ዋዜማ- ኢትዮጵያ 50 ቢሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች ከገነባች አምስት ዓመት አልሞላትም። አንዳንዶቹ ግንባታቸው ሊያልቅ የተቃረቡ ናቸው። በሀገሪቱ ባለው የፀጥታ ችግር፣ በኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት ችግርና በአስተዳደር ጉድለት ብዙ ተስፋ የተጣለባቸው እነዚህ ፋብሪካዎች አሁን ምርት አቁመው የሚታደጋቸውን አካል እየጠበቁ ነው። እስከወዲያኛው የመዘጋት አደጋ ያንዣበበባቸውም አሉ። ዋዜማ በጉዳዩ ላይ የሚከተለውን መረጃ አሰባስባለች። 

Tana Beles Sugar Factory

አርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካ

በቀድሞው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተመርቆ በግንቦት ወር 2007 ዓ.ም. ስራ የጀመረው በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን የሚገኘው የአርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካ፣ በሸንኮራ አገዳ ግብዓት አለመኖር፣ እንዲኹም ከስኳር ኮርፖሬሽኑ በኩል ለፋብሪካው በተሰጠው ዝቅተኛ ትኩረት ምክንያት ስራ ማቆሙን እና ሰራተኞቹንም መበተኑን ዋዜማ ከምንጮቿ አረጋግጣለች። 

ፋብሪካው እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ድረስ ምርት ሲያመርት ከቆየ በኋላ፣ ሙሉ ለሙሉ ስራ ማቆሙን የተናገሩት ምንጮች፣ ፋብሪካው ለማምረት ይጠቀምባቸው የነበሩትን ማሽኖች ከሚያንቀሳቅሱት ባለሙያዎች በቀር፣ ሌሎቹን ሰራተኞች በመበተን ወደ ጣና በለስ እና ኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካዎች እንዲመደቡ መደረጋቸውንም ዋዜማ ሰምታለች። 

እንደ ዋዜማ ምንጮች ገለፃ ከሆነ የፋብሪካው ግብዓት የአገዳ ምርት የጠፋው ፣ ለሸንኮራ አገዳ ማልሚያ በሚል ከመሬታቸው እንዲነሱ የተደረጉት የአካባቢው አርሶ አደሮች በቂ ካሳ አልተከፈለንም በሚል ምክንያት የደረሰውን የሸንኮራ አገዳ ምርት በእሳት በማጋየታቸው ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ፣ በመከላከያ ሰራዊት እና ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል በተደጋጋሚ በሚደረጉት ውጊያዎች የተነሳ በአካባቢው ባለው የፀጥታ መጓደል ነው።

በፋብሪካው በቂ የውሃ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሌለ የገለጹት ምንጮች፣ ፋብሪካው በመንግስት በኩል የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ከዚህ በኋላም በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ስራ ሊጀምር እንደማይችል ከፋብሪካው አስተዳደር በኩል መስማታቸውን ሰራተኞች ለዋዜማ አስረድተዋል። 

ከዚህ ቀደምም፣ የፌደራሉ መንግሥት “ኦነግ ሸኔ” ብሎ የሚጠራው እና በሽብርተኝነት የተፈረጀው ታጥቂ ቡድን በፋብሪካው ላይ በተደጋጋሚ በሚያደርሰው ጥቃት ምክንያት ምርት ለማቆም ሲገደድ መቆየቱንም ገልፀዋል። 

በዚኽ መሰሎቹ ተደጋጋሚ  ጥቃቶች በርካታ የፋብሪካው ተሽከርካሪዎች በእሳት መቃጠላቸውን እና ሌሎች ንብረቶችም ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን ሰምተናል። 

የአርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ  በምስራቅ ወለጋ ዞን በዲዴሳ ሸለቆ ውስጥ፣ ከአዲስ አበባ-ነቀምት-በደሌ በሚወስደው መንገድ በ395 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ እንደሚገኝ ከኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ

ከተመሰረተ 45 አመታትን ያስቆጠረው ነባሩ  የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በመስከረም ወር ስራ እንደሚጀምር ቢጠበቅም አልተሳካለትም። በተጨማሪም በመንግስትና ኦነግ ሸኔ መካከል በሚፈጠረው ተደጋጋሚ ግጭት መደበኛ ተግባሩን ማከናወን አልቻለም። ዋዜማ ጉዳዩን ከድርጅቱ ሰራተኞች ጠይቃ ለመረዳት ሞክራለች።

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የሚገኘው ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ፣ በወቅቱ የሚያስፈልገው ጥገና ሊደረግለት ባለመቻሉ እና ፋብሪካው በዋናነት ጥቅም ላይ የሚያውላቸው፣ ፋይቭራዘር እና ሸራውድ የተሰኙት ማሽኖች ከአገልግሎት ውጪ በመሆናቸው ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ስራ ማቆሙን የፋብሪካው ሰራተኞች ለዋዜማ ተናግረዋል። 

ፋብሪካው ከዚኽ ቀደም ባለው ልምድ መሠረት፣ ክረምት ላይ ጥገና ተደርጎለት መስከረም ወር ላይ ወደ ሥራ ይገባ እንደነበር የገለፁት ምንጮች፣ አኹን ላይ ግን አስፈላጊ የሚባሉት የማምረቻ ቁሳቁሶች ጭምር ባለመሟላታቸው ስራ ማቆሙን ገልፀዋል። 

ፋብሪካው ስራ ያቆመው በቀደመው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ እንደሆነ የጠቀሱት የፋብሪካው ሰራተኞች፣ አስፈላጊዎቹ ማሽኖች ተሟልተው፣ ፋብሪካው ወደ ስራ እንዲገባ በተደጋጋሚ ጥያቄያቸውን ለፋብሪካው አስተዳደር ቢያቀርቡም፣ ማሽኖቹ ከውጭ እንደሚገቡ እና እስከዛሬ የዘገየቱም በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት እንደሆነ ሲነገራቸው ከመሰንበቱ ውጪ በተግባር የተደረገ ነገር እንደሌለም ጠቁመዋል።

ፋብሪካው ከ35 ሺ ሄክታር በላይ የሸንኮራ አገዳ ማልሚያ መሬት ቢኖረውም፣ በአካባቢው ባለው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር የተነሳ ለስኳር  ምርት ግብአት የሚሆነውን የሸንኮራ አገዳ እንደሚፈለገው ለፋብሪካው ማቅረብ አለመቻሉም ለዚህ መሰሉ የምርት ማሽቆልቆል አንዱ ምክንያት መሆኑም ተጠቅሷል። 

የሸንኮራ አገዳውን ለማምጣት፣ ፋብሪካው ካለበት ቦታ ከ35 እስከ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ያህል መጓዝ እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት ሰራተኞቹ፣ በዚያ አካባቢ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል ከፍተኛ ውጊያ በመኖሩ የተነሳ፣ ያንን ማድረግ አለመቻሉን ተናግረዋል። 

በፋብሪካው ከ2 ሺ 700 በላይ ቋሚ እና ከ 8 ሺ በላይ ጊዜያዊ ሰራተኞች እንዳሉ የተገለፀ ሲሆን፣ ፋብሪካው አስፈላጊው ጥገና ተደርጎለት በቅርቡ ስራ የማይጀምር ከሆነ ደሞዛችን ሊቆም ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዳሉ ለዋዜማ ተናግረዋል። 

በአካባቢው የሚኖሩ ከ70 ሺ በላይ ሰዎችም ህልውናቸው ከዚሁ ፋብሪካ ጋር የተገናኝ እንደመሆኑ፣ ወደ ስራ የማይገባ ከሆነ የእነዚህ ነዋሪዎች ሕይወትም አደጋ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ዋዜማ ለመረዳት ችላለች። 

ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ

በአማራ ክልል አዊ ዞን የሚገኘው ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካም በኃይል አቅርቦት ችግር የተነሳ ስራ ማቆሙን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። 

ፋብሪካውን ለማንቀሳቀስ የሚያስችለው የኤሌክትሪክ ኃይል ጣቢያ ከአንድ ዓመት በፊት በተፈፀመበት የመለዋወጫ ዕቃዎች ስርቆት ምክንያት፣ ፋብሪካው እስካሁን ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለማግኘቱ ስራ ማቆሙንም ዋዜማ ተረድታለች። 

ፋብሪካው ባለፈው ዓመት እስከ ግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ድረስ በነዳጅ አማካኝነት ሲያመርት ቢቆይም፣ ክረምቱን ከተደረገለት ጥገና በኋላ ወደስራ አልተመለሰም።

የኃይል አቅርቦት ችግሩ ባለመስተካከሉ ምክንያት በቀጣይ ጥር ወር ስራ ይጀምራል እንደተባሉ የገለጹት ምንጮች፣ ይኽ ግን በቀላሉ የሚሳካ አይመስልም ብለውናል። 

ከዚኽ በተጨማሪም፣ ለፋብሪካው ምርት በግብዓትነት የሚውለውን የሸንኮራ አገዳ ለማመላለስ ያገለግል በነበረው የጋሪ ቁጥር ላይ ከፍተኛ እጥረት ማጋጠሙን የጠቀሱት ምንጮች፣ ይኽም ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ስራ ለማቆሙ ሌላኛው ምክንያት ነው ሲሉ ለዋዜማ ተናግረዋል። 

ከአንድ ሺ አምስት መቶ በላይ የሚሆኑት ቋሚ የፋብሪካው ሰራተኞች፣ አሁን ላይ መደበኛ ስራቸውን አቁመው ከፋብሪካው ጋር የተያያዙ የተለያዩ የጥገና ሥራዎችን በመስራት ላይ ብቻ መወሰናቸውንም ዋዜማ ተገንዝባለች። 

በ2013 ዓ.ም. የግንባታ ስራው ተጠናቆ የሙከራ ምርት የጀመረው ጣና በለስ የስኳር ፋብሪካ፣ ሥራ ከማቆሙ በፊትም በሸንኮር አገዳ ግብዓት እጥረት የተነሳ በሙሉ አቅሙ ለመስራት ሲቸገር እንደነበር ሲገለፅ ቆይቷል። [ዋዜማ] 

የዋዜማ ዝግጅት ክፍልን በwazemaradio@gmail.com ኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል