SS WARዋዜማ ራዲዮ- በደቡብ ሱዳን የዲንቃ ጎሳ ተወላጁ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና የኑዌር ጎሳን የሚወክሉት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሬክ ማቻር ብሄራዊ አንድነት ሽግግር መንግስት ከመሰረቱ በኋላም መተማመን እንደራቃቸው ነው፡፡ በድንገተኛው ግጭት ሳቢያ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ለሁለተኛ ጊዜ ጁባን ለቀው ተሰውረዋል፡፡ ግጭቱ ዳግመኛ መቀስቀሱ የሽግግር መንገስቱን ዕጣ ፋንታ አጠራጣሪ አድርጎታል፤ ኢትዮጵያንን ጨምሮ ሌሎች ብሄራዊ ጠቅሞቻቸው የሚነካባቸው የኢጋድ ቀጠና ሀገራት እና ምዕራባዊያንም ክፉኛ ስጋት ገብቷቸዋል፡፡ ግጭቱ ለጊዜው ጋብ በማለቱ ተመልሶ እንዳያገረሽ ዲፕሎማቶች ሩጫ ላይ ቢሆኑም አንዳችም ሁነኛ መፍትሄ አልተገኘም፡፡

ቻላቸው ታደሰ ያዘጋጀውን ዘገባ በድምፅ እዚህ ያገኙታል አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ

ሁለቱ ባላንጣዎች ከአምስት ቀናት ግጭት በኋላ ተኩስ አቁም ማወጃቸው የዓለም ዓቀፉን ማህበረሰቡ ውንጀላ በመፍራት እንጂ ለሰላም ቅን መንፈስ ኖሯቸው መሆኑን የሚጠራጠሩት ወገኖች በርካቶች ናቸው፡፡ ግጭቱ ከሁለቱ መሪዎች ዕውቅናም ሆነ ፍላጎት ውጭ የተቀሰቀሰ መሆኑን የሚጠቅሱ ወገኖች ግንአሁንም የነሃሴው ሰላም ስምምነት አልሞተም፤ በቶሎ ወደ ትግብራ መግባት ብቻ ነውበማለት ተስፋቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው፡፡

ሁለቱ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች በቀላሉ የማይታዘዟቸውን አክራሪ ፖለቲከኞችና ጦር አበጋዞችን ከጎናቸው ማሰለፋቸው ለሁሉን ኣቀፍ ሰላም ስምምነት እንቅፋት መፍጠሩን ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡ በተለይ የገዥው መንግስት ኤታማዦር ሹም (ቺፍ ኦፍ ስታፍ) የሆኑት ፖል ማሎንግ የማቻርን ዓይን የማየት አንዳችም ፍላጎት የሌላቸው አክራሪ መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡ አክራሪዎቹ የጎሳ እና ንዑስ ጎሳ መሰረታቸውን እንደ ማስፈራሪያ ጭምር በመጠቀም የሁለቱን ፖለቲከኞች እጅ በመጠምዘዝ ዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ የሚፈልገው ሰላም እንዳይሰፍን እንቅፋት መሆናቸው መነገር ከጀመረ ከራርሟል፡፡

የቀጠናው መንግስታት፣ አሜሪካ፣ ቻይና እና አውሮፓ ህብረት በደቡብ ሱዳን ቀጥተኛም ይሁን ተዘዋዋሪ ብሄራዊ ጥቅሞችና ፍላጎቶች አሏቸው፡፡ ሃያላን ሀገሮች ውስጥ ውስጡን የተለያዩ አቋም መያዛቸውም ከሁለቱም ወገን ሰላም በሚያደፈርሱት ላይ በፀጥታው ምክር ቤት ጠንካራ ማዕቀቦች የመጣሉን ዕድል እያጓተተው ነው፡፡ ሀገሪቱ በነዳጅ ሃብት የበለፀገች መሆኗ ዓለም ዓቀፍ ነዳጅ ኩባንያዎችም ውስጥ ውስጡን እጃቸውን እንዲያስገቡ ማድረጉ አልቀረም፡፡

የነሃሴው ሰላም ስምምነት የጦር ወንጀል በፈፀሙት ላይ ተጠያቂነት ከማምጣትና ፍትህ ከማስፈን ይልቅ በስልጣን ክፍፍል ላይ ብቻ በማተኮሩ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ክፉኛ ሲተች ቆይቷል፡፡ ዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ ግን ሲቪልና ወታደራዊ መሪዎች በዓለም ዓቀፍ ህግ ተጠያቂ ቢሆኑ ሀገሪቱ ወደከፋ ብጥብጥ ልትገባ ትችላለች የሚል ስጋት የገባው ይመስላል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትም ሰሞኑን ቁርጥ ያለ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ተቸግሮ የሰነበተበት አንዱ ምክንያት ይኸው ነው፡፡

የፀጥታው ምክር ቤት የነሃሴው ሰላም ስምምነት ፀንቶ ሊቀጥል ይችላል ወይስ ሌላ አማራጭ መፈለግ ይሻላል? በሚለው ላይ እስካሁንም ወጥ አቋም መያዝ እንዳልቻለ እየተነገረ ነው፡፡ አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት በተቀናቃኝ ወገኖች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ሲፈልጉ ሌሎች ግን በፖለቲካዊ መፍትሄዎች መግፋት እንደሚሻል አቋም መያዛቸው ውስጥ ውስጡን ሲናፈስ ሰንብቷል፡፡

ለጊዜው የፀጥታው ምክር ቤት መፍትሄ ያለው የጁባ አውሮፕላን ማረፊያን የሚጠብቅ እና በሁለቱ ባላንጣ ሰራዊቶች መካከል ሰፍሮ ፀጥታ የሚያረጋጋ ገለልተኛ ኃይል ማስፈርን ነው፡፡ ለዚህም ተልዕኮ የኢጋድ ቀጠና መንግስታት እንዲዘጋጁ ጥሪ አድርጓል፡፡ የኢጋድ ሚንስትሮችም ሰኞ ዕለት ናይሮቢ ላይ ተሰብስበው የተመድን ሰላም አስጠባቂ ኃይል የሚያግዙ ተጨማሪ ወታደሮች እንዲሰፍሩ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡

የፀጥታው ምክር ቤትም ሆነ የኢጋድ ሚንስትሮች ይህን ይበሉንጂ ወታደር የሚያዋጣ ሀገር ማግኘት ግን ቀላል አይሆንም፡፡ የኡጋንዳ ወታደሮች በይፋ ከሳልቫ ኪር ጎን ወግነው ሲዋጉ በመኖራቸው በሰላም አስከባሪነት ሊሰለፉ አይችሉም፡፡ ከጅምሩም የደቡብ ሱዳን ባላንጣ የሆነችው ሱዳን ደሞ ለሬክ ማቻር ኃይሎች ወታደራዊ ዕገዛ በመስጠት ስለምትጠረጠር ከሳልቫ ኪር ጋር ዓይንና ናጫ ነች፡፡ በሱማሊያ ጦሯን ያሰማራችው ቡሩንዲ በበኩሏ ገና ከተዘፈቀችበት ፖለቲካዊ ቀውስ አልወጣችም፡፡ ኬንያ ደቡብ ሱዳን በፍጥነት እንድትረጋጋ አጥብቃ ብትፈልግም ሱማሊያ የሰፈረው ጦር ሰራዊቷ አልሸባብ በሚያደርስበት ተከታታይ ጥቃት ሳቢያ አጣብቂኝ ውስጥ ከገባባት ሰነባብቷል፡፡ ምናልባት ተስፋ የሚጣልበት ብቸኛዋ የቀጠናው ሀገር የኢትዮጵያ ብቻ ትመስላለች፡፡

የኢጋድ አባል ሀገራት በተለይም ሱዳን እና ኡጋንዳ ተፃራሪ ፍላጎቶች ስላሏቸው ግጭቱ ኢጋድን ዳግመኛ ሊከፋፍል ይችላል ተብሎ ተሰግቷል፡፡ የሰሞኑ ግጭት እንደገና አገርሽቶ ከቀጠለ ብዙ የተለፋበትን ሰላም ስምምነትና ሸግግር መንግስቱን በማፍረስ ቀጠናውን ትርምስ ውስጥ ሊያስገባው ይችላል፡፡ በሳምንቱ መገባደጃ ኪጋሊ ላይ የአፍሪካ ህብረት መሪዎች የህብረቱን ቀጣይ ዋና ፀሃፊ ለመምረጥ ጉባዔ የሚቀመጡ ሲሆን የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ዋነኛ መወያያቸው እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ሰራዊታቸውን ከጁባ ካስወጡ በኋላ ስፍራው ባልታወቀ ምሽጋቸው ሆነው መግለጫ እየሰጡ ያሉት ሬክ ማቻርምበሁለቱ ኃይሎች መካከል ገለልተኛ ዓለም ዓቀፍ ሰላም አስከባሪ ኃይል ካልሰፈረ ደህንነት አይሰማኝምበማለት ከፀጥታው ምክር ቤት ሃሳብ ጋር የሚጣጣም አቋም ይዘዋል፡፡ በዲፕሎማሲ ክህሎታቸውና ብልጣብልጥ ተደራዳሪነታቸው የዋዛ ያልሆኑት ማቻርየኢጋድ አባል መንግስታት ዋስትና ካልሰጡኝ ወደ ጁባ ተመልሼ ስራዬን አልጀምርምበማለት ቅድመሁኔታ ማስቀመጣቸው ያለባቸውን የደህንነት ስጋት የሚያሳይ ሆኗል፡፡ በጦር አበጋዞች ትዕዛዝ ወይም በተራ ወታደሮች ፍትጊያ ሳቢያ በድንገት ተኩስ ሩምታ በሚጀመርባት ጁባ ግን የውጭ መንግስት ይቅርና ፕሬዝዳንቱ ሳልቫ ኪር ራሳቸው ለባላንጣቸው ደህንነት ዋስትና መስጠት መቻላቸው አጠራጣሪ ሆኗል፡፡

ባንፃሩ ሳልቫ ኪር ባለፈው ሃሙስ በሰጡት መግለጫበሀገሬ ቀደም ሲል የሰፈሩ 12 ሺህ የውጭ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ስላሉ ከእንግዲህ አንድም ተጨማሪ ወታደር አልቀበልምሲሉ አስታውቀዋል፡፡ ተጨማሪ ወታደሮችን የማስፈር ጉዳይ ሁለቱን ባላንጣዎች ካሁኑ ከፋፍሏቸዋል፡፡ በግትርነታቸው የሚታወቁት ፕሬዝዳንት ኪር የሚያራምዱት አቋም ወደፊትም ቢሆን ከኢጋድ እና ከፀጥታው ምክር ቤት ፍላጎት ጋር በቀላሉ የሚጣጣም አይመስልም፡፡ሰላም ስምምነቱ በውጭ ኃይሎች ግፊት የተጫነብን ነውእያሉ ሲያማርሩ የከረሙት ሳልቫ ኪር ሁኔታዎች ከተመቻቹላቸው በማንኛውም ጊዜ ሰነዱን ቀዳደው ከመጣል እንደማይመለሱ የበርካቶች እምነት ነው፡፡

እዚህ ላይ ግጭቱ የኢትዮጵያ መንግስትን ምን ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ እንዳስገባው ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ ኢህአዴግመራሹ መንግስት ሁለቱንም ተቀናቃኝ ኃይሎች ላለማስቀየም አጥብቆ ሲጠነቀቅ መኖሩ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት ማለቂያ ከሌለው ፖለቲካዊ ድርድር ያለፈ ሌላ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ሃሳብ ያቀርባል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በጋምቤላ ክልል በርካታ ኢትዮጵያዊያን ኑዌሮችን እና ኑዌሮች የሚበዙባቸው 250 ሺህ ደቡብ ሱዳናዊያን ስደተኞች በመጠለላቸው የደቡብ ሱዳን ግጭት በፍጥነት ጎሳዊ መልክ ይዞ ወደ ጋምቤላ እንዲዛመት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በቅርቡ የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ወደ ጋምቤላ ዘልቀው ገብተው በርካታ ንፁሃን የኑዌር ጎሳ ተወላጆችን ገድለው በመቶዎች የሚቆጠሩ ህፃናትን አፍነው መውሰዳቸው ከደቡብ ሱዳን አለመረጋጋት ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት አለው፡፡ ጋምቤላ ከዚህ ቁስል ገና ሳታገግም ነው ባለፈው ሳምንት በደቡብ ሱዳን ዳግመኛ ግጭት የተቀሰቀሰው፡፡

የኡጋንዳው ሙሴቬኒምከሦስት ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎቼን ከደቡብ ሱዳን ለማስወጣት ፈልጊያለሁበሚል ጦራቸውን ሃሙስ ዕለት ወደ ጁባ ልከዋል፡፡ ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉ የደህንነት ምንጮች ግን የተወሰኑ ወታደሮች ሳልቫ ኪርን ለማገዝ ጁባ ውስጥ እንደሚቀሩ ግምታቸውን እየሰነዘሩ ነው፡፡ በርግጥም በግጭቱ ገለልተኛ የሆነቸው ኬንያተኩሱ በመቆሙ ዜጎቼን ከጁባ ማስወጣት አላስፈለገኝምእያለች ባለችበት ወቅት የጁባው መንግስት ቀኝ እጅ የሆኑት ሙሴቬኒ ለዜጎቻቸው ደህንነት ተቆርቋሪ ሆነው ብቅ ማለታቸው ጥርጣሬ አሳድሯል፡፡ ሙሴቬኒ ወታደሮቻቸው ዳግመኛ በጁባ እንዲቆዩ ካደረጉ ግጭቱ ተመልሶ ሊያገረሽ እንደሚችል ጠቋሚ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ሁለቱ ባላንጣዎች ሰኞ ዕለት ወታደሮቻቸው ተኩስ እንዲያቆሙ በማዘዛቸው ተኩሱ ረገብ ብሎ ቢሰነብትም ሁኔታውን በቅርብ እየገመገመ ያለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግን ግጭቱ ዳግመኛ አገርሽቶ ወደሌሎች ግዛቶች ሊዛመት ይችላል ሲል ስጋቱን ሲገልፅ ሰንብቷል፡፡ የስጋቱን ጥልቀት የሚሳየውም ለሰብዓዊ ዕርዳታ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ጥቂት ሰራተኞቹ ውጭ ሌሎቹን ከደቡብ ሱዳን ሲያስወጣ መሰንበቱ ነው፡፡ ጁባ የሚገኘው የዓለም ምግብ ድርጅት መጋዘን መዘረፍ እና አንዳንድ ሰራተኞቹ ላይ ጥቃት መድረሱ እንዳሳሰበውም አስታውቋል፡፡ ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያንና ጃፓንም ዜጎቻቸውን ከጁባ ለማስወጣት ሲጣደፉ መሰንበታቸው ስጋቱን አባብሶታል፡፡ የፀጥታው ማሽቆልቆል ያሳሰበው የአሜሪካ መንግስትም ባለፈው ሃሙስ ከጥቂት ዲፕሎማቶች በስተቀር ቀሪዎቹን የኢምባሲው ባልደረቦች ከጁባ ያስወጣ ሲሆን ሃምሳ የሚጠጉ ወታደሮቹንም ወዲያው ነበር ኢምባሲውን እንዲጠብቁ የላከው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በሊቢያው ኢምባሲዋ በአሸባሪዎች አምባሳደር የተገደለባት አሜሪካ 130 ወታደሮችን ጅቡቲ ላይ በተጠንቀቅ ማቆሟ የስጋቷን ደረጃ የሚያሳይ ነው፡፡

ባሁኑ ጊዜ ኪር እና ማቻር የሚያዟቸው የየራሳቸው ታማኝ ወታደሮች ስላሏቸው ባንድ ሀገር ሁለት ሰራዊት እንዲኖር አድርጓል፡፡ ይህም በየፍተሻ ጣቢያው በሰበብ አስባቡ አፈሙዝን ለማዞር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ለዚህም ይመስላል ማቻር ሰሞኑንየሁለታችንም ሰራዊቶች በአስቸኳይ ተዋህደው ወጥ ብሄራዊ ጦር እና ፖሊስ ሰራዊት ይቋቋምሲሉም ጥሪ ያቀረቡት፡፡ ሆኖም በመካከላቸው ለዓመታት የዘለቀው ጎሳን የለየ ቁርሾ ብሄራዊ ጦር ሰራዊት ምስረታውን እያወሳሰበው ነው፡፡ ጦር ሰራዊት ቅነሳ፣ ፀጥታ ኃይሎችን መልሶ ማዋቀር ወይም ወጥ ብሄራዊ ጦር ሰራዊት ምስረታ የመሳሰሉት አወዛጋቢ የስምምነቱ ክፍሎች አንዳቸውም ገና አልተሞከሩም፡፡

ለዚህም ነው አሁን አሁን የሁለቱን መሪዎች ወገብ ሊያጎብጥ የሚችል ዒላማ የለየ ዓለም ዓቀፍ ማዕቀብ ካልተጣለባቸው ሀገሪቱ ከግጭት አዙሪት ልትወጣ አትችልም የሚሉ ታዛቢዎች የበረከቱት፡፡ በርግጥም ዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ ለዘላቂ መፍትሄ ካልተሯሯጠ ደቡብ ሱዳን በዲንቃ እና ኑዌር ጎሳዎች መካከል ብቻ ሳይሆን ውላ አድራ ሌላኛዋ ሱማሊያ ልትሆን ትችላለች የሚለው ስጋት እያየለ መጥቷል፡፡

የዓለም ኣቀፍ ነዳጅ ዋጋ በማሽቆልቆሉ፣ ሱዳን በምትጥልባት ከፍተኛ ቀረጥ እና በግጭቱ ሳቢያ ነዳጅ ምርቷ በመስተጓጎሉ ሀገሪቱ ከነዳጅ የምታገኘው ገቢ ክፉኛ ተመናምኖባታል፡፡ በኬንያ ላሙ ወደብ በኩል ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ለመዘርጋት የነበራት ዕቅድም በግጭቱ ሳቢያ ተጓትቷል፡፡ ይህ ለኬንያም ራስ ምታት ሆኖባታል፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት በለም መሬቷ እና ተፈጥሮ ሃብቷ የምትታወቀው ሀገር ዜጎች በመሪዎቻቸው ልቦና ማጣት ሳቢያ ለምግብ ዕጥረት ተዳርገው ከረድዔት ድርጅቶች ቀለብ የሚሰፈርላቸው ሆነዋል፡፡ ሀገሪቱ ለገባችበት ቀውስ ሁነኛ መፍትሄ በቅርቡ ይገኛል የሚለው ተስፋም አናሳ ነው፡፡