ኦሮሚያ በአስቸኳይ እንዲከፈላቸው አዟል፣ አማራ በጀት የለኝም ብሏል

ዋዜማ- የጤና ባለሙያዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ 12 ጥያቄዎችን ይዘው በሥራ ማቆም አድማ የተደገፈ እንቅስቃሴ ካደረጉ በኋላ መንግሥት ችግሩን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ መስማማቱ ይታወሳል።

ፌደራል መንግሥት ወጥነት ያለው ክፍያ እንዲፈጸም መመሪያ ቢሰጥም፤ በክልሎች ያለው የአፈጻጸም መጓደል ባለሙያዎችን እያስቆጣ ነው። ድምጻቸውን በማሰማታቸው ለእስር የተዳረጉና የከፋ እንግልት የደረሰባቸው እንዳሉም ዋዜማ ተረድታለች፡፡

የሐኪሞቹ ጥያቄ ከስምንት ወራት በኋላ

የጤና ባለሙያዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል፤ መሠረታዊ የሆነው የትርፍ ሰዓት አገልግሎት ክፍያ መቆራረጥ አንዱ ነው፡፡ 

የጤና ባለሙያዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ 12 ጥያቄዎችን ይዘው በሥራ ማቆም አድማ የተደገፈ እንቅስቃሴ ካደረጉ በኋላ ፌደራል መንግሥት ችግሩን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ መስማማቱ ይታወሳል። የደመወዝ ማሻሻያና የትርፍ ሰዓት ክፍያ (Duty payment) በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የተደረገ ቢሆንም፤ የጤና ባለሙያዎች ክፍያው ወጥነት ባለው መልኩ እየተፈጸመላቸው አለመሆኑን ለዋዜማ አስረድተዋል።

ፌደራል መንግሥት ክፍያው በአግባቡ እንዲፈጸም መመሪያ ቢሰጥም፤ በክልሎች ያለው የአፈጻጸም መጓደል ባለሙያዎችን እያስቆጣ ነው። ክልሎች ከበጀት እጥረት ጋር የተያያዘ ምክንያት በማቅረብ፤ ወጥነት የጎደለው የጤና ባለሙያዎችን የትርፍ ሰዓት ክፍያ አፈጻጸም እየተገበሩ ነው። 

የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ከታህሳስ 7 ቀን፤ 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ የትርፍ ሰዓት ክፍያ አከፋፈል መመሪያ ያወረደ ቢሆንም፤ መመሪያው በተለይም በክልሎች በአግባቡ እየተፈጸመ እንዳልሆነ እና በጤና ባለሙያዎች ላይ ከፍተኛ ቅሬታና ምሬት እየተፈጠረ መሆኑን ምንጮች ነግረውናል። 

ችግሩ በዋናነት ጎልቶ የታየው በአማራ ክልል ቢሆንም፤ እንደ ሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ኦሮሚያ ባሉ ክልሎች ተመሳሳይ ሁኔታ መኖሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የጤና ባለሞያዎች ጥያቄ በአማራ ክልል 

በአማራ ክልል በተለያዩ የጤና ተቋማት ውስጥ በማገልገል ላይ ያሉ የጤና ባለሞያዎች ፤የስድስት ወራት የትርፍ ሰዓት ውዝፍ ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸው ለዋዜማ ተናግረዋል። 

ባለሙያዎቹ ክፍያው እንዲከፈላቸው በየተቋማቸው ፊርማ አሰባስበው ጥያቄ በማቅረባቸው፤ በመንግሥት አካላት ጫና እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጸውልናል፡፡

የክልሉ መንግሥት ‹‹በጀት የለኝም›› በማለት፤ የጤና ተቋማት በራሳቸው ፍቃድ እንደየአቅማቸው እንዲከፍሉ ወይም እንዳይከፍሉ ፍቃድ ሰጥቷል። በዚህም አንዳንድ የጤና ተቋማት በአዲሱ የትርፍ ሰዓት ክፍያ አፈጻጸም መመሪያ መሰረት መክፈል ሲጀምሩ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ክፍያውን ከአዲሱ የደመወዝ ማስተካከያ በፊት በነበረው ተመን መሰረት ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡  

የክፍያ አፈጻጸሙ ወጥ ካለመሆኑ ባሻገር፤ የጤና ተቋማት በመረጡት አሰራር ጭምር እየከፈሉ መዝለቅ እንዳልቻሉ ተናግረዋል። በአዲሱ የአከፋፈል መመሪያ መሰረት የትርፍ ሰዓት ክፍያ ሲፈጽሙ የነበሩ አንዳንድ የጤና ተቋማት፤ ክፍያውን ከወራት በፊት ለማቋረጥ ሲገደዱ፣ በቀድሞው የደመወዝ ስሌት የሚከፍሉት ሌሎች የጤና ተቋማት በተቃራኒው ሳያቋርጡ ቀጥለዋል።

በክልሉ ያለው የባለሞያዎች የትርፍ ሰዓት ክፍያ አፈጻጸም ችግር እንዲስተካከል የጤና ባለሙያዎች ለወራት ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ገልጠዋል። ይሁን እንጂ እሰከ አንድ ዓመት ድረስ ክፍያ ያልተፈጸመላቸው ባለሙያዎች፤ በተለያዩ መንገዶች ድምጻቸውን በማሰማት እንዲሁም በአድማ ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ እየተንቀሳቀሱ ነው። 

ለአብነትም በምሥራቅ ጎጃም ዞን  የሚገኘው  ‹‹የሸጋው ሞጣ ጠቅላላ ሆስፒታል›› ባለሙያዎች ለተከታታይ 6 ወራት የትርፍ ሰዓት ክፍያ ያልተከፈላቸው በመሆኑ ከሁለት ሳምንታት በፊት በሆስፒታሉ በመሰባሰብ ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡ 

ይህን ተከትሎም፤ በጸጥታ አካላት ደብደባ፣ እስር እና እንግልት እንደገጠማቸው ተናግረዋል። በእለቱ 5 የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች የታሰሩ ሲሆን፤ ዳግመኛ ጥያቄ እንዳያነሱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው የተፈቱ እንዳሉም ጠቁመዋል።

በአካባቢው የተሰማራው የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች የሆስፒታሉን ጠቅላላ ሰራተኞች ስብሰባ መጥራታቸውን እና ከመሰል እንቅስቃሴ ተቆጥበው ስራቸውን የማይሰሩ ከሆነ ‹‹ችግር›› ሊገጥማቸው እንደሚችል የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ እንደሰጧቸው የገለጹልን ምንጮች፤ እንቅስቃሴውን አስተባብረዋል የተባሉ የጤና ባለሞያዎችም፤ በተናጠል ዛቻ፣ ማስፈራሪያና እንግልት እንደገጠማቸው ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኘው የመሐል ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል እንዲሁም በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኘው የደጀን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ባለሙያዎችም በመንግሥት አካላት ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል። ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ ቢያቀርቡም፤ ከዛቻ እና ማስፈራሪያ ውጪ አጥጋቢ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ነው የገለጹት፡፡

ከዚህ ቀደም የሰሩበት የትርፍ ሰአት ክፍያ ካልተከፈላቸው፤ አገልግሎቱን መስጠት እንደሚያቆሙ የሚገልጽ የበርካታ ባለሞያዎችን ፊርማ ባካተተ ደብዳቤ ማሳወቃቸውን ተከትሎም ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው ገልጠዋል።

በክልል ደረጃ የትርፍ ሰአት አገልግሎት እንዲቋረጥ አስተባብረዋል የተባሉ የጤና ባለሞያዎች የመጨረሻ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ዋዜማ የተመለከተቻቸው ደብዳቤዎች ያስረዳሉ።

የጤና አገልግሎት መስተጓጎል

የትርፍ ሰዓት ክፍያ ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ በክልሉ የህክምና አገልግሎት ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱን የገለጹት የጤና ባለሞያዎቹ፤ ብዛት ያላቸው ባለሞያዎችም ስራቸውን እየለቀቁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ይህም የአገልግሎት አሰጣጡ እንዲስተጓጎል እና ታካሚዎችም ለእንግልት እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል፡፡

በአዊ ብሄረሰብ ዞን የሚገኘው ‹‹አገው ግምጃ ቤት›› የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፤ ከነበሩት 12 የህክምና ባለሞያዎች ግማሽ ያህሉ፤ ስራቸውን ለቀው ሄደዋል። በአንዳንድ የህክምና ጣቢያዎችም የሀኪሞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በማሽቆልቆሉ አብዛኛው አገልግሎት በነርሶች ብቻ እየተሰጠ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡

የአማራ ክልል የሕክምና ማኅበር የክልሉን የጤና ባለሙያዎች የትርፍ ጊዜ ክፍያ መቋረጥና ሌሎችም ተያያዥ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ አለማግኘት፤ በክልሉ የጤና ዘርፍ ላይ ከባድ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ማኅበሩ በግንቦት ወር ለጤና ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ፤ የጤና ባለሙያዎች የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንዲከፈል በመጠየቃቸው ከመንግስት አካላት ዛቻ፣ ማስፈራሪያ እና አስተዳደራዊ ጫናዎች እየደረሱባቸው መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ምን አለ? 

በአማራ ክልል የጤና ባለሙያዎች በትርፍ ስዓት አገልግሎት ለማቆም ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ፤ የጤና ሚኒስትሯ መቅደስ ዳባ (ዶ/ር) ከጤና ባለሞያዎች ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ   ባደረጉት ውይይት፤ የትርፍ ሰዓት ክፍያ መቆራረጥና ወጥ ያልሆነ የአከፋፈል ስርአት መኖሩን አረጋግጠዋል።

ሚኒስትሯ በውይይቱ ላይ ‹‹ይከፈላችኋል ታገሱን›› በማለት የጤና ባለሙያዎች፤ የትርፍ ሰአት አገልግሎታቸውን እንዳያቋርጡ አሳስበዋል። የጤና ተቋማት አመራሮችንም፤ ‹‹ክፍያውን ሀብት አፈላልጋችሁ ክፈሉ›› ማለታቸውን ዋዜማ ከምንጮች ሰምታለች፡፡

ባለሞያዎቹ በሚኒስትሯ አቅጣጫ ተፈጻሚነት ላይ አሁንም ጥርጣሬ እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ክልሉ በጉዳዩ ላይ ክስ ቀርቦበት በፍርድ ቤት ጭምር የተላለፈበትን የመክፈል ትዕዛዝ፤ ‹‹በጀት የለኝም›› በሚል ምክንያት አለመፈጸሙን ገልጸውልናል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ያለው ሁኔታ

በኦሮሚያ ክልል ከትርፍ ስዓት አገልግሎት ክፍያ መቋረጥ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ የጤና ተቋማት ላይ ቅሬታ መኖሩ አለ። የክልሉ ጤና ቢሮ በተለያዩ መንግሥታዊ የጤና ተቋማት የትርፍ ሰዓት ክፍያ ለተጓደለባቸው ባለሙያዎች ሙሉ ክፍያቸው በአስቸኳይ እንዲፈጸም ከቀናት በፊት ጥብቅ መመሪያ አስተላልፏል።

ዋዜማ የተመለከተችው ቢሮው ለሁሉም ዞኖች የጻፈው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፤ የጤና ባለሙያዎች የትርፍ ሰዓት ክፍያ አፈጻጸም ወጥ ባልሆነ መልኩ ሲፈጸም መቆየቱን ጠቅሶ፤  በክልሉ የጤና ባለሙያዎች የትርፍ ሰዓት ክፍያ ወጥ ባልሆነና በተቆራረጠ መንገድ ሲከፈል እንደነበር ከባለሙያዎችና ከተለያዩ አካላት በሚደርሠው አቤቱታ መረዳቱን ገልጧል፡፡

ደቡብ ኢትዮጲያ

በግንቦት 2017 ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን፣ በካምባ ወረዳ የሚገኝ ሆስፒታል በትርፍ ሰአት ክፍያ ብቻ ሳይሆን፤ በደመወዝ ክፍያ መቋረጥ ጭምር አገልግሎት መስጠት አቁሞ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ በወቅቱ ሆስፒታሉ በአንድ የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ የሚሰጥ የጤና ባለሙያ ብቻ ለመስራት ተገድዶ ነበር፡፡

አለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ‹‹አምነስቲ›› ባወጣው የቅርብ ጊዜ መረጃ መሠረት፤ በአማራ ክልል አካባቢዎች፣ በሐዋሳ፣ በአርባ ምንጭና በአዲስ አበባ ዘመቻውን ያስተባብራሉ የተባሉ የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 2 መቶ 12 የሕክምና ባለሞያዎች በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር መግለጹ አይዘነጋም፡፡

አዲሱ የጤና ባለሞያዎች የትርፍ ሰአት ክፍያ መመሪያ

የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1353/2017 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ‹‹የመንግሥት ጤና ተቋማት ሠራተኞች የትርፍ ሰዓት የሚፈቀድበት ሁኔታ እና ክፍያ ለመወሰን የወጣ መመሪያ ቁጥር 1119/2018›› የተባለ መመሪያ ማውጣቱ ይታወቃል። ይህ መመሪያ በጤና ተቋማት ደረጃ በየፊናቸው ይተገበሩ የነበሩ የክፍያ መመሪያዎችን በማስቀረት፤ በመላ ሀገሪቱ ላሉ የፌደራልና የክልል የመንግሥት ጤና ተቋማት ወጥ የሆነ የትርፍ ሰዓት ክፍያ ሥርዓት መዘርጋት ዋነኛ ዓላማው ያደረገ ነው ።

መመሪያው በዋናነት በአራት መሠረታዊ ምሰሶዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ በቀዳሚነት ለአገልግሎት ጥራትና ለባለሙያው ደህንነት ሲባል አንድ የጤና ዘርፍ ሠራተኛ በአንድ ወር ውስጥ ከ2 መቶ 12 ሰዓት በላይ የትርፍ ሰዓት ሥራ እንዳይሠራ ገድቧል።

በመደበኛ የምሽት ክፍለ ጊዜ፣ በሳምንቱ መጨረሻ የእረፍት ቀናት እንዲሁም በበዓላት ወቅት ተመድበው ለሚሠሩ ባለሙያዎች (የሕክምናና የአስተዳደር ሠራተኞችን ጨምሮ) የሠራው ትርፍ ሰዓት ብዛት በ 1 ሰዓት መደበኛ የደመወዝ ስሌት ተባዝቶ በቀጥታ እንዲከፈል ይደነግጋል።

መመሪያው የሕክምና ባለሙያዎችን ብቻ ሳይሆን፣ በጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋም ውስጥ ያሉትን የአስተዳደር ሠራተኞችንም እንዲያካትት ተወስኗል፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት የሕክምና ባለሙያዎችን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ይህንን መመሪያ ቢያወጣም፤ በተግባር ግን በአማራ፣ ኦሮሚያ ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና ሌሎችም ክልሎች የሚገኙ የህክምና ተቋማት ‹‹አጋጥሞናል›› ያሉት የበጀት እጥረት መመሪያው በተሟላ ደረጃ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኗል።  [ዋዜማ]