Abay Woldu and Debretsion GMichael-FILE
Abay Woldu and Debretsion GMichael-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የድርጅቱ ብሔርተኛ ካድሬዎች ካልሆኑ በስተቀር እምብዛምም የሕዝብ አለኝታና ድጋፍ የላቸውም የሚባሉት አቶ አባይ ወልዱ የሕወሓትን የሊቀመንበርነት ቦታ ይዞ የመቀጠል እድላቸው ጠባብ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ዶክተር ደብረጺዮን ቦታውም ለመያዝ ግልጽ ፍላጎት እንዳሳዩም ተወርቷል፡፡ ምናልባት አቶ አባይ በዚህ ወንበር ላይ የሚቆዩት እስከሚቀጥለው የኢህአዴግ ጉባኤ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡
በአንጻሩ ዶክተር ደብረጺዮን ውስጥ ውስጡን ከፍተኛ የካድሬ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ እየሠሩ እንደሆነ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የሕወሓት ሊቀመንበር አቶ አባይና ምክትላቸው ዶክተር ደብረጺዮን የሻከረ ግንኙነት እንዳላቸውና ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ስብሰባዎች ኃይለቃል መለዋወጣቸው ይነገራል፡፡ አቶ አባይ ወልዱ በአካባቢው ተወላጆች በአቅም ማነስ ክፉኛ የሚተቹ ቢሆንም ‹‹የትግራይን ጥቅም አሳልፈው አይሰጡም፣ በሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ ጭምር ታማኝ ታጋይና አታጋይ ስለመሆናቸው በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የመጨረሻዎቹ ሰዓታት ተመስክሮላቸዋል›› ስለሚባል ስልጣናቸውን ማቆየት እንደቻሉ ይነገራል፡፡
ዘለግ ላሉ ቀናት በከፍተኛ ምስጢር እየተካሄደ የነበረው የሕወሓት የመቀሌ የማዕከላዊ ኮሚቴ ጉባኤ መስከረም 23 የተጀመረ ሲሆን ከሰሞኑ ፍጻሜዉን አግኝቷል፡፡ የጉባኤውን ምስጢራዊነት ለመጠበቅ ሲባል ከተሰብሳቢዎች ውጭ የፓርቲው ልሳን የሆኑት የወይን አዘጋጆች እንኳ እንዳይገቡ መደረጉ የዘንድሮወን ጉባኤ ልዩ አድርጎታል፡፡
በጉባኤው ፍጻሜ የወጡ መግለጫዎች አዲስነት ባይኖራቸውም ጉባኤው ላይ አዲስ ነገር አልተከሰተም ማለት እንዳልሆነ የሚናገሩ ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ጉባኤ በመጪው ኅዳር ለሚካሄደው ጉባኤ አሰላለፍና የፖለቲካ አቅጣጫ ፍንጭ የሚገኝበት እንደሚሆን ይታወቃል፡፡ የሕወሓት ነባር ጉምቱ አባላት ጉባኤውን ገባ ወጣ እያሉም ቢሆን በታዛቢነት ታድመውታል፡፡
የኢህአዴግ ሕልውና በራሱ ፈተና ላይ በወደቀበት በአሁኑ ጊዜ ያልተጠበቁ ለውጦችን ያስተናግዳል ተብሎ የሚጠበቀው 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ በመጪው ኅዳር መጨረሻ ይካሄዳል ቢባልም የኢህአዴግ ቢሮ ድርጅት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሹጉጤ ቀን አልተቆረጠለትም ሲሉ ለሳምንታዊው ካፒታል ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡ ጉባኤውን የምታስተናግደው ሐዋሳ ከተማ እንደምትሆን ይጠበቃል፡፡