• ፖሊሲው በ2016 አ.ም መጨረሻ የዋጋ ንረትን በእጅጉ ይቀንሳል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል

ዋዜማ – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረት ክፉኛ የፈተነውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከችግር ያወጣልኛል ያለውን ፖሊሲን ማውጣቱን ትላንት ገልጿል። ይህ በቅርጹ 2014 አ.ም መስከረም ወር ላይ ከወጣው ፖሊሲ ጋር የሚመሳሰለውን ፖሊሲ ጥር ወር ላይ ለባንኩ ገዥነት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙት ማሞ ምህረቱ ይፋ አድርገዋል። የፖሊሲው ዋነኛ ይዘት የብድር ስርጭትን በመገደብ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ላይ ያተኮረ ነው።

አዲስ በወጣው ፖሊሲ መሰረትም የሀገር ውስጥ የብድር እድገት ከ14 በመቶ በተጀመረው የ2016 በጀት አመት ጣሪያው 14 በመቶ እንዲሆን ተወስኗል። ባንኮችም በሚያወጡት የብድር እቅድ ውስጥ ይህን ጣሪያ ከግምት ውስጥ እንዲያስገቡ የብሄራዊ ባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ በመግለጫቸው ላይ አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የ2015 በጀት መዝጊያ ንግግርን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ሲያደርጉ ፣ በተጠናቀቀው በጀት አመት በሀገር ውስጥ የተሰጠው ብድር 461 ቢሊየን ብር እንደነበር ማንሳታቸው ይታወሳል። ከዚህ አጠቃላይ ብድር ውስጥ ደግሞ 85 በመቶው ብድር የተሰጠው ለግሉ ዘርፍ ሲሆን፣ ቀሪው 15 በመቶ ደግሞ ለመንግስት የተሰጠ መሆኑን አንስተው ፣ ይህም መንግስታቸው ለግሉ ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ማሳያ አድርገውም አቅርበውት ነበር። ሆኖም ከሀምሌ 1/ 2015 አ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ባለው አዲስ በጀት አመት ግን የብድር እድገቱ ላይ የ14 በመቶ ጣሪያ ተቀምጦለታል። ይህም የዋጋ ንረትን ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ተገልጿል።

ሌላው በበርካታ ምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደ በጎ እርምጃ የተወሰደው አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ ፣ መንግስት ከብሔራዊ ባንክ በቀጥታ የሚበደረው (ብር የሚያሳትመው) መጠን ላይ የጣለው ከፍተኛ ገደብ ነው። 

መንግስት በዚህ በጀት አመት ከብሄራዊ ባንክ መበደር የሚችለው በ2015 በጀት አመት የተበደረውን አንድ ሶስተኛ ያህሉን ብቻ እንደሆነ ፖሊሲው ደንግጓል። ድንጋጌውም መንግስት ላይ መሰረታዊ ገደብ የጣለ መሆኑንም ጠቅሷል። ይህም ብቻ ሳይሆን ማእከላዊ መንግስትን ወክሎ ከብሔራዊ ባንክ ገንዘብ አሳትሞ የሚበደረው የገንዘብ ሚኒስቴር ፣ ከብሔራዊ ባንክ ገንዘብን መበደርን እንደ ብቸኛ አማራጭ መጠቀም የሚችለው በቂ የግምጃ ቤት ሰነድን ማውጣት ያልቻለ እንደሆነ ብቻ ነው።

መግለጫው ማዕከላዊ መንግስት በ2015 አ.ም ከብሔራዊ ባንክ የተበደረውን የገንዘብ መጠን ባይገልጽም ፣ ከዚህ ቀደም በወጡ ሪፖርቶች መሰረት ማእከላዊ መንግስት እስከ ታህሳስ 2015 አ.ም መጨረሻ ከብሔራዊ ባንክ የተበደረው ብድር 200 ቢሊየን ብር በማለፍ ታይቶ የማይታወቅ ደረጃ ደርሷል ተብሎ ነበር። ይህም ከሌሎች ምክንያቶች ጋር ተዳምሮ የሀገሪቱን የዋጋ ንረት በማቀጣጠሉ እንደ ዋነኛ ምክንያት ተጠቅሷል።

ብሔራዊ ባንክ ለመንግስት የሚሰጠው ብድር በመሰረታዊነት እንደ ሌሎች ባንኮች ከተሰበሰበ ቁጠባ ጋር ስለማይገናኝ እና ከምርትም ጋር ዝምድና ስለሌለው የዋጋ ንረትን እንደሚፈጥር በኢኮኖሚስቶች ዘንድ ይታመናል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ካቢኔያቸው ወደ ስልጣን ሲመጣ ለብር ህትመት የሚያጋልጠው የብሄራዊ ባንክ ብድርን እንደሚተው በማክሮ ኢኮኖሚ እቅዱ ደጋግሞ ገልጿል።በ “ለውጡ’” የመጀመርያ አመታትም ይህን እቅድ ከማሳካት አንጻር ከኢህአዴግ ዘመንም የተሻለ ነበር። 

ይሁንና ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያ ከአበዳሪ እና ለጋሾች ታገኝ የነበረው ብድር  እና እርዳታ በእጅጉ በመቀነሱ እንዲሁም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያም ከአለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ ቃል የተገባላት ብድር ስላልተሰጣት መንግስት ያጋጠመውን ከባድ የበጀት ጉድለት ለመሙላት ብቸኛ አማራጭ ያደረገው ከብሄራዊ ባንክ መበደርን ነው።

የፕሪቶሪያውን የህወሀት እና ፌዴራል መንግስት የሰላም ስምምነትን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከአለም አቀፍ አበዳሪዎች ገንዘብን ልታገኝ እንደምትችል ተስፋ ተጥሏል። የሁለተኛው ዙር የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚል ስያሜ ያለውን እቅድን የነደፈው መንግስትም ; ለማሻሻያው መተግበሪያ 12 ቢሊየን ዶላር ብድርን እንደጠየቀ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ ሚኒስትር ተክለወልድ አጥናፉ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ተናግረዋል። 

ማዕከላዊ መንግስት ከብሄራዊ ባንክ የሚበደረውን ገንዘብ ለመቀነስ ያቀደውም ይህ የብድር ጥያቄ በጎ ምላሽን ያገኛል ከሚል መነሻም ሊሆን ይችላል።

የንግድ ባንኮችም የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥማቸው ከብሄራዊ ባንክ የሚበደሩበትን ወለድ ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ማሳደጉን ብሄራዊ ባንክ በአዲሱ ፖሊሲው አሳውቋል። ይህም የብድር ስርጭትን በመቀነስ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር አጋዥ ተደርጎ ተወስዷል። 

በ2014 አ.ም መስከረም ወር ላይ ነበር ንግድ ባንኮች ከብሄራዊ ባንክ የሚበደሩበት የወለድ ተመን 16 በመቶ እንዲሆን የተወሰነው።አሁን የወለድ መጠኑ የተጨመረው ባንኮች በከፍተኛ የገንዘብ ችግር ውስጥ ባሉበት ወቅት ነው።

የውጭ ምንዛሬ ክፍፍል ላይ የተላለፈው ውሳኔም በንግዱ ማህበረሰብ ሲነሳ ለነበረው አቤቱታ መጠነኛ ምላሽን የሰጠ ነው። እስከ ዛሬ በነበረው አሰራር ምርት ላኪዎች የሚያመጡት የውጭ ምንዛሬ 70 በመቶው ለብሄራዊ ባንክ በእለቱ ምንዛሬ ተመን የሚገባ ሲሆን ፣ 10 በመቶው የውጭ ንግዱን ለፈጸመው ባንክ ይሸጣል ፣ ቀሪው 20 በመቶ ነው ላኪው እንዲጠቀምበት የሚደረገው። በተለምዶም የ70/30 አሰራር ይባላል። 

መንግስት ብድር እና እርዳታ ተቋርጦበት በመቆየቱ የምንዛሪ ፍላጎቱን ለማሟላት ሲተገብረው የነበረ አሰራር ነው። የ70/30 የውጭ ምንዛሬ ክፍፍል በገበያ ውስጥ ከፍተኛ የምንዛሬ እጥረትን በመፍጠር ፣ ምንዛሬን ለማግኘት የሚከፈል ኮሚሽንን በማስወደድ ገቢ እቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሬ እንዲከሰት አድርጓል። 

አሁን ብሄራዊ ባንክ የ70/30 አሰራር ወደ 50/50 እንዲቀየር ወስኗል።በአዲሱ የብሄራዊ ባንክ ፖሊሲ መሰረትም ላኪዎች ከሚያመጡት ምንዛሬ 50 በመቶው ለብሄራዊ ባንክ ፣ 10 በመቶው ላኪው ደንበኛ ለሆነበት ባንክ ፣ 40 በመቶው ደግሞ ለላኪው ተመድቧል። በአዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ በ2016 አ.ም መጨረሻ የዋጋ ንረትን አሁን ካለበት 30 በመቶ ወደ 20 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ታስቧል። [ዋዜማ]