state departmentዋዜማ ራዲዮ- አሜሪካ በኢትዮጵያ መንግስት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ መንግስት የሚወስዳቸው እርምጃዎች እንደሚያሳስባት አስታወቀች።

ቀጥተኛ የሆነ ተፅዕኖ በመንግስት ላይ ስለማያሳድር ቢቀርም ቢመጣም ምንም አይነት የረባ ተፅእኖ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ አያሳድርም ተብሎ በብዙዎች የሚታማው የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት መግለጫ የኢትዮጵይ መንግስት በዜጎች ላይ የሚያደርገውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ኮንኖ ዛሬ ውጥታል።

ጥቅምት 2 ቀን 2009 ዓ.ም በአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የህዝብ ግንኙነት እና ረዳት ፀሃፊ ጆን ኪርባይ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩትና ኋላም በፅሁፍ በተለቀቀው መግለጫ አሜሪካ እንዳስታወቀችው የኢትዮጵይ መንግሰት ለደረሰበት ተቃውሞ እና አመፅ ምላሽ ይሆን ዘንድ በሃገሪቷ ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ የሚመጣው ያለ ፍርድቤት ትዕዛዝ እስር፣የንግግር አፈና፣የኢንተርኔት አቅርቦት መቋረጥ እና የስዓት እላፊ በእጅጉ ያሳስባታል።

አዋጁም መብቶቹን በመገደብ እና በማፈን ላይ አተኩሮ የሚተገበር ከሆነም የችግሩን ጥልቀት እንደሚያባብሰው ጆን ኪርባይ ተናግረዋል።

ፖለቲካዊ ልዮነት ማክበር እና የሰዎችን መሰረታዊ ነፃነት ማክበር በኢትዮጵያ ለተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ምላሽ ነው ያለው መግለጫው በድጋሚ የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎችን ህገ መንግስታዊ የሆነውን በነፃነት የመናገር እና የመሰብሰብ መብት እንዲያከብር እንጠይቃለን ይላል።

በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን በመግለፃቸው እና በመሰብሰባቸው ብቻ ለእስራት የተዳረጉ ዜጎች እንዲፈቱ የጠየቀው መግለጫው የተቃውሞ ድምፆችን ማፈን እና ማሰር ራስን ለሽንፈት መዳረግ ነው ይላል።

የበርካታ ንፁሃን ዜጎች ህይወት መጥፋቱን እና ንብረትም መውደሙን ያስታወሰሰው መግለጫው ለተጨማሪ አመፅ እና ብጥብጥ ከሚዳርጉ ተግባራት ሁሉም ወገን እንዲቆጠብ ጠይቋል።

የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት በጥር 5 ቀን 2008 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች መታሰራቸውን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫው ተቃዋሚዎችን ማሰር መዘዝ ያመጣል የሚል መልዕክት አስተላልፎ የነበር ሲሆን በሚያዚያ 21 ቀን 2008 ደግሞ በተመሳሳይ ባውጣው መግለጫ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር በቀለ ገርባ እና ሌሎች የክልሉ ነዋሪዎች በሽብር ክስ መከስሳቸው መንግስት የፀረ ሽብር አዋጁን ጋዜጠኞችን የፖለቲካ ፓርቲ መሪ እና አባላትን እና አክቲቪስቶችን ዝም ለማሰኛት መጠቀሙን እንዲያቆም ጠይቆ ነበር።