Addis Ababa, Ethiopia: office buildings in the central business district – photo by M.Torres
  • የግል ባንኮች ለአንድ የአሜሪካ ዶላር የሚጠይቁት ኮሚሽንም 38 ብርን አልፏል 

ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገበያ የይፋዊ ወይንም የባንኮች እና የጥቁር (የትይዩ) ገበያ የምንዛሪ ዋጋ ልዩነት ከፍ ያለ ጭማሪ ማሳየቱን ዋዜማ ያሰባሰበችው መረጃ ያመለክታል።

ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ሆቴል እና ሌሎች የጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ ግብይት የሚፈጸምባቸው አከባቢዎችን ተዘዋውረን እንደተመለከትነው እስከ ሰኞ ዕኩለ ቀን አንድ የአሜሪካን ዶላርን ይዞ ለሚሄድ ግለሰብ 90 ብር ይከፈለዋል።

ከነዚሁ የትይዩ ገበያዎች የውጭ ምንዛሪን መግዛት የፈለገ ግለሰብም 91 ብር ከ50 ሳንቲም መክፈል ይጠበቅበታል። ከሰሞኑ ባለ ዋጋም የይፋዊ እና የትይዪ ገበያ የአንድ የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ከ37 ብር በላይ ልዩነት አለው።

በቅኝታችን እንደተረዳነው በባንኮች በኩል የሚቀርብ የውጭ ምንዛሪ በእጅጉ እየቀነሰ በመምጣቱ እና የትይዩ ገበያ ፍላጎት በእጅጉ እየናረ ይገኛል።

ባለፈው ዓመት መጀመሪያ መንግስት ባንኮች ከሚሰበስቡት የውጭ ምንዛሪ 70 በመቶውን ለብሄራዊ ባንክ በእለታዊው ዋጋ እንዲሸጡ እና 30 በመቶውን ባንኮቹ እና የውጭ ምንዛሪውን ያመጡት ባለሀብቶች እንዲካፈሉት ካደረገ በኋላ በመንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ለግሉ ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ ያቀርባል ተብሎ ቢጠበቅም መንግስት የውጭ ምንዛሬ ክፍፍል ህጉን ከአለም አቀፍ አበዳሪዎች የተስተጓጎለበትን የፋይናንስ አቅርቦት ለማካካስ እንዲጠቀምበት ሳያስገድደው እንዳልቀረ የባንክ ዘርፍ ምንጮቻችን አስረድተውናል።

ይህም የትይዩ ገበያ ፍላጎትን በማናር የምንዛሪ ውድነትን አምጥቷል።

በኢትዮጵያ ለሚታየው የዋጋ ንረት መንስኤዎች ውስጥም መንግስት የሚያደርገው የብርን የምንዛሪ ተመን ማራከስና የጥቁር ገበያ የምንዛሬ ዋጋ መናር ይጠቀሳሉ።

በተለይ ነጋዴዎች ያለ ምንም የባንክ የውጭ ምንዛሪ ፍቃድ(ፍራንኮ ቫሎታ) ባገኙት የውጭ ምንዛሬ መሰረታዊ ምርቶች እንዲያመጡ መፈቀዱ ነጋዴዎችን እየናረ በመጣው የጥቁር ገበያ ምንዛሪን እየገዙ ምርት እንዲያስገቡ መንገድን በመክፈቱም የገቢ እቃዎች ላይ የዋጋ መወደድን አምጥቷል። ከውጭ የሚገቡ የምግብ ዘይት ፣ የግንባታ እና መሰል እቃዎች ላይ ከባድ የዋጋ ጭማሬ የመጣውም በዚሁ ሳቢያ እንደሆነ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

በእርግጥ የኢትዮጵያ የነሐሴ ወር አጠቃላይ የዋጋ ንረት ወደ 32.5 ዝቅ ማለቱን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ባወጣው መረጃ ገልጧል። ወርሃዊው የዋጋ ንረት 35 በመቶ ከነበረበት ሰኔ ወር ጀምሮ ቅናሽ ሲያሳይ የአሁኑ ለሦስተኛ ጊዜ ነው። የዋጋ ንረቱ የቀነሰው፣ በተለይ የምግብ ዋጋ ንረት በሐምሌ ወር ከነበረበት የ35.5 በመቶ ቀንሶ በነሐሴ ወር ወደ 33.2 በመቶ ዝቅ በማለቱ እንደሆነ ባለሥልጣኑ ጠቅሷል። የምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ ንረት ግን፣ በሐምሌ ከነበረበት ዋጋ ንረት በ1.1 በመቶ ጨምሮ በነሐሴ ወደ 31.5 በመቶ ደርሷል። .

በሌላ በኩል በግል ንግድ ባንኮች እየቀረበ ያለው አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ ላይ የሚጠየቀው ኮሚሽን ለአንድ የአሜሪካ ዶላር እስከ 38 ብር መሆኑም ሌላው ችግር ነው። ባንኮች ለውጭ ምንዛሬ ጠያቂዎች የውጭ ምንዛሪ ካላቸው ደንበኞቻቸው ጋር አገናኝተው ለማቅረብ ለአንድ ዶላር የይፋዊ ዋጋው 52.51 ብር ላይ 38 ብር ኮሚሽን እየጨመሩ በጥቅሉ ለአንድ የአሜሪካ ዶላር እስከ 90 ብር ያስከፍላሉ።ይህን ከፍለው ምርቶችን የሚያመጡ ነጋዴዎችም ወጪያቸውን በተጠቃሚው ላይ የሚያካክሱ በመሆኑ የዋጋ ንረት ፈጣሪ ሆኗል።

ኢትዮጵያ ባለፈው በጀት ዓመት ከሁሉም የውጭ ምንዛሪ ምንጮች ከ20 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ብታገኝም ጦርነትና ግጭት እንዲሁም ምዕራባውያን ሀገራት መንግስት ላይ ጫና በመፍጠራቸው ኢኮኖሚው ላይ ደንቃራ መሆኑን የመንግስት መረጃዎች ያመለክታሉ። [ዋዜማ ራዲዮ]