ዋዜማ- በቅርቡ የቀድሞ አመራሮቹንና በርከት ያሉ አባላቱን ያጣው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ተጨማሪ ከ250 በላይ አባላቱ ፓርቲውን ለቀው መውጣታቸውን ለዋዜማ የደረሳት መረጃ ያመለክታል።

ኢዜማ ለገዥው ፓርቲ ብልፅግና ውግንና አሳይቷል፣ የተቋቋመለትን ዓላማ በሚቃረን መልኩ በዜጎች ላይ የሚፈፀሙ የስብዓዊ መብት ረገጣዎችን ከመታገል ይልቅ እንዳላየ ማለፍና መግለጫ በማውጣት ተወስኗል ያሉት አባላቱ ችግሮችን በፓርቲ ውስጥ ሆኖ ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ባለመሳካቱ ከድርጅቱ አባልነታቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።


ከፓርቲው የተነጠሉት አባላት ከአዲስ አበባ፣ ከአማራ ክልልና ከደቡብ ክልል የኢዜማ መዋቅር ውስጥ የነበሩ አመራሮችና ተራ አባላት ናቸው።


” ኢዜማ በጥቂት የሥልጣን ችሮታ በክህደት መንገድ ተጉዞ ከአላማው ስለወጣ ወደ ትክክለኛው የትግል መስመር እንዲገባ በግልም በቡድንም ውይይቶች ስናደርግ፣ ጥያቄ ስናነሳ ብንቆይም አሁን ባሉት አመራሮች ምክንያት ምንም ዓይነት ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል ተረድተናል” ይላል የለቃቂዎቹ መግለጫ።


ቀደም ሲል ኢዜማ የአባላቱን ቅሬታ መነሻ አድርጎ በተለይም ገዥው ፓርቲ ከሚመራው መንግስት ጋር ያለውን ትብ ብር በተመለከት ጥናት አድርጎ ውይይት ማድረጉን አስታወቆ ነበር


ቅሬታ አቅራቢ አባላትም በዚህ ጥናት ብዙ ችግሮች ይፈታሉ ብለው ተስፋ አድርገው የነበረ ሲሆን ውጤቱ ግን እንደተጠበቀው አልሆነም።


“ኢዜማ በቅርቡ አጠናሁት ባለው ሠነድ ካገኘው ግብዓት መነሻ አድርጎ ራሱን አርቆ በአዲስ መንፈስ ወደ ትክክለኛ ትግል ይገባል ብለን ብንጠብቅም ከሰነዱ እንደተረዳነው አሁን ያለው አመራር ለብልጽግና ፓርቲ ገደብ ባለፈ ውግንና ውስጥ መገኘቱ፣ ብልፅግናን ታግሎ ሀገር አፍራሽነቱን የማስቆም ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌለው በማስመስከሩ፣ በተጨማሪም ብልፅግና የብሔር ፓርቲ መሆኑን ስለ ራሱ የሰጠውን ምስክርነት ኢዜማ በመካድ የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ አድርጎ በሰነዱ ማሳየቱ ፖርቲው ለመሻሻል ምንም ዓይነት ፍላጎት የሌለው መሆኑን አረጋግጧል” ይላል የአፈንጋጮቹ አባላት የጋራ መግለጫ።


የኢዜማ አመራሮች በበኩላቸው ድርጅታቸው ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ሳይሆን ከመንግስት ጋር በሀገራዊ ጉዳዮች ተባብሮ እንደሚሰራ በአፅንኦት ያስረዳሉ። ከፓርቲው የለሚለቁ አባላትን በተመለከተ ኢዜማ በጥቂት አባላት መልቀቅ የሚፈርስ ፓርቲ አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ።


ከአንድ ወር በፊት አርባ አንድ የፓርቲው የቀድሞ አመራሮችና አባላት ድርጅቱን ለቀው መውጣታቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል። [ዋዜማ]