ዋዜማ- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰኔ ወር 2014 እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍነውንና በአገሪቱ ያለውን አጠቃላይ የሰብዓዊ መብት አያያዝን የሚዳስስ ሪፖርት ይፋ አደረገ፡፡

የኮሚሽኑ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ዛሬ ሃምሌ 5 ቀን 2015 ዓም ሪፖርቱን ለጋዜጠኞች ይፋ ያደረጉ ሲሆን በውስጡ የበርካታ መብቶች ጥሰት ማጋጠሙንና የአንዳንዶቹ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን በመግለፅ አሳስቧል።

በሪፖርቱ እንደተመላከተው የአስገድዶ መሰወር፣ የጭካኔ፣ አዋራጅና ኢሰብአዊ አያያዝ መጨመር፣ የኢመደበኛ ማቆያ ቦታዎች መበራከት እንዲሁም ከሕግ ውጪ የሆነ የዘፈቀደ እስሮችም ሆኑ በመብቶች ላይ የሚጣሉ ገደቦች እጅግ አሳሳቢ ሆነዋል፡፡ በመሆኑም የእነዚህ መብቶች መጣስ በሌሎች ነጻነቶችና መብቶች ላይ እጅግ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደፈጠሩና አጠቃላይ ሀገራዊውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ ወደኋላ የሚጎትቱ በመሆናቸው መንግሥት በአፋጣኝ ተገቢውን እርምጃዎች በመውሰድ ሊያስቆመው እንደሚገባ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አሳስቧል::

ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 2015 ዓ.ም. ድረስ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች በተከሰቱና በአብዛኛውም በቀጠሉ ግጭቶች፣ ጥቃቶችና የጸጥታ መደፍረሶች ምክንያት ሲቪል ሰዎች በታጣቂ ኃይሎችና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎች ለሞት እና ለአካል ጉዳት መጋለጣቸውን ጠቅሶ በዚህም በህይወት የመኖር መብት አደጋ ላይ መውደቁን አስታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ የአድዋ ድል በዓል በታሰበበት ዕለት እንዲሁም በሸገር ከተማ መስጊድ መፍረስ ጋር ተያይዞ በአንዋር መስጊድ ተቋውሟቸውን ባሰሙ ሙስሊሞች ላይ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ የሰው ሕይወት መጥፋቱንና በርካታ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት እንደደረሰ በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡

በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ደብረ ኤልያስ ወረዳ በሚገኘውና ብሔረ ብፁዓን አፄ መልከዓ ሥላሴ ገዳም የአማራ ልዩ ኃይልና የአካባቢው ጸጥታ አካላት ገዳሙ የፋኖና የሽፍታ መደበቂያ ሆኗል በማለት ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ገዳሙን ሲፈትሹ ከዋሉ በኋላ “የገዳሙን አባቶች ይዘን እንሄዳለን” ሲሉ በገዳሙ ውስጥ የነበሩ ምእመናን እና መነኮሳት “አባቶችን ይዛችሁ አትወጡም” በማለት በተፈጠረ ግጭት የፀጥታ አካላት በወሰዱት የኃይል እርምጃ ቢያንስ 15 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውንና በ18 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት መድረሱን ሪፖረቱ ያስረዳል፡፡

በተመሳሳይ ግንቦት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ ዞን በሀገር መከላከያ ሠራዊት በተወሰደ የኃይል እርምጃ ምክንያት በሸዋሮቢት ቢያንስ 5 ሲቪል ሰዎች፣ በዚሁ ዞን ራሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሣሪያ ማስፈታት በሚል በተወሰደ እርምጃ አንድ ቄስን ጨምሮ 7 ነዋሪዎች ላይ ግድያ መፈጸሙን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ ሪፖርት በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ላጋጠማቸው የውሃ ችግር መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ለመጠየቅ የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ሰልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ በፖሊስ በተወሰደ የኃይል እርምጃ 3 ሰዎች ሲገደሉ 30 ነዋሪዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ በምሥራቅ ወለጋ ፣ በምዕራብ ወለጋ ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በቄለም ወለጋ፣ ኢሉ አባቦራ ፣ በቡኖ በደሌ ፣ በምሥራቅ ሸዋ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ በአርሲ ዞኖችና በሁለቱ የጉጂ ዞኖች ያለው ግጭት አሁንም መቀጠሉን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አብራርቷል፡፡

በእነዘህ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በተለይም በኪረሙ፣ ጊዳ አያና፣ አልጌ፣ ሁሩሙ፣ በአሙሩ፣ ሆሮ ቡሉቅ፣ ጃርደጋ ጃርቴ፣ ቦሰት፣ ግንደበረት፣ ጮቢ፣ ደራ፣ ኩዩ፣ መርቲ ጀጁ እና የአርሲ ዞን አጎራባች ወረዳዎችን የሚደርሱ ግጭቶችና ጥቃቶች ለሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት ምክንያት መሆናቸው አሁንም እጅግ አሳሳቢና ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ተገልጧል፡፡

ኮሚሽኑ ከአዲስ አበባ ከተማ፣ ከኦሮሚያና ከአማራ ክልሎች በደረሰው አቤቱታና ጥቆማማ በመነሳት አደረኩት ባለው ክትትል በርካታ የአስገድዶ መሰወር ድርጊቶች መከሰታቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

በዚህ ድርጊት አብዛኛውን ጊዜ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከሥራ ቦታ ወይም ከመንገድ ላይ የሲቪልና የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግሥት ጸጥታና ደኅንነት ሠራተኞች መሆናቸውን ሪፖርቱ ያመለካክታል፡፡  የተያዙ ሰዎችም ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ወዳልታወቀ ስፍራ እንደሚሰወሩና ከፊሎቹ ከተወሰኑ ቀናት፣ ሳምንታት ወይም ወራት መሰወር በኋላ የተገኙ ቢሆንም በግዳጅ መሰወሩ አሁንም መቀጠሉን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ከማደራጀት ጋር በተያያዘ በመንግሥት በሚወሰዱ እርምጃዎች የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የሲቪክ ማኅበራት ኃላፊዎች እና አባላት እንዲሁም “ሰላማዊ ሰልፍን ጨምሮ በተለያዩ አማራጮች ሕዝቡ መንግሥትን እንዲቃወም አደራጅተዋል” የተባሉ ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ እስርና አስገድዶ መሰወር መፈጸሙን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ ከእነዚህ አካላት መካከል በተለያየ ቦታና ሁኔታ በክልሉ ፖሊስ ታስረው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የቆዩ በርካታ ስለመሆናቸውም ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡

ከጭካኔ፣ ኢሰብአዊና አዋራጅ አያያዝና ቅጣት ነጻ የመሆን መብትን በተመለከተ በሚያብራረው ሪፖርቱ በበርካታ ማረሚያ ቤቶችና የፖሊስ ማቆያ ቦታዎች መሻሻሎችን ቢኖሩም በበርካታ አካባቢዎች በወንጀል የተጠረጠረን ሰው የተጠረጠረበትን ወንጀል እንዲያምን ድብደባና ግርፋትን ጨምሮ ሌሎች ኢሰብአዊና አዋራጅ ተግባራት የሚፈጸሙባቸው እስር ቤቶችና መደበኛ ያልሆኑ የተጠርጣሪዎች ማቆያ ቦታዎች ስለመኖራቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ሜጫ ወረዳ ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ዝርፊያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠረ ግለሰብ የእምነት ቃልን አስገድዶ ለማግኘት ከታሰረበት ቀን ጀምሮ ባሉ የተለያዩ ቀናት በተደጋገሚ በፖሊስ ጣቢያና ወደ ጫካ በመውሰድ የግለሰቡን እጅና እግር ለየብቻ በማሰርና እንጨት ላይ በማንጠልጠል “ወፌ ላላ” ተብሎ የሚጠራ ግርፋት እንደተፈጸመበትና “የማታምን ከሆነ እንገድልሃለን” በማለት በአንገቱ ገመድ በማስገባት በጉልበቱ አንበርክከው በጠጠር ላይ በመጎተት የግድያ ማስፈራሪያ እንደደረሰበት ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሽርቆሌ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ አንድን ተጠርጣሪ የአእምሮ ሕመም ያለበት ነው በማለት ለበርካታ ቀናት በካቴና አስሮ በአንድ ክፍል ማቆየታቸውን እንዳረጋገጠም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

በሶማሊ ክልል በፋፈንና ሀቫና ፖሊስ ጣቢያዎች በተጠርጣሪዎች ላይ ዛቻና ማስፈራራት በመፈጸም የተጠረጠሩበትን ወንጀል እንዲያምኑ የማስገደድ ድርጊት በመፈጸም በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች ተጠርጣሪዎች ለረጅም ሰዓታት በካቴና እንደሚታሰሩ ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡

የፖለቲካ መብቶችን ጥሰትን በሚያመላክተው የሪፖረቱ ክፍል በሚድያ አካላት፣ በፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ላይ የሚፈጸሙ እስሮች፣ ወከባዎችና ሌሎች እንግልቶች የጨመሩ ሲሆን፣ ይህም በሲቪክ ምኅዳሩ ላይ በርካታ አሳሳቢ ክስተቶች መመዝገባቸውን ተረድቻለሁ ብሏል ኮሚሽኑ፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከየካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ  የኢንተርኔት አገልግሎቶች ላይ (ዩትዩብ፣ ቴሌግራም እና ፌስቡክ) ገደብ መጣሉ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽና መረጃ የማግኘት መብትን መገደቡንና ሰዎችን ለተጨማሪ ወጪ መዳረጉን አስታውቋል፡፡

በአማራ ክልል በተለይም ከ”ሕግ ማስከበር ዘመቻ” ጋር ተያይዞ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የማኅበረሰብ አንቂዎችን፣ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት እንዲሁም በተለያዩ የሲቪል ማኅበራት ተደራጅተው የሚሰሩ ሰዎች ላይ “ተደጋጋሚ እና የተራዘመ እስር” ስለመቀጠሉ ሪፖርቱ አብራርቷል፡፡

የመንቀሳቀስ መብት ላይ ያተኮረው ሌላኛው የሪፖርቱ ክፍል ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ለመንቀሳቀስም ሆነ በአንድ ክልል ወይም በአንድ ቦታ ውስጥ የሰዓት እላፊ ገደብ በመጣልና መስፈርቶችን በማስቀመጥ በመንቀሳቀስ መብት ላይ የተደረጉ በርካታ ገደቦች ሰፋ ያሉ መሆናቸውን አመላክቷል፡፡

የመንቀሳቀስ ገደቦቹ በአብዛኛው በከተማዎቹ አስተዳደሮች የሚጣሉና በአብዛኛውም የዘፈቀደ፣ ወይም በተገቢው የሕግ ማዕቀፍ ያልታነጹ መሆናቸው ሰዎችን ለእንግልትና ለእስር እንዲሁም ለሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መዳረጉ ተገልጿል፡፡

በትግራይ ክልል ከፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረም በኋላ የአየርና የየብስ ትራንስፖርት ቢጀምርም ተጠቃሚዎች ላይ በእድሜ ወይም በጾታ ገደብ ማድረግን ጨምሮ የዘፈቀደ ክልከላዎች መቀጠላቸውን ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች በተለይም በአሶሳ በባምባሲ ወረዳ “ወቅታዊ ሁኔታዎች” በሚል ለእስር የሚያበቃ በቂ ምክንያት በሌለበት አግባብና የሰዎችን በሀገሪቱ የትኛውም አካባቢ ተቀሳቅሶ የመኖርና የመሥራት መብት በሚጥስ መልኩ በተለይም ከአማራ ክልል ወደ ክልሉ የሚመጡ ሰዎችን ከኤርፖርት ጭምር በመታወቂያ በመለየት ተገቢ ያልሆነ እስርና በኃይል የመመለስ ድርጊት ስመፈጸሙ አብራርቷል፡፡

በጥበቃ ሥር ያሉ (የታሠሩ) ሰዎች መብቶችና የተያዙ ሰዎች ሁኔታ በሚብራረው የሪፖርቱ ክፍል በሁሉም ክልሎች የሚገኙ አብዛኛዎቹ ፖሊስ ጣቢያዎች የሕክምና፣ የምግብ እና የውሃ አገልግሎት በቂ አለመሆኑን ተጠቁሟል፡፡  በተጨማሪም ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበትን ወንጀል እንዲያምኑ በፖሊስ ድብደባና የማሰቃየት ተግባር መፈፀሙን፤ የፖሊስ አባላት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በሚያውሉበት ጊዜ ማንነታቸውን ወጥ በሆነ መልኩ የማያስተዋውቁና ተጠርጣሪዎች የቀረበባቸውን ክስና የተያዙበትን ምክንያት የማያሳውቁ ስለመሆኑ በክትትል ደርሸበታለሁ ብሏል ኮሚሽኑ፡፡

በፖሊስ ማቆያ ጣቢያዎች ሕጉ ከሚፈቅደው የጊዜ ገደብ በላይ ተጠርጣሪዎችን ለረጅም ጊዜ ማሰር ፤ የዋስትና መብትን አለማክበርና ሕጋዊ ሥርዓትን ያልተከተለ እሥር መኖሩ፤ በአብዛኛው ፖሊስ ጣቢያዎች የሴቶች እና የወንዶች ማቆያ ክፍሎች በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ የተለየ ግቢ የሌላቸውና ሰፊ የንጽሕና ጉድለት ያለባቸው  መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች የጸጥታ ችግርን ምክንያት በማድረግ ሰዎችን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝ፣ በጅምላ ማሰር፣ በሕግ በተመለከተው ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤት አለማቅረብ፣ የዋስትና መብት መንፈግ እና ለረዥም ጊዜ በእሥር ማቆየት መቀጠሉን ሪፖረቱ ያመላካታል፡፡ በዚህም ከሽብር ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸሁ ተብለው የተያዙ ሰዎች ከ6 ወር እስከ 1 ዓመት በላይ ክስ ሳይመሠረትባቸው በፖሊስ ጣቢያ እና በማረሚያ ቤቶች መኖራቸው ኮሚሽኑ በክትትሉ የለያቸውና እጅግ አሳሳቢ ጉዳዮች ናቸው ብሏልል፡

የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ ለኢሰመኮ ከ1325 በላይ አቤቱታዎችን በዋናነት የቀረቡት ቅሬታዎች በሕይወት የመኖር መብት፣ አካል ደኅንነት መብት፣ ፍትሕ የማግኘት መብት፣ ከሕገ-ወጥ እሥር የመጠበቅ መብት፣ ዋስትና የማግኘት መብትና በቁጥጥር ሥር ያሉ ሰዎች አያያዝ ጋር የተያያዙ ስመሆናቸው ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

ኮሚሽኑ ከሴቶችና የሕፃናት መብቶች ጋር በተያያዘ በሲዳማ ክልል የሴት ሕፃናት ላይ ጠለፋና አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ፆታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶች መጨመራቸውን ሪፖቱ ያመላከተ ሲሆን በተለይም በሃዋሳ በርካታ ሴት ሕፃናት የዚህ የመብት ጥሰት ሰለባ መሆናቸው አሳሳቢ ነው ብሏል ፡፡  በመሆኑም የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ለመከላለክል የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ማረጋገጥ በዕርቅ ስም ቸል ሊባል አይገባም ሲል ኮሚሽኑ አሳስቧል ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የሚደረጉ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ጉባኤዎችና ሌሎች ተመሳሳይ ኹነቶች ጋር በተያያዘ በርካታ በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከጎዳና ላይ እንዲነሱ በማድረግ ለተለያየ የጊዜ መጠን በአንድ ማቆያ ስፍራ እንዲቆዩ እንደሚደረግ የገለጸው ሪፖርቱ ሕፃናቱን ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የሚያጋልጥ በመሆኑ በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባ አሳስቧል ፡፡

ከአካል ጉዳት ጋር በተገናኘ በሚያብራራው ሪፖርቱ የአማራ ክልል ከአካል ጉዳተኞች ዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ስምምነት ጋር የሚቃረኑ መመሪያዎች ያወጣ መሆኑ ጠቅሶ የአካል ጉዳተኞች የተናጥል መብቶች እንዳይከበሩ እንቅፋት አንደፈጠረ አንስቷል፡

ኮሚሽኑ በፍትሕ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አጠቃላይ ሂደት በተለይም ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ፣ ተዓማኒና ግልጽነት ያለው እንዲሆን እንዲሁም ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ያሟላና የሰብአዊ መብቶች መርሖች የተከተለ እንዲሆን ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቋል፡

በክልሎች ከሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች ጋር የተጀመሩ ሰላም የማምጣት እንቅስቃሴዎች አበረታች ቢሆኑም ዘላቂ እንዲሆኑ ሂደታቸው ተጎጂዎችን ጨምሮ ሁሉንም ባለድርሻ አካላትና ሴቶችን ያካተቱ እና ግልጽ ሊሆኑ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡ [ዋዜማ]