የአዳማ ከተማ አስተዳደር በጉዳዩ ላይ ምላሽ ሰጥቶናል

Adama city Adminstration Bldg, Photo credit- Reporter

ዋዜማ- ከሰሞኑ በኦሮምያ ክልላዊ መንግስት በአዳማ ከተማ አስተዳደር የ”ህዝብ ቆጠራ ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የነዋሪችዎን መረጃን የመሰብሰብ ስራ በበርካቶች ዘንድ ግርታን መፍጠሩን ዋዜማ ካነጋገረቻቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተረድታለች።

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የአዳማ ከተማ ነዋሪ ለዋዜማ ሲናገሩ “ከቀበሌ ነው የመጣነው ; የህዝብ ቆጠራ እያደረግን ነው ” ያሉ ሰዎች ” የቤተሰባቸውን ብዛት ; ብሄር ; ሀይማኖት ; የቤተሰባቸውን የጾታ ተዋጽኦ እና እድሜ ተጠይቀው መረጃ እንደሰጡ ገልጸዋል።ሆኖም ነገሩ ግርታን እና ስጋትን እንደፈጠረባቸው አልሸሸጉም።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው በተመሳሳይ የእሳቸውን እና የቤተሰባቸውን የሀይማኖትና የብሄር እንዲሁም ሌሎች መረጃዎችን ከቀበሌ ለህዝብ ቆጠራ መጣን ላሉ ሰዎች መናገራቸውን ፣ ግን ደግሞ ሁኔታው ግን ግራ አጋቢ እንደሆነባቸው ገልጸውልናል።

“ሲጀመር የህዝብ ቆጠራ በክልል ደረጃ ይካሄዳል ወይ?” የሚል ጥያቄን ያነሱት ግለሰቡ “መረጃው የተፈለገው ለመሰረተ ልማትና መንግስታዊ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት ከሆነስ ብሄር እና ሀይማኖትን መጠየቅ ለምን አስፈለገ ? ” ሲሉ የተፈጠረባቸውን ግርታ ያስረዳሉ።

ከሰሞኑ በከተማው የመኖርያ ቦታ ካርታን ለማስተካከል በሚል ከነዋሪዎች እየተጠየቀ ካለው ከፍያለ ክፍያ ጋር በማያያዝ  ሁኔታውን አዲስ ከተመሰረተው የሸገር ከተማ የመፈናቀል እንቅስቃሴ ጋር በማገናኘት ምቾት እንደነሳቸውም ጨምረው ነግረውናል። 

ይህን መሰሉ ስጋትና ውዥንብር የበርካታ አዳማ ከተማ ነዋሪዎች ጥያቄ መሆኑንም መረዳት ችለናል።

ዋዜማ በጉዳዩ ላይ የአዳማ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሙሉጌታ ቃበቶን ማብራሪያ ጠይቃለች።

አቶ ሙሉጌታ ” አዳማ ከተማ አስተዳደር በከፍተኛ ደረጃ እየሰፋች ስለሆነ ይህንንም ተከትሎ አዲስ የከተማ እና ወረዳ አወቃቀር እየተሰራ ስለሆነ ቆጠራው ለዚያ መዋቅር እንዲያግዝ ታስቦ ነው” ብለዋል።

የኦሮምያ ክልላዊ መንግስት በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው የአዳማ ከተማ አስተዳደር በዙሪያው ያሉ የአዳማ ወረዳ የገጠሮቹን አካቶ 24 ቀበሌዎችን እንዲሁም ወንጂ እና ሶደሬ ከተሞችን በማካተት ፣ በጥቅሉ በስድስት ክፍለ ከተሞች እና 19 ወረዳዎች  እየተዋቀረ መሆኑን የጽህፈት ቤት ሀላፊው አስታውሰዋል።

ከዚህ በኋላ የቀበሌ መዋቅር አዲስ በሚፈጠው የአዳማ ከተማ አስተዳደር እንደማይኖር የነገሩን አቶ ሙሉጌታ ቃበቶ ፣ እየተደረገ ያለው ቆጠራ እያንዳንዳቸው ቀበሌዎች ወረዳ ለመሆን በቂ ህዝብ ይኑራቸው አይኑራቸው ለመለየት እና የህዝብ ቁጥር የሚያሟሉት ቀበሌዎች ወደ ወረዳ እንዲያድጉ የማያሟሉት ደግሞ ከሌላ ቀበሌ ጋር ተቀላቅለው ወረዳ እንዲሆኑ ለማስቻል እንደሆነ አስረድተዋል።

ታዲያ የወረዳ እና የክፍለ ከተማ መዋቅር ለመስራት ነዋሪዎችን ብሄርና ሀይማኖት መጠየቅ ምን ይጠቅማል? ስትል ዋዜማ ለአቶ ሙሉጌታ ጥያቄን አቅርባለች። 

አቶ ሙሉጌታ ለጥያቄው ምላሽን ሲሰጡ ” ብሄርና ሀይማኖት እየተጠየቀ ያለው እግረ መንገድ መረጃ ለመሰብሰብ ፣ ለየትኛውም አካል እና በየከተማ ፣ ክፍለ ከተማ እና ወረዳ ለሚመደቡ አመራሮች በስራቸው ያለ ነዋሪን የብሄር ፣ የሀይማኖት ፣ የጾታ እና እድሜ ስብጥር መረጃ ለማዘጋጀት እንጂ ምንም ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ የለውም”

“ከወቅታዊ ነገሮች ጋር አያይዞ መስጋትም በፍጹም አይገባም” ብለዋል አቶ ሙሉጌታ። 

የአዳማ ከተማ አስተዳደር አዲስ የምታካትታቸው አካባቢዎችን ጨምሮ እስከ 57 ሺህ ሄክታር ስፋት ስለሚኖራት ፣ ቆጠራውም ለሚሰራው መዋቅር የሚረዳ መሆኑን የአዳማ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል። [ዋዜማ]