HH Abune Matias-FILE
HH Abune Matias-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- ብዙ ውጣ ውረዶችና ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት የሚፈታተናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክህነት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ለቅርብ ስዎቻቸው በመጪው ሳምንት “ስልጣኔን እለቃለሁ” ማለታቸውን የዋዜማ ምንጮች ነግረውናል።
ባለፉት አራት ቀናት ሲካሄድ በነበረውና ትናንት ሐሞስ በተጠናቀቀው 36ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ላይ ከሌሎች ጳጳሳትና ከቤተክህነት አስተዳደር ጋር በአደባባይ እስጥ አገባ ውስጥ ያሳለፉት አቡነ ማትያስ በጉባዔው ጣልቃ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ እንደሚፈልጉ ለቅርብ ስዎቻቸው ተናግረዋል።
በቤተክህነቱ አካባቢ ስልጣናቸውን የሚገዳደሩና የማይታዘዟቸው እየበዙ በመምጣታቸው ክፉኛ የተበሳጩት አቡነ ማቲያስ በመጪው ሰኞ በሚጀምረው የሲኖዶሱ ጉባዔ ላይ መልቀቂያ ማቅረብ እፈልጋለሁ ብለዋል።
የፓትርያርኩ እርምጃ ያሳሰበው መንግስት ፓትርያርኩ ሀገሪቱ ያለችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ አጢነው ስልጣን ከመልቀቅ ይልቅ በውይይት ችግሮችን እንዲፈቱ ከማክስኞ ምሽት ጀምሮ አንድ ቡድን በመላክ እያግባባቸው ነው።

አቡነ ማትያስ የቤተክርስቲያኒቱ የወንጌል ማስፋፋትና ትምህርት አንድ አሀድ ከሆነው ማህበረ ቅዱሳን ጋር የተካረረ ውዝግብ ውስጥ የቆዩ ሲሆን መንግስት ማህበሩን እንዲዘጋው እስከመጠየቅ ደርሰዋል። ማህበሩ በቅርቡ የጀመረውን የቴሌቭዥን ስርጭትም ህገወጥ በመሆኑ ሊታገድ ይገባል ባይ ናቸው አቡነ ማትያስ።
ፓትርያርኩ ለአራት ቀናት በተካሄደው የመንፈሳዊ ሰበካ ጉባዔ ላይ የማህበረ ቅዱሳን ተወካዮች እንዳይካፈሉ ትዕዛዝ ስጥተው ማህበሩን እንዳይሳተፍ ማድረግ ቢችሉም የቤተክህነት አስተዳደርና ሌሎች ገዳማት የማህበረ ቅዱሳንን ሚና የሚያጎላና የሚያወድስ ሪፖርት ማቅረባቸው አቡነ ማቲያስን አስከፍቷቸዋል።
ጉባዔው ማህበረ ቅዱሳንን ከማውገዝ ይልቅ ለቤተክርስቲያኒቷ አለኝታ የሆነና ድጋፍ ሊደረግለት የሚገባ መሆኑንም የተናገሩ አባቶች ነበሩ።
በአራቱ ቀን ጉባዔ ከአቡነ ፋኑኤል ጋር የከፋ የቃላት ልውውጥ ያደረጉት ፓትርያርኩ ብዙውን ጊዜ በዝምታና በማኩረፍ እንዳሳለፉ ከጉባዔው ተሳታፊዎች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የውዝግቡን መካረር ተከትሎ መንግስት የጉባዔውን ሂደት በቅርብ ሲከታተል የቆየ ሲሆን በማጠቃለያ የአቋም መግለጫ ላይ የማህበረ ቅዱሳን የቴሌቭዥን ስርጭት “ህገ-ወጥ” መሆኑን የሚገልፅ አንቀፅ ከጉባዔተኛው ስምምነት ውጪ እንዲጨመር መደረጉ ብዙዎችን አሳዝኗል። አንቀፁ የተጨመረው አቡነ ማትያስን “ተሰሚ” አድርጎ ለመሳል “በትዕዛዝ” የተካተተ እንደሆነ ከቃለጉባዔ መዝጋቢዎች ተሰምቷል።
አቡነ ማትያስ መንግስት በማህበረ ቅዱሳን ላይ እርምጃ አለመውሰዱ እንዳስኮረፋቸው ለመንግስት ተወካዮች ከዚህ በፊት ተናግረዋል። በመንግስት በኩል ግን ማህበሩ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ፍላጎት አለመኖሩን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ያሰረዳሉ።
የአቡነ ማትያስ ዛቻ መንግስትንም ሆነ ሲኖዶሱን ለመገፋፋት የተዘየደ መላ ሊሆን እንደሚችል ግምት ያስቀምጣሉ።
ሌሎች አስተያየት ስጪዎች ደግሞ ፓትርያርኩ ስሜታዊና “ለክብራቸው ሟች” ስለሆኑ ሊሰናበቱ ይችላሉ ሲሉ ያስረዳሉ።