳም ሆነ የአገልግሎት ክፍያ እስካሁን መልስ አላገኘም።
ነፃ ትራንስፖርት
የህክምና ባለሙያዎች ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ አቅም ላላቸው ደግሞ መኪና ሲገዙ/ ሲያስገቡ ከቀረጥ ነፃ እንዲደረጉ ያቀረቡት እስካሁን መልስ አላገኘም።
የመኖሪያ ቤት
መንግስት ለህክምና ባለሙያዎች ነጻ የቤት መስሪያ መሬት ወይም የረጅም ጊዜ ብድር እንዲመቻች የቀረበው ጥያቄም ገና አልተመለሰም።
በሙያ ብቃት ላይ የተመሰረተ የህክምና ተቋማት አመራሮች አሿሿም እንዲኖር የቀረበው ጥያቄም መልስ ይጠብቃል። አለማቀፍ የሙያ ምዘና ፈተና የሚሰጥበት ማዕከል እንዲከፈት ማመቻቸትና የህክምና ባለሙያዎችን የስራ ቦታ ከፖለቲካና ሌሎች ተፅዕኖዎች አላቆ ምቹ የስራ ቦታ ለማድረግ የሚያስችል ማዕቀፍ ማዘጋጀትም ከባለሙያዎቹ ቀርቦ መልስ እየተጠበቀ ነው።
መንግስት ለመመለስ ዝግጁ ያልሆነባቸው ቀልፍ ጥያቄዎች
እንደህክምና ባለሙያዎቹ የጋራ አስተያየት የጤና ዘርፉ በራሱ በዘላቂነት በቂ ገቢ የሚያመነጭ በአደረጃጀቱም ሙያውን መሰረት አድርጎ የሚደራጅ እንዲሆን ይፈልጋሉ። ከነዚህ ማሻሻያዎች የመጀመሪያው እርምጃ ዘርፉን ከሲቪል ሰርቪስ አወቃቀር ማስወጣት ነው። አሁን በተያዘው መንገድ የጤናው ዘርፍ ሩቅ መንገድ መጓዝ አይችልም ብለው ያምናሉ ባለሙያዎቹ።
አሁን የተደረገው አነስተኛ የደሞዝ ጭማሪም በባለሙያዎች የተነሱትን ቅሬታዎች እስከወዲያኛው የሚፈታ ስላልሆነ፣ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመውሰድ ዘርፉን በዘላቂነት ማዘመንና ሀብት እንዲያፈራ ማድረግ ይቻላል።
የህክምና ባለሙያዎቹ ያደረጉት አድማና ተቃውሞ ፖለቲካዊ ትርጉም እንዳይሰጠውና “እንዳይጠለፍ” ብርቱ ጥንቃቄ ማድረጋቸውንና በመንግስት በኩል ግን የአድማው አስተባባሪዎችና መብታቸውን የጠየቁትን በፓለቲካ የመፈረጅና የእስር እርምጃ መውሰድ መስተዋሉን በቅሬታ ያነሳሉ።
“ቅሬታችንን ሌላ ሀገር ሄደን ማቅረብ አንችልም፤ ማቅረብ የነበረብን እዚሁ ለመንግስት ነው። መንግስት ጥያቄያችንን ለመስማት ከጅምሩ ፈቃደኛ ቢሆን ኖሮ አድማ መጥራትም ባላሰፈለገ ነበር። አሁንም መንግስት እውቅና ሊሰጠን ስለማይፈልግ ማሻሻያውን በመሰለው መንገድ አድርጓል። ቀርበን ብንነጋገር የተሻሉ አማራጮችን ለመጠቆም ዕድል ይኖረን ነበር” ይላሉ አድማውን ለ4 ወራት ሲያስተባብሩ የነበሩና በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ በትምህርት ላይ የሚገኙ ባለሙያ።
በጉዳዩ ላይ የጤና ሚኒስቴር ምላሽ እንዲሰጠን ለአንድ ሳምንት ያህል ደጅ ብንጠናም እስካሁን ምላሽ አለገኘንም።[ዋዜማ]
