ዋዜማ- ቅዳሜ ዕለት በየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲጂታል መዋቅር ላይ የተከሰተውን ግድፈት ተጠቅመው ገንዘብ የወስዱ አካላትን ለማደን ግብረ ኀይል መቋቋሙን ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ሰምታለች።


ከብሔራዊ ባንክና ንግድ ባንክ ባለሙያዎች እንዲሁም የፀጥታ አካላት የተካተቱበት ይህ ግብረ ኀይል በስድስት ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ከባንኩ ያለ አግባብ ተወስዷል ያለውን ገንዘብ ለማመለስ ያለመ ነው። ባንኩ የተወሰደበትን የገንዘብ መጠን አላሳወቀም። ፎርቹን ጋዜጣ እንደዘገበው ግን ከ66 ሺህ በላይ ደንበኞች አካውንት በችግሩ መታወኩን፣ ቅዳሜ ለስድስት ሰዓታት በቆየው መታወክ 25 ሺ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር መደረጉን እንዲሁም ሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊየን ብር ተንቀሳቅሷል። ባንኩ መረጃውን ማረጋገጥ አልፈለገም።

አንዳንድ የትምህርት ተቋማት ከወዲሁ ገንዘብ ከክፍያ ማሽኖች የወሰዱና በህገወጥ ዝውውሩ የተሳተፉ ተማሪዎች ገንዘቡን ለባንኩ እንዲመልሱና ራሳቸውን ከህግ ተጠየቂነት እንዲያተርፉ የሚያሳስብ ጥሪ አድርገዋል።

በባንኩ ላይ የደረሰው ችግር የሳይበር ጥቃት አለመሆኑንና ውስጣዊ ግድፈት መሆኑን ባንኩ አበክሮ ገልጿል።

የባንኩ የውስጥ ምንጮች ለዋዜማ እንደተናገሩት ግን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የተከናወነ አንድ መንግስታዊ የባንክ ክፍያ (ከአንድ መቶ ሚሊየን ብር ያላነሰ) ከአንድ በላይ የከፋይ ወገን በዲጂታል ፊርማ ሊያፀድቀው ሲገባ በአንድ ሰው ፈራሚነት ወደ ተከፋይ መተላለፉ የባንኩን ሀላፊዎች አስደንግጦ ነበር። አርብ ዕለት ችግሩን ለማወቅና ለመፍታት ሙከራ ሲደረግ መዋሉንና የቅዳሜ ሌሊቱ ቀውስ መከተሉን ሰምተናል።


ባንኩ የሳይበር ጥቃት አለመፈፀሙን ይናገር እንጂ ክስተቱ በባንኩ ዲጂታል መዋቅር ላይ በውስጥ አዋቂ የተፈፀመ ጥቃት ሊሆን እንደሚችል የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ባንኩ ከተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ ጋር በተያያዘ በርካታ ሰራተኞችን ከስራ ያሰናበተ መሆኑን ባለፈው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል።

ብሄራዊ ባንክ፣ ቅዳሜ እለት በንግድ ባንክ ላይ ያጋጠመው የአገልግሎት መቋረጥ በባንኩ አገልግሎት መስጫ ሥርዓት ላይ ከተደረገ የደኅንነት ፍተሻና የማሻሻያ ሥራ ጋር የተያያዘ እንደኾነ ገልጧል።

ብሄራዊ ባንክ፣ ክስተቱ የባንኩን፣ የደንበኞቹንና አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል አለመኾኑን አረጋግጫለኹ ብሏል። ባንኩ፣ ችግሩ ባስከተላቸው ጉዳቶች ላይ ምርመራ አድርጎ ውጤቱን ወደፊት እንደሚገልጥ አስታውቋል። ባኹኑ ወቅት የኹሉም የፋይናንስ ተቋማት የፋይናንስ ሥርዓቶች ደኅንነቸው የተጠበቀ መኾኑን ባንኩ ገልጦ፣ ኅብረተሰቡ ያለ ስጋት የፋይናንስ አገልግሎቶችን መጠቀም እንዲቀጥል አሳስቧል። [ዋዜማ]