ዋዜማ- ከሶስት ዓመት በፊት በደኅንነት ስጋት ምክንያት ሥራውን ያቋረጠው የፈረንሳይና የአይስላንድ ኩባንያዎች ጥምረት የሆነው የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ፕሮጀክት ወደ ሥራ ለመመለስ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተደራደረ ነው፡፡

ዋዜማ የተመለከተችውና ከማዕድን ሚኒስቴር የተገኘው ሠነድ እንደሚያመላክተው፤ የኢትዮጵያ መንግሥትና ኩባንያው በመካከላቸው የነበረውን የክስ ሂደት አቋርጠው በአፋጣኝ ወደ ሥራ ለመግባት በቅርቡ ስምምነት ተፈራርመዋል። በአሁኑ ወቅት ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ማዕድን ሚኒስቴር፣ ፍትሕ ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የኃይል ግዥ እና የኢንቨስትመንት ስምምነቶችን የማሻሻል ድርድር እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን፤ በቅርቡ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

‹‹ከቱሉ-ሞዬ ጂኦተርማል ፒ ኤል ሲ ጋር የነበረው የክስ ሂደት ተቋርጦ ወደ ሥራ እንዲገቡ በሀገሪቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች አቅጣጫ ተሰጥቶበት በኩባንያው ከፍተኛ ሼር ካለው ሜርዲየም እና በመንግስት (ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ማዕድን ሚኒስቴር፣ ፍትህ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል) ድርድር ቢጀመርም ሂደቱ ተጓትቶ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ከፍተኛ ክትትል በማድረግ ድርጅቱ በአፋጣኝ ወደ ስራ እንዲገባ ለማስቻል ከድርጅቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በመወያየት በጊዜያዊነት አለመግባባትን የማቆም ስምምነት በመፈራረም የኃይል ግዢ ስምምነት ማሻሻያ ድርድር እየተደረገ ነው፡፡ በቅርቡም የመግባቢያ ስምምነት (Letter of Intent) ከመንግሥት ጋር በመፈራረም ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት ላይ ይገኛል›› ሲል ያትታል የማዕድን ሚኒስቴር ሰነድ፡፡

በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የአስተዳደር ዘመን የወጣውን ዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦት መርሃ ግብር መነሻ በማድረግ፣ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን 500 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የተለያዩ የቁፋሮ ሥራዎችን ሲያካሂድ የነበረውና በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር መዋዕለ ንዋይ የተመደበለት የቱሉ-ሞዬ ጂኦተርማል ኩባንያ፤ ‹‹ፕሮጀክቴ ላይ በታጣቂዎች ጥቃት ደርሶብኛል›› በማለት ሥራውን አቋርጦ ከኢትዮጵያ የወጣው ከሶስት ዓመታት በፊት በ2015 ዓ.ም ነበር።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኩባንያው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በሕግ ክርክር ላይ ቆይቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት በአካባቢው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን አሰማርቶ አካባቢው በጥንቃቄ እንዲጠበቅ ማድረጉን በመጥቀስ የተከራከረ ሲሆን፤ የፈረንሳዩ ሜሪዲያም ኩባንያ ግን በትልቁ ባለድርሻነቱ (ባለአክሲዮን) ክሱን ገፍቶበት፣ የደረሰበትን የኪሳራ ኢንሹራንስ ክፍያ ከዓለም ባንክ የባለብዙ ወገን የኢንቨስትመንት ዋስትና ባለሥልጣን (MIGA) እንዲከፈለው ጠይቆ ነበር።  

ሆኖምበአሁኑ ወቅት ድርጅቱና የኢትዮጵያ መንግሥት ክሱን ለማቋረጥ ተስማምተው ፕሮጀክቱን እንደገና ለማስጀመር ድርድሮችን እያካሄዱ ነው፡፡ የቱሉ-ሞዬ ሌላኛው ባለአክሲዮን የአይስላንዱ ሬክጃቪክ ጂኦተርማል የተባለው ኩባንያ ነው።

በሌላ በኩል፣ ሥራ አቋርጦ የነበረው ሌላኛው ኮርቤቲ ጂኦተርማል ኩባንያ የኃይል ግዥ ስምምነት የዋጋ ተመኑን እንደገና ለማሻሻል ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ድርድር እያደረገ መሆኑን ሰምተናል።

ኮርቤቲ ጂኦተርማል ኩባንያ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሥራው በመዘግየቱና ይህም በኃይል ግዥ እና በፕሮጀክት ትግበራ ስምምነቶቹ ላይ ተፅዕኖ በማሳደሩ ሥራውን ሙሉ በሙሉ አቋርጦ የነበረ ሲሆን፤  በቅርቡም ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አመራሮች ጋር ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡ ኩባንያው ያለበትን የገንዘብ እጥረት ችግር ለመወጣት ፔሬንኮ ግሩፕ በተባለው ግዙፍ ዓለም አቀፍ ተቋም ሥር ከተመሠረተው ታራኒስ ኦፕሬሽንስ ኩባንያ ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል። በዚህም መሠረት ሥራውን ለመቀጠል ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ቀደም ሲል የነበሩት የኃይል ግዥና የትግበራ ስምምነቶችን በማደስ የቁፋሮ ሥራዎችን በአስቸኳይ ለመጀመር በሂደት ላይ ይገኛል።

ምንጮች እንዳረጋገጡት፤ ድርጅቱ ሥራውን በዋናነት ያቋረጠበት ምክንያት ከደኅንነቱ ሥጋት ባሻገር በኃይል ግዥ ስምምነት የዋጋ ተመን (PPA) ላይ በነበረ አለመግባባት ሲሆን፣ አሁን በዋነኝነት ድርድሩ እየተደረገ ያለውም ይህንን የኃይል ሽያጭ ዋጋ ከፍ ለማድረግ እንደሆነ ታውቋል።

ኩባንያው በሁለት ፈቃዶቹ ላይ በገባው ውል መሠረት የምርመራ ሥራ አለማከናወኑ በመረጋገጡ እና ሪፖርቶችንም ባለማቅረቡ ውሉ ተሰርዞ ቆይቷል። [ዋዜማ]