• በአዲስ አበባ ፣ አዳማና ባህርዳር ከፍያለ ገንዘብ ተጠይቀናል አሉ

ዋዜማ- በአዲስ አበባ በተለያየ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች በማያውቁት ስልክ እየተደወለላቸው ገንዘብ እየተጠየቁ ፤ ገንዘቡን የማይሰጡ ከሆነም ለደህንነታቸው የሚያሰጋ ማስፈራርያ እየደረሰባቸው እንደሆነ ዋዜማ ካሰባሰበችው መረጃ ተረድታለች ።

አዳማና ባህርዳር ያሉ ባለሀብቶችም በታጣቂዎች ከአንድ ጊዜ በላይ ገንዘብ መጠየቃቸውን ነግረውናል። 

እየደወሉ በማስፈራርያ ገንዘብ የሚጠይቁ ግለሰቦች ፤ ባለሀብት ነው ብለው ያሰቡትን  ሰው ሙሉ አድራሻ ብቻ ሳይሆን ፤ በባንክ ውስጥ የሚያንቀሳቅሱትን ገንዘብ እና የባንክ መረጃቸውን የሚያውቁ መሆኑ ደግሞ በግለሰቦች ላይ ከፍተኛ ስጋት እየፈጠረ መሆኑን ተረድተናል ።

ለዚህ ዘገባ ሲባል ጉዳያቸውን የተከታተልነው እና ለደህንነታቸው ስማቸው እና የኩባንያቸው ስም እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ግለሰብ ፤ በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ፋብሪካ አሏቸው ሌሎች የንግድ ስራዎች ላይም ተሰማርተዋል ።

ሆኖም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በስልካቸው እየተደወለ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ እየተጠየቁ ፤ ይህን ማድረግ የማይችሉ ከሆነ ዛቻ እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል።የሚደውሉላቸው ሰዎች ግለሰባዊ ጉዳዮቻቸውን ሳይቀር የሚያውቁበት ደረጃ ስላሰጋቸውም መጀመርያ ይኖሩበት ከነበረበት ቦታ ሁለት ግዜ የመኖርያ ሰፈር እንደቀየሩም መረዳት ችለናል።ሁኔታውን በስራ እና ኑሯቸው ላይ ስጋት እንደፈጠረባቸውም ገልጸዋል ።

ሌላው ባለሀብት እንዲሁ በአዲስ አበባ በንግድ ላይ የተሰማሩ ሲሆን ፤ በተመሳሳይ በስልክ እየተደወላላቸው መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብን እየተጠየቁ እንደሆነ ያስረዳሉ። በዚሁ ሳቢያ የእጅ ስልካቸውን ለቤተሰብ አባላቸው ሰጥተው በሌላ ስልክ እንደሚጠቀሙ ይገልጻሉ ።ሆኖም ለቤተሰብም እንፈልጋቸዋለን እየተባለ እንደሚደወል ይናገራሉ ።

ለዚህ ዘገባ ጉዳያቸውን የተመለከትናችው ግለሰቦች ከሚደውሉላቸው ሰዎች ንግግር በመነሳት ገንዘብ ካላመጣችሁ ብለው የሚያስፈራሯቸው ግለሰቦችን ከንግግራቸው በመነሳት ፖሊቲካዊ አላማ ያላቸው እንደሆነ እንደሚገምቱ ይገልጻሉ ።

ከአርባ አንድ አመታት በላይ በአዳማ ከተማ ከትንሽ ስራ ተነስተው ስመጥር ባለሀብት ለመሆን የበቁና ስሞኑን ከሀገር መውጣት የቻሉ ባለሀብት እንደነገሩን ደግሞ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ያህል በአገዳጅ ሁኔታ የተጠየቁትን ስድስት ሚሊየን ብር በሚሰጥር ከፍለው የቤተሰባቸውን ደህንነት ለጊዜው ማረጋገጥ ቢችሉም በጥር ወር በድጋሚ አስር ሚሊየን ብር ካልከፈልክ የሚል ማስፈራሪያ እንደደረሳቸው ይናገራሉ። 

“ጉዳዩን ለመንግስት አካላት አስውቄ ለንብረቴ ጥበቃ እንዲደረግልኝ ተወስኖ ጠባቂዎቹ ስራ በጀመሩ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ የድርጅቴ አንድ ሚኒባስ መኪና ከግቢው ውስጥ ባልታወቀ ግለሰብ ተወስዶ ተሰወረ” ይላሉ። 

ስድስት ቤተሰቦቻቸውን ከሀገር አስወጥተው ራሳቸው ለአጭር እረፍት በውጪ ሀገር የሚገኙት ባለሀብት የኦሮምያም ሆነ ፌደራል ፖሊስ በዚህ መሰል ጉዳይ ተደጋጋሚ ጥቆማ ቢደርሳቸውም ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት አቅምም ፍላጎትም ይጎድላቸዋ ሲሉ ያስረዳሉ። 

የባንክ ብድር መክፈል ተስኗቸው ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት ሌላ የባህርዳር ባለሀብት ድግሞ ክልሉ በጦርነት ላይ በመሆኑ የተበደሩትን በወቅቱ ሰርተው መክፈል እንደተቸገሩ ያብራራሉ። 

“ባለፈው አንድ አመት ሶስት ታጣቂ ቡድኖች ከፍያለ ገንዘብ እንድሰጣቸው በማግባባት ጠይቀውኝ ነበር። መንግስት ደግሞ ለታጣቂዎች ትረዳለህ ብሎ ለሶስት ወር ያህል ድርጅታቸውን ዘግቶት  ቆይቷል” 

 ታጣቂዎቹ አቀራረባቸው የማስፈራራት ባይሆንም የጠየቁትን ድጋፍ እምቢ ማለት ከነሱ የሚያጣላ እንደሆነባቸውም አልሸሸጉም። ባለሀብቱ ለታጣቂዎቹ ገንዘቡን ይክፈሉ አይክፈሉ ለመናገር ፈቃደኛ አልሆኑም። 

በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ እንዲሰጠን የጠየቅነው የፌደራል ፖሊስ በማናቸውም የወንጀል ጉዳይ በወቅቱ መረጃ ከቀረበለት እርምጃ ለመውሰድና ምርመራም ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ነግሮናል። ስዎች ከወንጀለኞች ጋር ተሰማምተውና ገንዘብ ከፍለው  ከጨረሱ በኋላ የሚመጣ አቤቱታ ላይ ፖሊስ ስራውን ለመስራት ይቸገራል ብሏል። 

የኦሮምያ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ መልስ ለመስጠት ትናንት ዓርብ ዕለት ቀጠሮ ቢሰጠንም አስቸኳይ ስራ ገጥሞናል በሚል በቀጠሮው ሳይገኙ ቀርተዋል። 

በንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን የባንክ መረጃን እናውቃለን በማለት አስፈራርቶ ገንዘብ መጠየቅ በተለይ በኦሮምያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በመለመዱ ንብረታቸውን ጥለው ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ እንዳሉም ዋዜማ ሰምታለች። [ዋዜማ]