ዋዜማ- በአማራ ክልል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትከሎ ባንኮች በክልሉ የሚያንቀሳቅሱትን ጥሬ ገንዘብ ወደ አዲስ አበባ እያሽሹ መሆኑን ዋዜማ ከባንኮች ሰምታለች፡፡

የገንዘብ ማሸሹ የተከናወነባቸው የአማራ ክልል ከተሞች ከትናንሽ የወረዳ ከተሞች እስከ ክልሉ ዋና ከተማ ባህርዳር ጭምር  እንደሆነ ምንጮቻችን ነግረውናል።

ባንኮች ገንዘባቸውን ከክልሉ ወደ አዲስ አበባ ማንቀሳቀስ የጀመሩት ካለፈው ሳምንት ወዲህ ሲሆን፣  ከሃምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በተለይ ከወረዳ ቅርንጫፎች በስፋት ገንዘባቸውን  ማውጣታቸውን ዋዜማ ካነጋገረቻቸው የባንክ ምንጮች ተረድታለች፡፡

በተለይ የመንግሥት ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በክልሉ ለሚገኙ ዲስትሪክቶች ባስተላለፈው ትዕዛዝ መሰረት ከወረዳ ጀምሮ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች የተወሰነ ጥሬ ገንዘብ እንደመጠባበቂያ አስቀርቶ አብዘኛውን መሰብሰቡን የባንኩ ምንጮች ገልጠዋል፡፡

የክልሉ ክልሉ ዋና ከተማ ባህርዳርን ጨምሮ ባንኮች ሰሞኑን አገለግሎት መስጠት ያቆሙ ሲሆን፣ በተለይ እንደ ጎንደር ከተማ ባሉ ግጭቱ በተባባሰባቸው ከተሞች ከባንክ አገልግሎት ባሻገር የግብይት እንቅስቃሴ መስተጓጎል ተከስቷል፡፡

የክልሉ ነዋሪዎች እንደገለጹት በተለይ በንግድ ባንክ አንድ ሰው በቀን ከ10 ሺሕ ብር በላይ ማውጣት አይችልም የሚል ዕለታዊ ገንዘብ የማውጣት ገደብ ተጥሎባቸዋል፡፡

በደንበኞች ላይ የዕለታዊ ገንዘብ ወጪ መገደቡን ዋዜማ ያነጋገረቻቸው በክልሉ የሚገኙ የባንክ ሰራተኞች አረጋግጠዋል፡፡ የባንክ ቅርንጫፎች እጃቸው ላይ ያለው ጥሬ ገንዘብ ውስን ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በክልሉ በአሁኑ ወቅት ወደ ባንክ የሚገባ ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ምንጮች ያስረዳሉ፡፡

ገደቡን ተከትሎ የባንክ ደንበኞች “ገንዘባችንን እንዳናወጣ ተከለከልን” የሚል ቅሬታ እያቀረቡ ነው፡፡ የባንክ ሰራተኞች የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዳጋጠማቸው ከመግለጽ ውጪ ከደንበኞች በኩል በስፋት ለሚቀርብላቸው ቅሬታ መልስ መስጠት አልቻሉም ተብሏል፡፡ 

በክልሉ የተከሰተው አለመረጋጋት መስፋፋቱን ተከትሎ መንግሥት በታጣቂዎች ላይ “ሕግ ማስከበር” ያለውን እርምጃ አጠናክሬ እቀጥላለሁ ማለቱ በክልሉ ነዋሪቾ ዘንድ የባንክ አገልግሎት ተቋርጦ ይቆያል የሚል ስጋት መፍጠሩንም ካነጋገርናቸው ነዋሪዎች ተረድተናል። [ዋዜማ]