ዋዜማ – በዚህ ሳምንት በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢጋድ ሰላም አፈላላጊ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በሱዳን “የአመራር ክፍተት ተፈጥሯል” ሲሉ በሰጡት አስተያየት ሱዳን መደንገጧን አስታወቀች። 

የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በሱዳን ላይ ” የአየር በረራ እገዳ” እንዲጣልና ተፋላሚዎች “የከባድ ጦር መሳሪያ ትጥቅ እንዲፈቱ” እንዲደረግ ጥሪ አድርገዋል በማለት ያወገዘችው ሱዳን፣ ጥሪው “ሉዓላዊነቴን የጣሰ ነው” ብላለች።

የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አስተያየት ከዚህ ቀደም ለሱዳን ሉዐላዊ ምክር ቤት ሰብሳቢና ለሀገሪቱ ጦር አዛዥ አብዱልፈታ አልቡርሃን በግል ከነገሯቸው አቋም ጋር የሚቃረን መሆኑን የገለፀው መግለጫው በዚህም አስተያየት ሱዳን መደንገጧን አብራርቷል። 

በአዲስ አበባው የሰላም አፈላላጊ የአራት ሀገራት መሪዎች ምክክር ላይ ሱዳን ለመሳተፍ ቃል ገብታ የነበረ ቢሆንም በጉባዔው ላይ ሳትገኝ ቀርታለች። የሰላም አፈላላጊ አባል ሀገራቱ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲና ኢትዮጵያ ናቸው። 

ሱዳን የኢጋድ የሰላም አፈላላጊ ኮሚቴ ሊቀመንበር የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ “ገለልተኛ አይደሉም” በሚል የኢጋድን ሽምግልና  አሻፈረኝ ስትል ቆይታለች። 

ሱዳን በግብፅ በተጠራውና በካይሮ ነገ በሚደረገው ለሱዳን ሰላም የማፈላለግ ጉባዔ ላይ  ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኗንም አስታወቃለች።

የኢጋድ ሀገራት የሱዳንን ሉዐላዊነት ጥያቄ ውስጥ በሚከት አቋማቸው ከቀጠሉ “ሱዳን የኢጋድ አባልነቷን ዳግም ለማጤን ትገደዳለች” ብሏል የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር መግለጫ።

በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ምላሽ ይኖር እንደሆነ ላቀረብነው ጥያቄ ምላሽ አላገኘንም። [ዋዜማ]