ዋዜማ ራዲዮ- የሰላም አማራጭ ዐቢይ ኮሚቴ፣ ከሕወሃት ጋራ ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቀው የሰላም ድርድር አስፈላጊ ነው ያለውን የመንግሥት አቋምና ፍላጎት የሚያብራራ “የሰላም ሐሳብ ይሁንታ” (ፕሮፖዛል) ማዘጋጀቱን ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 11 ቀን ዓ.ም አሳውቋል። ይህ ሰነድ ሰሞኑን ለአፍሪካ ህብረት እንደሚቀርብ የኮሚቴው አባላት በአዲስ አበባ ተቀማጭ ለሆኑ የተለያዩ ሀገራት ለዲፕሎማቶች በሰጡት ማብራሪያ አረጋግጠዋል።

አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት በአደራዳሪነት የመሳተፋቸውን ሐሳብ መንግስት አሁንም አለመቀበሉ በውይይቱ ተገልጧል። የኮሚቴው አባላት “ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ” በሕወሃት ላይ በቂ ጫና አላደረገም፣ ለጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅት እያየ እንዳላየ ማለፍን መርጧል ሲሉ መተቻተውን ዋዜማ ሰምታለች።


የአፍሪካ ኅብረት በመንግስትና በሕወሃት መካከል የታሰበውን ድርድር በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ የማስጀመር እቅድ እንዳለው አስቀድሞ መዘገቡ ይታወሳል። ደመቀ መኮንን፣ ሬድዋን ሑሴን እና ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በጋራ ለዲፕሎማቶቹ እንደነገሩት፣ መንግሥት ድርድሩ ሁሉም አካላት የሚያከብሩት ዘላቂ የተኩስ አቁም የሚያቋቋም ስምምነት የሚደረስበት እንዲሆን ይፈልጋል።

የመንግስት ዋና ፍላጎት ወደ ሌላ ጦርነት እንዳይገባ ማድረግ ነው መባሉን ዋዜማ ሰምታለች። በውይይቱ የተሳተፉ ዲፕሎማት ለዋዜማ እንደገለጹት፣ መንግሥት ከህወሃት ጋር የሚደረገው ድርድርና የሰላም ስምምነት በሃገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ስራ ይካተታሉ ተብለው የሚጠበቁ ውስብስብ ፖለቲካዊና አገራዊ ጉዳዮችን ለመፍታት ያግዛል የሚል እምነት አንጸባርቋል።


በገለጻው ላይ የተገኙት ዲፕሎማቶች የተለያዩ ጥያቄዎች ማንሳታቸውን ዋዜማ ከዲፕሎማቲክ ምንጮች ተረድታለች። ከሌሎች ታጣቂ ቡድኖች በተለየም ከሸኔ ጋራ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ለቀረበ ጥያቄ በተሰጠ ማብራሪያ ታጣቂዎቹ በዋናነት የሚረዱት በሕወሃት በመሆኑ ከእርሱ የሚደርገው ድርድር ከተሳካ ሌሎቹ ታጣቂዎች ወደ ሰላም የሚመጡበት እድል እንደሚኖር መነገሩን ዲፕሎማቶቹ ጠቅሰዋል።


ዲፕሎማቶቹ፣ መንግሥት የአፍሪካ ኅብረት ዋና አደራዳሪ መሆን አለበት በሚል የያዘው አቋም ቅድመ ሁኔታ ይመስላል ብለው ጠይቀው ነበር። አደራዳሪነቱን በተመድ ወይም በሌላ አካል የመተካትን ሐሳብ አንድ የአውሮፓ ዲፕሎማት አንስተዋል።

የሰላም አማራጭ ዐቢይ ኮሚቴው አባላት የአፍሪካ ኅብረት ጉዳይ የመርህ እንጂ የቅድመ ሁኔታ ጉዳይ እንዳልሆነ አብራርተው፣ መንግሥታቸው በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይም ተመሳሳይ መርህ መከተሉን እንደጠቀሱ በስብሰባስ የተገኙ ምንጮች ነግረውናል።

አንድ የኮሚቴው አባል፣ በአፍሪካ ሕብረት ድርድሩን የመምራት አቅምና ፍላጎት ላይ መንግሥት እንደሚተማመን ተናግረዋል። ኅብረቱ ወይም የሚሰይማቸው መልእክተኖች አቅም እና ገለልተኝነት ይጎድላቸዋል በሚል በህወሃት በኩል ተደጋጋሚ ቅሬት መቅረቡ ይታወሳል።


የመንግሥት ተወካዮች ተመድም ሆነ አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት በአደራዳሪነት ለመሳተፍ ያላቸውን ፍላጎት አሁንም እንዳልተቀበሉት የገለጹት በተዘዋዋሪ ነው፣ ዋዜማ እንደሰማቸው። “ድርድሩን በቴክኒክና በገንዘብ ልታግዙ ትችላላችሁ” የሚል መልስ ተሰጥቷል።


በትግራይ እና በአማራ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን አወዛጋቢ አካባቢዎች በተመለከተ ዲፕሎማቶቹ ጠይቀዋል።

የመንግስት ተወካዮች፣ ዘላቂ ተኩስ አቁምና ስምምነት ሳይደረስ ሌሎች ጉዳዮችን መነጋገርም ሆነ መፍታት አይቻልም የሚል መልስ ሰጥተዋል።

ሕወሃት ጦርነት ለመጀመር እየተዘጋጀ ነው ብለው የከሰሱት የኮሚቴው አባላት፣ ለሕወሃት መሳሪያ የሚያቀብሉት እነማን እንደሆኑ መንግስት እንደሚያውቅ ለዲፕሎማቶቹ በሰጡት ማብራሪያ ጠቅሰዋል። በውይይቱ ሕወሃት ጦርነት ሊጀምር ይችላል የሚል ግምትና ስጋት መንጸባረቁን የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል።


የስልክ፣ ኤሌክትሪክ፣ ባንክ፣ ኢንተርኔትና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች ለማስጀመር የድርድሩን ውጤት ትጠብቃላችሁ ወይስ ከወዲሁ ለመልቀቅ ታሳባላችሁ የሚል ጥያቄም ቀርቦ ነበር። አገልግሎት ማስጀመር የድርድሩ አካል አይደለም፣ ሆኖም አገልግሎቶቹን ማስጀመር ራሱ ምክክርና ትብብር የሚፈልጉ ብዙ የዝግጅት ስራዎችን ይፈልጋል ሲሉ ነው መልሰዋል አንደኛው የመንግስት ተወካይ። አገልግሎች ሰጪ ተቋማት ውይይቱ እንደጀመረ ሥራቸውን ለመጀመር የሚያስችላቸውን ዝግጅት እንዲያደርጉ መታዘዛቸው በወቅቱ መነገሩን ዋዜማ አውቃለች።

መንግሥት ከሕወሃት ጋር እንዲደራደር በሰኔ ወር ያቋቋመውን የሰላም አማራጭ ዐቢይ ኮሚቴ የሚመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ሲሆኑ፣ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፣ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን፣ ተመስገን ጥሩነህ፣ አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር፣ ጌታቸው ጀምበር እና ሌ/ጀኔራል ብርሃኑ በቀለ ደሞ በአባልነት ተካተውበታል። ሕወሃትም ተደራዳሪ ቡድን ማቋቋሙን ዘግየት ብሎ በሐምሌ አጋማሽ ገደማ ለውጭ ዜና ምንጮች ተናግሯል። የቡድኑን አባላት ማንነት እና ብዛት ግን ሕወሃት እስካሁን ይፋ አላደረገም። [ዋዜማ ራዲዮ]