ዋዜማ – ለበርካታ አመታት ባልተመለሰ ብድር ምጣኔ መናር ብሎም በብልሹ አሰራር በቀውስ ውስጥ የከረመው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከረጅም ጊዜ በኋላ ባልተመለሰ ብድር ምጣኔ ከፍተኛ የሚባል መሻሻልን ማስመዝገቡን ለዋዜማ ተናግሯል።
የባንኩ ፕሬዝዳንት ዮሀንስ አያሌው (ዶ/ር) ለዋዜማ እንደተናገሩት ባንኩ ትግራይ ክልል ውስጥ ያለው የብድር ሁኔታ ሳይካተት ያልተመለሰ ወይንም መመለሱ አጠራጣሪ የሆነው (non performing loan) ብድር ምጣኔው ወደ ዘጠኝ በመቶ ወርዷል።
የባንኮች የብድር ጤናማነትን ለመለካት በተቀመጡ መስፈርቶች መሰረት ለንግድ ባንኮች ያልተመለሰ የብድር ምጣኔ ከአምስት በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ፣ ለልማት ባንኮች ደግሞ ከ15 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ተቀምጧል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በሚቀበለው የሂሳብ ሪፖርት ማድረጊያ ስልት መሠረት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትግራይ ክልል ብድር ሳይካተት ያለበት ያልተመለሰ የብድር ምጣኔው ከተቀመጠው 15 በመቶም ዝቅ ብሎ ዘጠኝ በመቶ ሆኗል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ ዮሀንስ አያሌው( ዶ/ር) ።
የመንግስት የፖሊሲ ባንክ የሆነው ልማት ባንክ ያልተመለሰ የብድር ምጣኔው 43 በመቶ ደርሶ እንደነበር ይታወሳል። አንዳንድ ይፋ ያልተደረጉ የውስጥ መረጃዎች የተበላሸ የብድር መጠኑ 50 በመቶ ደርሶ እንደነበረም ያመለክታሉ።
“ፍጥነት ጥራትና ግልጽነት : እንዲሁም ደንበኛች ከሰራተኞቻችን ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማስተካከልና : ብድርን መክፈል የሚጠቅመው ተበዳሪውን እንደሆነ በማሳመን የመጣ ለውጥ ነው ” ያሉት የባንኩ ፕሬዝዳንት “የልማት ባንኩ ያልተመለሰ ብድር ምጣኔ መሻሻልን ያሳየው የመክፈያ ጊዜን በማራዘም ሳይሆን ብድርን በመክፈል እና በመክፈል ብቻ ነው” ብለውናል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሰጠው አጠቃላይ ብድር 73 ቢሊየን ብር ሲሆን ከዚህ ውስጥ 19 ቢሊየን ብሩ መመለሱ አጠራጣሪ ብድር ነው።ከ19 ቢሊየን ብር ብድር ውስጥ 11 ቢሊየን ብር ገደማው ወለድን ሳይጨምር ትግራይ ውስጥ ለተሰሩ ፕሮጀክቶች የተሰጠ ነው።
“በትግራይ ውስጥ ይህ ያጋጠመው በፖለቲካዊ ሁኔታ እንጂ የባንኩን የስራ አፈጻጸም የሚያሳይ አይደለም ” ያሉት ዮሀንስ አያሌው “በትግራይ ክልል ሁሉንም ባንኮች ያጋጠማቸው ችግር ነው እኛንም ያጋጠመን “ብለዋል።
የልማት ባንኩ ፕሬዝዳንት ትግራይ ጦርነት ባያጋጥም ኖሮ ምናልባትም የተሻለ ብድር የሚመለስበት እንደሆነ ፣ ምክንያቱም እሳቸው ወደ ባንኩ ፕሬዝዳንትነት ሲመጡ ትግራይ ክልል ውስጥ ፕሮጀክት ላላቸው ተበዳሪዎች ከተሰጠው ብድር ውስጥ የመመለስ ጥርጣሬ ያለበት አስር በመቶ እንደሆነና ፣ ፖለቲካዊ ችግሩ ባይከሰት ከዚህም በጣም ዝቅ ይል እንደነበርም ነግረውናል።
በክልሉ የነበሩ ፕሮጀክቶች ጥሩ አፈጻጸም የነበራቸው እንደነበሩና አሁን ሰላም መፈጠሩን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክም አቅጣጫ በመምጣቱ በክልሉ ያሉ ፕሮጀክቶችን መልሶ በማየት ወደ ጤናማ መንገድ ሊመጡ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራልም ብለዋል የልማት ባንኩ ፕሬዝዳንት።
ከትግራይ ውጪ ያልተመለሰው የልማት ባንክ ብድር ስምንት ቢሊየን ብር ሲሆን ከዚህ ውስጥ 3.5 ቢሊየን የሚሆነው በጋምቤላ ክልል ለሰፋፊ እርሻዎች ተሰጥቶ የነበረው ብድር ነው።
የቀድሞ የብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥ እንዲሁም ዋና ኢኮኖሚስት የነበሩት ዮሀንስ አያሌው የኢትዮጵያ ልማት ባንክን በመሪነት ከያዙ በኋላ ባንኩ በብዙ መሻሻሎች ውስጥ እያለፈ መሆኑ ይነገራል።
ልማት ባንክ ከዚህ ቀደም ባልተመለሰ ብድር ብቻ ሳይሆን በብድር አሰጣጥ በኩል በነበረ ብልሹ አሰራር ተደጋግሞ ስሙ ሲነሳ ነበር።
ለአንድ እርሻ መሬት ሁለት ብድርን ለሁለት የተለያዩ ተበዳሪዎች መስጠት ፣ እንደነ ኤልሲ አዲስ ያሉት ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ ብድር ያለባቸው በርካታ ኩባንያዎች ላይ በተገቢው ሁኔታ ብድር አለመሰበሰብ ፣ ብድር ሲሰጥ ተገቢውን ማስያዣ እስካለመያዝ የደረሱ ጉድለቶች ነበሩበት። ይህም ባንኩን በአንድ አመት ውስጥ እስከ አንድ ቢሊየን ብር ኪሳራ እንዲሸከም አስገድዶትም ነበር። በአንድ ወቅት “ባንኩ ይዘጋ ወይንስ አይዘጋ” የሚሉት ውይይቶች ከመንግስት በኩል እስከመነሳት መድረሱ የውድቀቱ ማሳያም ሆኖ ነበር።
ከ2013 አ.ም ጀምሮ ግን ልማት ባንኩ በተመላሽ ብድርም በትርፍም ጥሩ የሚባሉ ውጤቶችን ማስመዝገብ ጀምሯል። በተለይ ብድር ያልመለሱ ኩባንያዎች ላይ ጠንካራ አሰራር በመከተል የቻሉ እንዲመልሱ ፣ የማይችሉ ደግሞ ድርሻን ሽጠው ወደ ስራ በመግባት ወደ ብድር መክፈል እንዲመጡ ተደርገዋል።
የዚህ በጀት አመት የባንኩ የዘጠኝ ወራት ሪፖርት እንደሚያሳየውም 2.35 ቢሊየን ብር ትርፍን እንዳስመዘገበ ፣ ለሊዝ ፋይናንስ 6.5 ቢሊየን ብር ብድርን እንዳቀረበ ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። [ዋዜማ ]