FILE
  • ሁለተኛው ተርባይንም ሀይል ለማመንጨት ዝግጁ ሆኗል

ዋዜማ ራዲዮ- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሶስተኛ ዙር የውሀ ሙሌት ተጠናቆ ዛሬ ወይ ነገ በግድቡ አናት ላይ ውሀው ይፈሳል ተብሎ እየተጠበቀ መሆኑን ዋዜማ ራዲዮ ከግድቡ ግንባታ ከፍተኛ አመራሮች ሰምታለች።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመርያ ምዕራፍ  የውሀ ሙሌቱን ላለፉት ተከታታይ ሁለት የክረምት ወቅቶች ያደረገ ሲሆን በ2012 አ.ም የክረምት ወራት 4.9 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ ይዟል።

ባለፈው ክረምት ማለትም በ2013 አ.ም 13.4 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀን በእቅዱ መሰረት መያዝ የነበረበት ቢሆንም በሀገሪቱ በተለያዩ አቅጣጫዎች የተፈጠሩ ፖሊቲካዊ ቀውሶች የግንባታ እቃዎችን ወደ ስፍራው ማጓጓዝን ከባድ ስላደረጉት የተጠቀሰውን የውሀ መጠን ለመያዝ የግድቡ ቁመት መድረስ የነበረበት ከባህር ጠለል በላይ 595 ሜትር ላይ ባለመድረሱ እቅዱ አልተሳካም። ዋዜማ ራዲዮ ከታማኝ ምንጮቿ መስማት እንደቻለችውም ህዳሴ ግድብ ባለፈው አመት የክረምት ወራት 1.8 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ ነው መያዝ የቻለው።

በዚህኛው የክረምት ወቅት ግን የግድቡን ቁመት ከባህር ጠለል በላይ 600 ሜትር በማድረስ ተጨማሪ ከ14 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ በላይ በመያዝ በጥቅሉ ግድቡ ከ21 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ በላይ ውሀን የሚይዝ መሆኑንም ሰምተናል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ የሀይል ማመንጫ ተርባይን ተከላ እና ሙከራ ተከናውኖ ሀይል ለማመንጨት ዝግጁ መሆኑ ተነግሯል።

ከአምስት ወራት በፊትም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመጀመርያው የሀይል ማመንጫ ተርባይን ሀይል ማመንጨት መጀመሩ የሚታወስ ነው።እስካሁንም እንደሚያገኘው የውሀ መጠን የኤሌክትሪክ ሀይል እያመነጨ ነው።

ከዚህ የክረምት ወቅት ጀምሮ የሚከናወነው ሁለተኛው ምእራፍ ሶስተኛ ዙር የውሀ ሙሌት ለሶስት አመታት የሚከናወን ሲሆን የግድቡን ቁመት መሰረት በማድረግ ግድቡ በጥቅሉ 49 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ እስኪይዝ በየክረምት ወራቱ እንደሚሞላ የቀደሙ የእቅድ ሰነዶች ያሳያሉ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ 11 አመታት አልፈውታል። [ዋዜማ ራዲዮ]