Alemu Sime (PhD) -FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚንስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) የሲቪል ማህበራት ተወካዮችን አርብ ዕለት ሰብስበው በሰጡት ማብራሪያ መንግስት የሲቪል ማህበራቱ  ያወጡት መግለጫ  ስህተት  ነው ብሎ እንደሚያምንና እርምት በማያደርጉት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል። 

ጳጉሜ 1 ቀን  35 አገር በቀል ሲቪል ማኅበራት “በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልል ያለው ጦርነት እና በሌሎችም አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች” በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ የመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት እንዲቀጥልና ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀርብ ያቀረቡት “አስቸኳይ የሰላም ጥሪ” ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት የተጋረጠባትን አደጋ ያላገናዘበ፣ በህወሃት የተፈጸመውን ጥፋት ያልገለጸ ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ነቅፈዋል።

አርብ ጳጉሜን 4፣ 2014 ከሰዓት በኋላ በኢሊሌ ሆቴል በተደረገውና በአጭር ጊዜ በተጠራው ስብሰባ ከመቶ በላይ የሲቪል ማኅበራት ወኪሎች መገኘታቸው ታውቋል። ስብሰባው ለሚዲያ ዝግ የነበረ ቢሆንም ወደኋላ ላይ የኢቢሲ ጋዜጠኞች ሳይገቡ እንዳልቀሩ ታዳሚዎች ተናግረዋል። 

በዚህ ስብሰባ ላይ አለሙ ስሜ ያደረጉት ወቅታዊውን ሁኔታ በማብራራት ቢሆንም ዋና ትኩረቱ ግን  መንግስት ሲቪል ማኅበራቱ ባወጡት መግለጫ ላይ የተሰማውን ቅሬታ ና ቁጣ መግለጽ ነበር። ሚኒስትሩ አክለውም ሲቪል ማኅበራቱና ድርጅቶቹ ከህወሃት ጋራ በሚደረገው ጦርነት መንግሥት መደገፍ ካልቻሉ ወይም ካልፈልጉ “ዝም ብለው የተመዘገቡበትን ስራ” ብቻ እንዲያከናውንና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግልጫ ከመስጠት እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል። ከዚህ ውጭ “አንፈቅድም” ብለዋል። ሁሉም በተመዘገበበት መስክ ከመስራት ውጭ፣ “መከላከያ ሲዋጋ ሐሞት የሚያፈስ መግለጫ” ለሚያወጡ “ቶለራናንስ (ትዕግስት)” እንደሌለ የገለጹት አለሙ ስሜ (ዶ/ር) “የሚያጠፋውን ተከታትለን በጋራ እናርማለን፣ ከዚያ ያለፈ እርምጃ የሚያስፈልገውን ለኢትዮጵያ ስንል [እርምጃ] እንወስዳለን” ብለዋል በንግግራቸው ማሳረጊያ። 

ዋዜማ ባሰባሰበቸው መረጃ የሲቪል ማኅበራቱ ተወካዮች በሁለት የተከፈለ አቋም እንዳንጸባረቁ ተረድታለች። ጦርነቱን በተመለከተ መንግሥትን ሙሉ በሙሉ የሚደግፉ አስተያተቶችና ጥያቄዎችን ያቀረቡ ተወካዮች ድምጻቸው ጎላ ብሎ ተሰምቷል። ከዚህ አልፎ ለብልጽግ ና ፓርቲ እና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የጻፏቸውን ግጥሞች ያነበቡ አንድ የመያድ ተወካይ እንደነበሩ ተሰምቷል። ሲቪል ማኅበራትን “የፈረንጅ ፍርፋሪ ለማግኘት” የሚጥሩ በማለት በከሃዲነት የከሰሱ በመንግስት ደጋፊነታቸው የሚታወቁ ተወካዮችም ድጋፋቸውን በስሜት ከመግለጽ አልተቆጠቡም።  ለሚኒስትሩ ትንተናና አቋሞች ድጋፋቸውን በጭብጨባ ሲገልጹ የነበሩ የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ነበሩ። 

በተቃራኒው የሚኒስትሩ ንግግርና የስብሰባው ድባብ “አስጨናቂና አሳሳቢ” የሆነባቸው እንደነበሩ ካነጋገርናቸው ታዳሚዎች ተረድተናል። በሚንስትሩ አቋም እና በሌሎች አስተያየቶች ያዘኑ አንድ ታዋቂ የሕግ ባለሞያ፣ የሰላም ጥሪ  መግለጫውን በፈረሙት ድርጅቶች ላይ የቀረበውን ነቀፋ በመቃወም “ድርጅታችንን ልትዘጉት ትችላላችሁ። ይህ ቀን ግን ያልፋል። ይህ ቀን እንደሚያልፍ አትርሱ…ሁሉም ነገር በሕግ አግባባ ብቻ ቢያዝ ሁላችንንም ይጠቅማል” በማለት ተናግረዋል። ከፈራሚዎቹ ድርጅቶች አንዱ የሆነ ሌላ ድርጅት ባልደረባ የሰላም ጥሪው የትግራዩን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ግጭቶች የሚመለከት መሆኑን፣ ጥሪውም ለመንግስት ብቻ ሳይሆን ለተሳታፊዎቹ ሁሉ  መሆኑን ማስረዳታቸውን ሰምተናል። አንዲት ሴት ተሳታፊ በበኩላቸው፣ ድርጅቶቹ የፓርቲ ወገንተኘነት እንደሌላቸው መናገራቸው ሚኒስትሩ ጉዳዩ የፓርቲ ሳይሆን የአገር ህልውና ጉዳይ ነው የሚል ረጅም ማብራሪያ እንዲሰጡ አድርጓቸዋል። 

የሲቪል ማህበራቱ በመግለጫቸው ሕወሓትንና የፌደራሉን መንግስት እኩል ጥፋተኛ በማድረግ “ተፋላሚ ወገኖች”  ሲሉ መግለጻቸውን አምርረው የተቹት ሚንስትሩ  መንግስት እንዴት ሀገር ሊያፈርስ ከተነሳ “ወንበዴ”  እኩል ይታያል? ሲሉ ጠይቀዋል። “ወያኔን ማጋለጥ የማትችሉ ከሆነ፣ የምትፈሩ ከሆነ ተዉት። የወያኔን አስከፊ ገጽታ መናገር የማትችሉ ከሆነ ተዉት፣ ዝም በሉ። እናንት ስትፈሩ፣ ተፋላሚ ስትሉ ዩኤን ወያኔ ይህን ያህል ነዳጅ ዘረፈችብኝ ብሏል።” ሲሉ ማኅበራቱን ተችተዋል። 

“በዚህ ጊዜ ሃይል የሚበታትን ነገር አንፈልግም። ለመደገፍ ሞራል ካጣችሁ፣ ፍላጎት ካጣችሁ ዝም በሉ። ፈቃድ የወሰዳችሁበትን ስራ ዝም ብላችሁ ስሩ” በማለት አስጠንቀዋል።  ሲቪል ማህበራቱ በጦርነቱ ጉዳይ ራሳቸውን ገልልተኛ አድርገው ለማቅረብ ባደረጉት ሙከራ መንግስት ማዘኑን የገለፁት አለሙ፣ ጉዳዩ የፖለቲካ አጀንዳ ወይም የፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራም ልዩነት አይደለም፣ ይልቁንም የኢትዮጵያ ጠላቶች ከውስጥ ተባባሪዎቻቸው ጋር ሀገራችንን ለማደከምና ለማፍረስ የሞከሩት ሴራ መሆኑን በማንሳት የማኅበራቱን ገለልተኝነት ጉዳይ ጠይቀዋል። አለሙ ስሜ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለህወሃት የሚያሳዩትን ድጋፍ በመጥቀስ የገለለተኝነት ጥያቄ ችግር ያለበት ጉዳይ መሆኑን ሞግተዋል።

ከህወሃት ጋር የሚደረገው ጦርነት የመንግስትና የፓርቲ ጉዳይ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ መሆኑን አብራርተው “የሀገር ህልውና አይመለከተኝም የሚል ሲቪል ማህበረሰብ ካለ ፈቀዱን መነጠቅ አለበት”  ሲሉ ተደምጠዋል ሚንስትሩ። “ወይ [የህወሃት ጥቃት] ሀገር ላይ የተቃጣ አይደለም የራሳችሁ ጉዳይ ነው በሉና ንገሩን። በግልፅ መነጋገር ያስፈልጋል። እያንዳንዱ አቋሙን ይግለፅ። ኢትዮጵያዊነት የሚፈተነው፣ እውነትና የሀገር ፍቅር የሚፈተነው እንዲህ ባለ ጊዜ ነው፣ እንነጋገር”  ብለዋል አለሙ ስሜ በንግግራቸው መግቢያ። 

ሲቪል ማህበራቱ ያወጡት መግለጫ ሁሉም አምነውበት እንዳልሆነና “አብዛኞቹ ተታለው ነው”  ያሉት ሚንስትሩ፣ ማህበራቱ በጋራ ምክር ቤታቸው ተወያይተው የጋራ አቋም መያዝ እንደሚችሉ ካልሆነም በተናጠል ራሳቸውን ችለው መግለጫ ማውጣት እንደሚችሉ መክረዋል። አለሙ አታለሉም ሆነ ተታለሉ ያሏቸው ድርጅቶች የትኞቹ እንደሆኑ አልገለጹም። ይህ ዜና እስከተዘጋጀበት ቅዳሜ እኩለ ቀን ድረስ፣ ተታልዬ ፈርሜያለሁ ያለ ድርጅት ወደ አደባባይ አልመጣም። መግለጫውን ከፈረሙት ድርጅቶች መካከል ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ሃላፊዎች፣ የመግለጫውን ረቂቅ በድርጅቶታቸው ውስጥ አይተው ውይይት ማድረጋቸው ማንም እንዲፈርሙ እንዳላግባባቸው ለዋዜማ ገልጸዋል። የሚኒስትሩን ንግግር እንደማስፈራሪያ የቆጠሩት ሌላ ሐላፊ፣ “የሰላም ጥሪውን መግለጫ” የሚቃረን ሌላ መግለጫ ይወጣል ብለው እንደሚጠብቁና በሲቪል ማኅበራቱ መካከል ያለው ልዩነት ሊሰፋ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ሲቪል ማኀበራቱ ጳጉሜ 1 ቀን በኢንተር ለግዠሪ ሆቴል ጠርተውት የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ “የመንግሥት አካል ነን” ባሉ ግለሰቦች፣ ባልተገለጸ ምክንያት እንደተከለከለ በወቅቱ ተገልጾ ነበር። ሚኒስትሩ ግን ጋዜጣዊ መግለጫው እንዴት እንደተከለከለ እንደማያውቁ ለተሰብሳቢዎቹ ተናግረዋል።  መግለጫው የዚያኑ ዕለት በዙም መካሄዱንና ጋዜጠኖች ተገኘተው እንደነበር ዋዜማ አረጋግጣለች።  

ድርጅቶቹ ባለፈው ሳምንት ባስተላለፉት “አስቸኳይ የሰላም ጥሪ” አገር በቀል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልል ያለው ጦርነት እና በሌሎችም አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች በአስቸኳይ ቆመው፣ ሐቀኛ፣ ሰላማዊና የግጭቶቹ ተሳታፊ አካላትን በሙሉ ያካተቱ የእርቅ ንግግሮች እንዲጀመር ጠይቀው ነበር።

መግለጫቸው አክሎም ከሰሜኑ ጦርነት ባሻገር በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በአንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢዎች ግጭቶች የበርካታ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፉ እና የአካል ጉዳት እያስከተሉ መሆኑን ያትታል። ሴቶች መደፈርና ሌሎችም ዘግናኝ ጥቃቶች እየተፈፀሙባቸው ይገኛልም ብለዋል። ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ካልተፈቱ አገራችን መውጣት የማትችልበት ቀውስ ውስጥ ትገባለች የሚል ስጋት እንዳላቸውም ገልጸው ነበር።  የትግራዩ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ አገር በቀል ሲቪል ማኅበራት በጋራ የሰላምጥሪ ሲያቀርቡ ይህ መግለጫ ሁለተኛቸው ነው [ዋዜማ ራዲዮ]